ከወለድ ነጻ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች ከሸሪዓ መርሆዎች እና ሕግጋቶች ጋር በተጣጣመ መልኩ በመንግሥት ግምጃ ሰነድ ግብይት ላይ እንዲሳተፉ የሚያስችላቸው ስርዓት በቀጣይ ሶስት ወራት ተግባራዊ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ። ባለፈው ስድስት ወራት ብቻ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ የተጣራ የመንግስት የበጀት ፍላጎት በግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ ማሟላት መቻሉንም ብሔራዊ ባንክ ገልጿል።
ባንኩ ይህን የገለጸው የራሱን እና የተጠሪ ተቋማቱን የግማሽ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት፤ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፕላን በጀት እና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ ሰኞ ጥር 26፣ 2018 ባቀረበበት ወቅት ነው። ሪፖርቱን ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረቡት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ፤ ተቋማቸው በቀጣዩ ሩብ ዓመት ከሚያከናውናቸው ጉዳዮች መካከል ከሸሪዓ መርሆዎች እና ሕግጋት ጋር ተስማሚነት ያለው የመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ ግብይት ስርዓት ማዘጋጀት አንዱ መሆኑን አስረድተዋል።
አሁን ያለው አሰራር ከሸሪዓ መርህ ጋር አብሮ የሚሄድ ባለመሆኑ፤ ከወለድ ነጻ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች በመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ ላይ እንዳይሳተፉ እንዳደረጋቸው ዶ/ር እዮብ ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ በሸሪዓ ሕግጋት ላይ ተመሥርተው አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች፤ ዘምዘም፣ ሂጅራ፣ ራሚስ እና ሸበሌ ናቸው።

እነዚህን መሰል ባንኮች በመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ ግዢ ላይ እንዲሳተፉ የሚያስችላቸው ስርዓት በኢትዮጵያ እስካሁን ባይዘጋጅም፤ በቀሪው ዓለም ግን “ሱኩክ” (Sukuk) የተሰኘ ከሸሪዓ መርህ ጋር የተጣጣመ የፋይናንስ አካሄድ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል። “ሱኩክ” የሚለው ስያሜ የመጣው፤ “ሰርተፍኬት” ወይም “የክፍያ ትዕዛዝን” ከሚያመለክተው “ሳክ” ከሚለው የአረብኛ ቃል ነው።
“ሱኩክ” በቋሚ ንብረት ወይም አገልግሎት ላይ ያለን ባለቤትነት የሚወክል ሰነድ ነው። በአንድ ፕሮጀክት ወይም ንብረት ላይ መዋዕለ ንዋይ ያፈሰሱ ኢንቬስተሮች የሚያገኙት ትርፍ ከሸሪዓ መርህ ጋር የተጣጣመ በመሆኑ በወለድ ላይ ከተመሰረተው ከተለመደው የቦንድ ሰነድ እንዲለይ ያደርገዋል።
ብሔራዊ ባንክ ከሶስት ወራት በኋላ ተግባራዊ የሚያደርገው ስርዓት ከሸሪዓ መርህ ጋር “የሚመጣጠን” እንደሆነ ዶ/ር እዮብ በዛሬው የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል። ይህ ስርዓት ተፈጻሚ የሚሆንበት የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ ግብይት በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው በኢትዮጵያ ሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያ በኩል ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለበጀት ጉድለት ማሟያ የሚጠቀምባቸው የግምጃ ቤት ሰነዶችን (T-Bills) ሽያጭ፤ በሰነደ መዋለ ንዋዮች ገበያ በኩል እንዲከናወን የተደረገው ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ ነው። በጨረታ ወይም ያለ ጨረታ ለሽያጭ የሚቀርቡት የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነዶች፤ 28፣ 91፣ 182 እና 364 ቀናት “የክፍያ ቆይታ ጊዜ” (maturity period) አላቸው።
የገንዘብ ሚኒስቴር ባለፈው ታህሳስ ወር መጨረሻ ያወጣው የሶስተኛው ሩብ ዓመት የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ ጨረታ፤ 288.28 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው ነበር። የገንዘብ ሚኒስቴር ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ የተጣራ የበጀት ፍላጎቱን በግምጃ ቤት ሰነድ ማሟላት መቻሉን የብሔራዊ ባንክ ገዢው በዛሬው የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)





























