ኢትዮጵያ ለህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ምንም አይነት “ብድር” እና “እርዳታ” እንዳላገኘች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። የህዳሴ ግድብ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ያሉ ኢትዮጵያውያን “በቁርጠኝነት” “በጋራ ቆመው የሰሩት” ፕሮጀክት መሆኑን አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያስታወቁት፤ ዛሬ ማክሰኞ ጥር 26፤ 2018 በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከፓርላማ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው። የፓርላማ አባላቱ ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል በግማሽ ዓመት ውስጥ የነበረው የፌደራል መንግስት የፕሮጀክቶች አፈጻጸምን የተመለከተው ይገኝበታል።
አብይ ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ “ህዳሴን ካለ አንድ ብር እርዳታ፣ ካለ አንድ ብር ብድር ያሳካ መንግስት እና ህዝብ ‘ፕሮጀክት ሊሰራ አይችልም’ ሊባል አይችልም” ብለዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ፤ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ወጪን በተመለከተ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሞኑ ደጋግመው ካነሱት አስተያየት ጋር ተገጣጥሟል።

ትራምፕ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የተገነባው “በአብዛኛው በአሜሪካ ገንዘብ እንደሆነ” በተደጋጋሚ ተናግረው ነበር። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የግድቡን ወጪ በተመለከተ ያላቸውን ይህን መሰሉን አስተያየት ከመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው ጀምሮ ሲያንጸባርቁ ቆይተዋል።
የዛሬ ሁለት ሳምንት ገደማ ጥር 13፤ 2018 በስዊትዘርላንድ ዳቮስ በተካሄደው የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ጎን ለጎን ከግብጹ አቻቸው ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ጋር በተወያዩበት ወቅትም ይህንኑ ጉዳይ በድጋሚ አንስተዋል። ፕሬዝዳንቱ በዚሁ ውይይታቸው የህዳሴው ግድብ ከዓለም ግዙፍ ግድቦች አንዱ እንደሆነ አመልክተው፤ ወጪው በአሜሪካ መሸፈኑን ተናግረዋል።
ትራምፕ ይህን መሰል አስተያየት በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲናገሩ ቢደመጡም፤ ኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ ላይ ይፋዊ ምላሽ ሳትሰጥ ቆይታለች። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ ስለ ህዳሴው ግድብ የገንዘብ ምንጭ የተናገሩት፤ የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት በቀጥታ የጠቀሰ ባይሆንም ለትራምፕ አስተያየት የተሰጠ ምላሽ የሚመስል ገለጻን የተጠቀመ ነው።

“ኢትዮጵያ በህዳሴ [ግድብ] ላይ አንድም ብር እርዳታ፤ አንድም ብር ብድር አልወሰደችም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የፕሮጀክቱ ወጪ የተሸፈነው በኢትዮጵያውያን ብቻ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል። “[ግድቡ] በጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ቁርጠኛ አቋም፤ በሀገር ውስጥም፣ በሀገር ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን በቁርጠኝነት ጨክነው በጋራ ቆመው ስለሰሩ የተከወነ ፕሮጀክት ነው” ብለዋል አብይ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































