ወደ ትግራይ ከተሞች ተቋርጦ የነበረው የአየር በረራ ከነገ ጀምሮ ዳግም ሊጀመር ነው

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላለፉት አምስት ቀናት አቋርጧቸው የነበሩትን ወደ ትግራይ ክልል የሚደረጉ የመንገደኞች በረራዎች ከነገ ማክሰኞ ጥር 26፤ 2018 ጀምሮ ዳግም ሊጀምር እንደሆነ የተቋሙ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። አየር መንገዱ በዛሬው ዕለት የበረራ ትኬቶች ሽያጭ ሲያከናውን መዋሉን የትኬት ቢሮ ሰራተኞች እና መንገደኞች ተናግረዋል።

በመቐለ ከተማ የሚገኘው ድሪም የአውሮፕላን ትኬት መሸጫ ቢሮ፤ ለነገ ስምንት በረራዎች እንዳሉ ተገልጾላቸው ሽያጭ ሲያከናውን መዋሉን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቋል። ለነገ በረራዎች የተዘጋጁ ሁሉም ትኬቶች ተሽጠው ማለቃቸውን የገለጸው ድርጅቱ፤ ለረቡዕ ጉዞ የሚሆኑ ትኬቶችን ከነገ ጠዋት ጀምሮ ለሽያጭ እንደሚያቀርቡ አመልክቷል።

የአየር መንገዱ በረራ ከተቋረጠባቸው የትግራይ ከተሞች መካከል አንዱ ወደ ሆነው ሽረ ከተማ፤ በነገው ዕለት ከጠዋቱ 12፡40 ጀምሮ ከአዲስ አበባ የሚነሳ በረራ እንዳለ ተቋሙ ዛሬ በድረ ገጹ ላይ ሲያስተዋውቅ ውሏል። ከአዲስ አበባ ወደ አክሱም ከተማ ከጠዋቱ 1፡50 ጀምሮ የሚደረግ በረራ መኖሩንም የተቋሙ ድረ ገጽ በተመሳሳይ ሁኔታ አመልክቷል።

ከአክሱም ወደ አዲስ አበባ የሚደረግ የመንገደኞች በረራ በነገው ዕለት እንደሚኖር ከአየር መንገዱ መልዕክት እንደደረሳቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። እኚሁ ግለሰብ እናታቸው ከ15 ቀናት በፊት ለሰርግ ወደ አክሱም ከተማ መጓዛቸውን እና በመጪው የካቲት 5 ለመመለስ ትኬት ቆርጠው እንደነበር አስታውሰዋል። 

ሆኖም ወደ ትግራይ ከተሞች የሚደረገው በረራ መቋረጡን ተከትሎ፤ ከዚህ በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን አይነት ጦርነት ከተጀመረ “ከእናታችን ጋር ተለያይተን ልንቀር ነው” በሚል ስጋት ምክንያት መላው ቤተሰብ ጭንቀት ላይ ወድቆ እንደነበር  ግለሰቡ አስረድተዋል። በዚህም ምክንያት አየር መንገዱ በረራ ድንገት ከተጀመረ “የጉዞ ማስተካከያ” ለማድረግ ወስነው በየቀኑ ክትትል ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስረድተዋል።

የአዲስ አበባው ነዋሪ ክትትላቸው ፍሬ አፍርቶ፤ በነገው ዕለት ከአክሱም ወደ አዲስ አበባ ለሚደረግ በረራ ዛሬ ትኬት አግኝተው መቁረጣቸውን አብራርተዋል። ከአየር መንገዱ ትኬት ቢሮም የቅድመ በረራ ማረጋገጫ እንዲያደርጉ የኢሜይል መልዕክት እንደደረሳቸውም አመልክተዋል።

በደረሳቸው የኢሜይል መልዕክት መሰረት ከአክሱም ወደ አዲስ አበባ ለሚደረገው በረራ “ቼክ-ኢን” ማድረጋቸውን እና በረራው ለነገ ጠዋት አራት ሰዓት ዝግጁ መሆኑን የሚገልጽ የማረጋገጫ መልዕክት እንደደረሳቸውም አክለዋል። አንድ የመቐለ ከተማ ነዋሪም ተመሳሳይ መልዕክት ዛሬ ከሰዓት እንደደረሳቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የእነዚህን የኢትዮጵያ አየር መንገድ መልዕክቶች እና የአየር በረራው ዳግም መጀመርን በተመለከተ ለተቋሙ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፤ በተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ ማግነት አልቻልንም። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ትግራይ ከተሞች በረራ ያቋረጠበትን ምክንያት እስካሁን በይፋ አልገለጸም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)