በአማራ እና ትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ ከሚነሳባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ የሆነውን የወልቃይት ጉዳይ እርሳቸውም ሆነ የፓርላማ አባላት “እንደማይወስኑ” ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጹ። በወልቃይት ህዝብ ህልውና ላይ “መወሰን” የሚችለው “የእዚያው አካባቢ ህዝብ” መሆኑን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የፌደራል መንግስት አቋም አሁንም ጉዳዩ “በህዝበ ውሳኔ (ሪፈረንደም) እና በህጉ አግባብ ይወሰን” የሚል መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት ዛሬ ማክሰኞ ጥር 26፣ 2018 ከህዝብ ተወካዮች ምክር አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው። ከሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ጉዳይ በጥያቄያቸው ያነሱት አብዱ ሀሰን የተባሉ የፓርላማ አባል፤ ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው ለመመለስ የፌደራል መንግስት እያከናወናቸው የሚገኙ ስራዎች “በምን ደረጃ ላይ” እንደሚገኙ ጠይቀዋል።
“ህወሓት ለዓመታት ሲያደርገው እንደነበረው የተፈናቀሉ ዜጎችን ለፖለቲካ ዓላማ ሲጠቀምባቸው ይታያል” ሲሉ የወነጀሉት የፓርላማ አባሉ፤ ለተፈናቃዮች “ድጋፍ እንዳይደርስ” እና “ወደ ቀዬአቸው እንዳይመለሱ እያደረገ ይገኛል” በማለት ከስሰዋል። “ይህንን ሁኔታ ለመፍታት በፌደራል መንግስት በኩል ምን እየተሰራ ይገኛል?” ሲሉም ተያያዥ ጥያቄ አስከትለዋል።

ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ በጉዳዩ ላይ የፌደራል መንግስት “ጽኑ እምነት” ያሉትን አስረድተዋል። “የወልቃይት አካባቢ ነዋሪዎች ከትግራይም ይፈናቀሉ፣ ከወልቂጤም ይፈናቀሉ፣ ከአሶሳም ይፈናቀሉ፤ ወልቃይት በሰላማዊ መንገድ መኖር 100 ፐርሰንት መብታቸው ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግስታቸውን አቋም አስታውቀዋል።
“ወልቃይትን በሚመለከት ሁላችሁም ታውቃላችሁ ሚስጢር አይደለም። የይገባኛል ጥያቄ በአማራ እና በትግራይ ክልል ለረጅም ጊዜ ቆይቷል። ሁለቱም ክልሎች ማስረጃ አስደግፈው፤ ተቀባይነት ይኑረውም አይኑረውም ‘ይሄ ቦታ ይገባኛል’ ይላሉ። ፌደራል መንግስት እያለ ያለው፤ ‘ሰው አይፈናቀል፣ ባለበት ይመለስ፣ ራሱን ያስተዳድር፣ ራሱ ይወስነው ነው” ሲሉም አብይ አክለዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ባስቆመው የፕሪቶሪያው ስምምነት ላይ፤ “አወዛጋቢ ቦታዎችን” በተመለከተ ያሉ ጉዳዮች የሚፈቱት በኢፌዲሪ ህገ መንግስት መሰረት እንደሆነ ሰፍሯል። የፕሪቶሪያው ስምምነት አንዱ ፈራሚ የሆነው የፌዴራል መንግስት፤ የወልቃይት እና ሌሎች አወዛጋቢ ቦታዎችን ጉዳይ “በሕዝበ-ውሳኔ” ለመፍታት የሚያስችሉ ሂደቶችን እንደሚተገብር በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።
“የወልቃይት አካባቢ ነዋሪዎች ከትግራይም ይፈናቀሉ፣ ከወልቂጤም ይፈናቀሉ፣ ከአሶሳም ይፈናቀሉ፤ ወልቃይት በሰላማዊ መንገድ መኖር 100 ፐርሰንት መብታቸው ነው”
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዛሬው የፓርላማ ማብራሪያቸው ይህንኑ ጉዳይ በድጋሚ አስተጋብተዋል። የፌደራል መንግስት የወልቃይትን ጉዳይ “አንድ ሰው እዚህ ተቀምጦ ከሚወስን”፤ “በሪፈረንደም”፣ “በህግ አግባብ” እንዲወሰን እንደሚሻ የገለጹት አብይ፤ “በዚያ ህዝብ ህልውና እና መሻት ላይ አሁን ማን መወሰን ይችላል? ማን ከእናንተ መካከል መወሰን ይችላል?” ሲሉ ለፓርላማ አባላቱ ጥያቄ አዘል አስተያየት ሰንዝረዋል።
“ራሱ ህዝቡ፣ ቤቱ ገብቶ፣ በሰላም ኖሮ ‘እኔ ልተዳደር የሚገባኝ፣ እዚህ ወይም እዚያ ነው’ ካላለ በቀር፤ የትኛው ባለስልጣን ነው የሚገባህ እዚህ ነው ብሎ መወሰን የሚችለው?” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለዋል። እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ኃላፊዎች እና የህወሓት አመራሮች፤ የወልቃይት አካባቢ “በትግራይ ክልል ስር መሆን አለበት” የሚል ግልጽ አቋም አላቸው።
ኃላፊዎቹ እና አመራሮቹ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ከአካባቢው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀዬአቸው ከመመለሳቸው በፊት፤ ቀድሞ የነበረው የምዕራብ ትግራይ ዞን አስተዳደር መዋቅር ወደ አካባቢው መመለስ እንዳለበት ይሟገታሉ። ወልቃይትን በተመለከተ የትግራይ፣ የአማራ እና የፌደራል መንግስታት የሚያራምዷቸው የተለያዩ አቋሞች፤ አካባቢው በጸጥታ ስጋት እና ውጥረት ውስጥ እንዲቆይ አድርጎታል።

ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ በጸለምት/ ጠለምት አካባቢ በትግራይ ኃይሎች እና በመከላከያ ሰራዊት አባላት መካከል የተፈጠረው ግጭት፤ አካባቢው ወደ ለየለት ጦርነት እንዳይገባ ስጋት ፈጥሮ ቆይቷል። ይህንኑ በተመለከተ ባለፈው ቅዳሜ ጥር 23፤ 2018 ለትግራይ ቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ የሰጡት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናል ጀኔራል ታደሰ ወረደ፤ የግጭቱ ምክንያት “ወደ ግዛታችን ለመግባት ፍላጎት እንዳለን ለማስታወስ ነበር” ሲሉ ተደምጠዋል።
የትግራይ ኃይሎች ወደ አካባቢው ያቀኑት “ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ግጭት ሳይፈጥሩ” ይህንኑ ለማሳካት ቢሆንም፤ ባልጠበቁት መልኩ ግጭት መፈጠሩን ፕሬዝዳንቱ በቃለ ምልልሳቸው ላይ አመልክተዋል። በዚህም ምክንያት ወደ ስፍራው የተላኩት ኃይሎች እንዲመለሱ ማዘዛቸውን አስረድተዋል።
ከትግራይ ኃይሎች ጋር ሰሞኑን ስለተፈጠረው ግጭት በዛሬው የፓርላማ ቆይታቸው ያልተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ፤ የወልቃይት አካባቢ ተፈናቃዮች ጉዳይ ግን “ችግር” እንደሆነባቸው ገልጸዋል። እልባት ያልተገኘለት የወልቃይት ይገባኛል ጥያቄ፤ የፌደራል መንግስት ለአካባቢው ሊያደርገው የሚገባውን ድጋፍ እንዳስተጓጎለ አብይ በዛሬው ማብራሪያቸው ላይ ጠቅሰዋል።
“ባለፉት ዓመታት የወልቃይት ህዝብ እንደ የትኛውም ኢትዮጵያዊ የሚገባውን በጀት ማግኘት ሲገባው፣ ትምህርት መደገፍ ሲገባው፣ ጤና መደገፍ ሲገባው፣ የፌደራል መንግስት ማገዝ የሚገባውን ነገር ሳይግዘው እንዲቆይ ያደረገው [ይኸው] ጉዳይ [ነው]” ሲሉ አብይ ተናግረዋል። የወልቃይት አካባቢ ነዋሪዎች “ዛሬ ከሰዓት እንኳን ቢመጡ እንቀበላቸዋለን” ያሉት አብይ፤ የኢትዮጵያ መንግስት አቅም በፈቀደ መጠን ኑሮአቸው እንዲመቻች እገዛ እንደሚያደርግ አክለዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በሁመራ ከተማ ጉብኝት ያደረጉት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ፤ ቅድሚያ መሰጠት ያለበት በአካባቢው ባለው ሁኔታ “በእጅጉ ለተጠቁ” ሰዎች “ደህንነት” እንደሆነ ተናግረው ነበር። ከጉብኝታቸው በኋላ ሁሉም ወገኖች “ከፖለቲካ በላይ ህዝቡን እንዲያስቀድሙ” የጠየቁት የአሜሪካው አምባሳደር፤ በወልቃይት አካባቢ የሚኖረው ህዝብ “በተገቢው ጊዜ” “የፖለቲካ እጣ ፈንታውን በራሱ እንዲወስን” ሊደረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዛሬው የፓርላማ ማብራሪያቸው፤ ከዚሁ ጋር ተመሳሳይነት ያለው አቋም አንጸባርቀዋል። “የወልቃይትን ጉዳይ እኔ አልወስንም። ተስፋ አደርጋለሁ እናንተም አትወስኑም። የሚወስነው የእዚያ አካባቢ ህዝብ ነው። ለዚያ ፓርቲዎች አስቻይ ነገር መፍጠር የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል” ሲሉ ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)





























