የአሜሪካው አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ባለፈው ሳምንት በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰቱ ሁነቶች፤ ለሰላም እና መረጋጋት “ዘላቂ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ” “አስታዋሽ” መሆናቸውን ገለጹ። አምባሳደሩ “ወደ ዘላቂ ሰላም የሚመራው የተሻለ መንገድ” “ምክንያታዊ እና የሰከኑ ውይይቶች” እንደሆነም አስታውቀዋል።
ማሲንጋ ይህንን ያሉት፤ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ዛሬ ሐሙስ ጥር 28፤ 2018 በተሰራጨ መልዕክታቸው ነው። የአምባሳደሩ መልዕክት በመከላከያ ሰራዊት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ጸለምት/ጠለምት በተባለው አካባቢ በተፈጠረ ግጭት ያንዣበበው ውጥረት የመርገብ አዝማማሚያ ማሳየቱን ተከትሎ የተሰጠ ነው።

ውጥረቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መቐለ፣ አክሱም እና ሽረን ወደ መሳሰሉ የትግራይ ክልል ከተሞች የሚያደርጋቸውን በረራዎች እስከማቋረጥ ደርሶ ነበር። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት እና የአውሮፓ ህብረት በየፊናቸው ባወጧቸው መግለጫዎች፤ ውጥረቱ እንዲረግብ እና ልዩነቶች በፕሪቶሪያ በተፈረመው ግጭት የማቆም ስምምነት እንዲፈቱ በወቅቱ ግፊት አድርገዋል።
ህወሓት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዮሱፍ በጻፈው ደብዳቤ፤ በትግራይ እና በፌደራል መንግስት መካከል ያሉ ልዩነቶችን “በንግግር ለመፍታት” “ዝግጁ እንደሆነ” አቋሙን አሳውቋል። የሰሞኑን ግጭት በተመለከተ በፌደራል መንግስት በኩል እስካሁንም በይፋ የተሰጠ መግለጫም ሆነ ለጥሪዎቹ የተሰጠ ምላሽ የለም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































![“ኢትዮጵያ በህዳሴ [ግድብ] ላይ አንድም ብር እርዳታ፤ አንድም ብር ብድር አልወሰደችም” – ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ](https://ethiopiainsider.com/wp-content/uploads/2026/01/Grand-Ethiopian-Renaissance-Dam-GERD-in-September-2025-Office-of-the-Prime-Minister-of-Ethiopia-218x150.jpeg)
