በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ግጭት ለነዋሪዎች መፈናቀል ምክንያት መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። በእነዚህ አካባቢዎች የተቀሰቀሰውን “ግጭት እና ወታደራዊ እንቅስቃሴ” ተከትሎ፤ ሁኔታው ወደ “ጦርነት” ሊሸጋገር ይችላል የሚል ሥጋት መፈጠሩን ኮሚሽኑ ገልጿል።
ብሔራዊው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ይህን የገለጸው ዛሬ አርብ ጥር 22፤ 2018 ምሽት ባወጣው መግለጫ ነው። በእነዚህ ግጭቶቹ የተቀሰቀሱት ካለፈው ሳምንት እሁድ ጥር 17 ጀምሮ መሆኑን ኢሰመኮ በዛሬ መግለጫው ላይ አመልክቷል።
ግጭቶቹ በወለዱት ስጋት ነዋሪዎች “በኮማንድ ፖስት” ሲተዳደሩ ከቆዩት አላማጣ ከተማ እና ሌሎች አካባቢዎች “እየተፈናቀሉ” መሆናቸውን እንዲሁም በሰዎች እንቅስቃሴ ላይ “ገደቦች መጣላቸውን” እንደተገነዘበም ኮሚሽኑ ገልጿል። በተለይም “በጸለምት/ጠለምት፣ በመጋሌ እና አብአላ” አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶችን ተከትሎ፤ የሰዎችን የሕይወት፣ የአካል ደህንነት፣ ነጻነት እና ንብረት መብቶች ሥጋት ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ኢሰመኮ ጠቅሷል።
ግጭቶቹ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ተከትሎ በአካባቢዎቹ ሰፍኖ የነበረውን አንጻራዊ ሰላም እና መረጋጋት ወደ ኋላ የሚመልስ እንደሆነ ኮሚሽኑ አመልክቷል። ከዚህም አልፎ የአካባቢዎቹን ነዋሪዎች ለተጨማሪ ጉዳት፣ መፈናቀል እና ሌሎች ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የሚያጋልጥ እንደሆነ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ በመግለጫው አጽንኦት ሰጥቷል።
በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ችግሩን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ ጥሪ ያቀረበው ኢሰመኮ፤ የግጭቱ ተሳታፊዎች፤ በሲቪል ሰዎች እና መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃቶችን ከማድረስ እንዲታቀቡም አሳስቧል። እነዚህ አካላት ለግጭት መነሻ የሆኑ ልዩነቶችን “በሕግ መሠረት በምክክርና በመግባባት ለመፍታት በቁርጠኝነት እንዲሠሩ” ኮሚሽኑ ጠይቋል።
ማናቸውም እርምጃዎች የሰብአዊ መብቶች መርሆዎችን ያከበሩ መሆን እንዳለባቸው እና በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚጣሉ ገደቦች በዓለም አቀፍና ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ማዕቀፎች መሠረት የሕጋዊነት፣ የጥብቅ አስፈላጊነት እና የተመጣጣኝነት መርሆዎችን ያከበሩ እንዲሆኑም ኢሰመኮ በመግለጫው አስገንዝቧል። ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር የተፈጠረው ግጭት በውይይት የሚፈታበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት እንደሚያደርግም ኢሰመኮ ገጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)





























