በግብጽ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የአባይን “ውሃ የመጋራት” ጥያቄ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ “በኃላፊነት ለመፍታት”፤ የአሜሪካንን ሽምግልና ዳግም ለማስጀመር ዝግጁ መሆናቸውን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገለጹ። ፕሬዝዳንት ትራምፕ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለውን ውጥረት መፍታትን ቅድሚያ የሰጡት፤ በግብጽ እና በኢትዮጵያ መካከል “ከፍተኛ ወታደራዊ ግጭት” እንዳይቀሰቀስ “ለመከላከል” እንደሆነ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ አስታውቀዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የህዳሴውን ግድብ ድርድር እንደገና ለማስጀመር መዘጋጀታቸውን የገለጹት፤ ለግብጹ አቻቸው አብዱል ፋታህ አልሲሲ ትላንት አርብ ጥር 8፤ 2018 በጻፉት ደብዳቤ ነው። የፕሬዝዳንቱ ደብዳቤ በቅደም ተከተል ለሳዑዲ አረቢያው ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን፣ ለተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ፕሬዝደንት ሼኽ ሞሐመድ ቢን ዛይድ አልናህያን፣ ለኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ እና ለሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር አብደል-ፋታህ አል-ቡርሃን ግልባጭ ተደርጓል።
ትራምፕ ለአልሲሲ በጻፉት ደብዳቤ፤ “በግል ጓደኝነታቸው” እና አሜሪካ “ለግብጽ ህዝብ ሰላም እና ደህንነት ባላት ቁርጠኝነት መንፈስ” በኢትዮጵያ እና የግብጽ መካከል የሚካሄድን ድርድር ዳግም ለማስጀመር ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል። የአሜሪካ ሽምግልና በግብጽ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የአባይን “ውሃ የመጋራት” ጥያቄ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ “በኃላፊነት ለመፍታት” የሚደረግ እንደሚሆንም አመልክተዋል።

የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር በመጀመሪያው የስልጣን ዘመኑ፤ ኢትዮጵያ፣ ግብጽን እና ሱዳንን በማደራደር ለችግሩ እልባት ለማምጣት ያደረገው ጥረት አልተሳካም። የሀገሪቱ የወቅቱ የግምጃ ቤት ኃላፊ በነበሩት ስቲቨን መኑሽን መሪነት፤ የሶስቱን ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጨምሮ ሌሎች ተደራዳሪዎችን ያሳተፈ ተከታታይ ድርድር ከተካሄደ በኋላ የስምምነት ሰነድ ተዘጋጅቶ ነበር።
ይሁንና የስምምነት ሰነዱ ይፈረምበታል በተባለው በየካቲት ወር 2012 በአሜሪካ በተካሄደው የመጨረሻው ዙር ውይይት ላይ፤ ኢትዮጵያ ሳትገኝ ቀርታለች። ኢትዮጵያ በውይይቱ ላይ ያልተገኘችው፤ በአሜሪካ ግምጃ ቤት እና በዓለም ባንክ የተዘጋጀው የስምምነት ሰነዱ “አድሎአዊ ይዘት ያለው”፣ “የግብጽን ታሪካዊ የውሃ ድርሻ ፍላጎት የሚያስጠብቅ ነው” በሚል ተቃውሞ ነበር።
ኢትዮጵያ ከፊርማው በፊት “በሀገር ውስጥ ምክክር ያስፈልገኛል” በማለት በድርድሩ ባለመገኘቷ የትራምፕ አስተዳደር ግፊት ሲያደርግበት የነበረው ስምምነት ሳይካሄድ ቀርቷል። አሜሪካ በህዳሴው ግድብ ድርድር ላይ የነበራትን ጉልህ ሚና በየጊዜው ሲጠቅሱ የሚደመጡት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ “በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል ያለን ጦርነት” አስቁሜያለሁ ሲሉ ከእውነታው የራቀ መልዕክትም በተደጋጋሚ ሲያስተላልፉ ቆይተዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በትላንቱ ደብዳቤያቸው፤ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ያለው ሙግት በኢትዮጵያ እና ግብጽ መካከል ወደ “ከፍተኛ ወታደራዊ ግጭት” እንደማያመራ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ማሳድ ቡሎስም የትራምፕን ደብዳቤ ተከትሎ በኤክስ ገጻቸው ላይ ተመሳሳይ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለውን ውጥረት መፍታትን ቅድሚያ የሰጡት፤ በግብጽ እና በኢትዮጵያ መካከል “ከፍተኛ ወታደራዊ ግጭት” እንዳይቀሰቀስ “ለመከላከል” እንደሆነ አማካሪው ገልጸዋል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በትላንቱ ደብዳቤያቸው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለውን ውጥረት መፍታት “ከዋነኛ አጀንዳቸው” መካከል መሆኑን አረጋግጠዋል።
“እኔና የቡድኔ አባላት የናይል ወንዝ ለግብጽ እና ለሕዝቧ ያለውን ጥልቅ ጠቀሜታ እንረዳለን” ያሉት ትራምፕ፤ የግብጽ፣ የሱዳን እና የኢትዮጵያን የውሃ ፍላጎቶች ለረጅም ጊዜ የሚያረጋግጥ ውጤት እንዲገኝ የማገዝ ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል። በቀጣናው ውስጥ ያለ ማንኛውም ሀገር “የናይልን ውድ ሀብት ብቻውን መቆጣጠር” እና “በዚህም ጎረቤቶቹን መጉዳት እንደሌለበት” የአሜሪካ አቋም መሆኑንም ፕሬዝዳንት ትራምፕ በደብዳቤያቸው ላይ አስፍረዋል።

በትክክለኛው የቴክኒክ ባለሙያዎች መካከል በሚደረግ “ፍትሃዊ እና ግልጽ ድርድር”፤ ሁሉም የናይል ተፋሰስ አገሮች ዘላቂ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚችሉ እምነታቸው መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ አመልክተዋል። አሜሪካ ድርድሩን በማስተባበር እና በመምራት “ጠንካራ ሚና” እንደሚኖራትም ፕሬዝዳንት ትራምፕ በደብዳቤያቸው ገልጸዋል። ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን፤ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በአሜሪካ ከተመራው ውጭ ለዓመታት ሲያደርጉት የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር ስምምነት ሳይደረስበት መቅረቱ ይታወቃል።
አስራ ስድስት አንቀጾች ባሉት የጋራ መደራደሪያ ሰነድ ላይ ተመስርቶ ሲካሄድ በቆየው የሶስትዮሽ ድርድር፤ ከፍተኛ ልዩነት የታየው በድርቅ ወቅት በሚኖረው የውሃ አያያዝ እና አለቃቀቅ ላይ ነበር። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ዳግም ለማስጀመር ባሰቡት አሜሪካ መራሽ ድርድር፤ በድርቅ ወቅት እና ለረጅም ጊዜ በሚቆዩ የድርቅ ዓመታት ውስጥ ለግብጽ እና ለሱዳን ሊገመት የሚችል የውሃ ልቀት እንዲኖር ዋስትና የሚሰጥ “ስኬታማ አካሄድን” እንደሚከተሉ አስታውቀዋል።
ይህ የድርድር አካሄድ፣ ኢትዮጵያን ከፍተኛ መጠን ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል እንድታመነጭ “ያስችላል” ያሉት ትራምፕ፤ ኢትዮጵያ ከምታመነጨው ኃይል ምናልባትም “የተወሰነውን” ለግብጽ እና ለሱዳን “ልትሰጥ” ወይም “ልትሸጥ” እንደምትችል ገልጸዋል።

ለ13 ዓመታት በተለያየ መልኩ ሲካሄድ የነበረው ድርድር ያለስምምነት ከተጠናቀቀ በኋላ፤ ግብጽ በቀጣይነት ድርድር የማድረግ ፍላጎት እንደሌላት በመሪዎቿ በኩል በተደጋጋሚ ገልጻለች። ሆኖም “ታሪካዊ” የምትለው የውሃ ድርሻዋ እንዳይነካ “እስከ ኃይል አማራጭ” የሚደርስ እርምጃ እንደምትወስድም ዝታለች።
ግብጽ በህዳሴው ግድብ ላይ በዋናነት የምታቀርበው ተቃውሞ፤ “የማገኘውን የውሃ መጠን ይቀንስብኛል” የሚል ነው። በተለያዩ ጊዜያት የተለያየ አቋም በማንጸባረቅ የምትታወቀው ሱዳን ደግሞ “ከግድቡ የሚለቀቀው የውሃ መጠን ወጥነት የሌለው ከሆነ በአነስተኛ ግድቦቼ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል” የሚል ስጋት እንዳላት ትገልጻለች።
በእነዚህ ምክንያቶች ሁለቱ ሀገራት የግድቡን የውሃ ሙሌት እና በየዓመቱ ከግድቡ የምትለቀውን የውሃ መጠን በተመለከተ ኢትዮጵያ አስገዳጅ ስምምነት እንድትፈርም ይፈልጋሉ። ኢትዮጵያ በበኩሏ አስገዳጅ ስምምነት ላይ የመድረስ ጥያቄን ፈጽሞ እንደማትቀበል አቋምን ስታንጸባርቅ ቆይታለች።
ግብጽ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በተደጋጋሚ ብትወስድም፤ በኢትዮጵያ ላይ እንዲተላለፍ የምትሻውን ውሳኔ ማሳካት አልቻለችም። በድንበር ተሻጋሪ ውሃ ምክንያት የተፈጠረን አለመግባባት ለመጀመሪያ ጊዜ በአጀንዳነት ተቀብሎ የተወያየው የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት፤ ጉዳዩን ወደ አፍሪካ ህብረት መመለሱ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)





























