ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የትግራይ ክልል ምክር ቤትን ወደ ስራ መመለሱ እና “የተናጠል የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላን” ተግባራዊ ማድረጉ፤ “የፕሪቶሪያ ስምምነት ድንጋጌዎችን የሚጥስ ነው” ሲል በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ተቸ። የፕሪቶሪያ ስምምነትን በተጨባጭ ተፈጻሚ ለማድረግ፤ በሁሉም ወገኖች የሚደረጉ ውይይቶች “በአስቸኳይ” በድጋሚ መጀመር እንዳለባቸውም ልዑኩ አሳስቧል።
የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ይህን ያለው፤ በትግራይ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ዛሬ ቅዳሜ ሰኔ 20፤ 2018 ባወጣው አጭር መግለጫ ነው። የህብረቱ ልዑክ በዚሁ መግለጫው፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው “ውጥረት የተሞላበት ሁኔታ እንደሚያሳስበው አስታውቋል።
ሃያ ሰባት ሀገራትን በአባልነት ያቀፈው የአውሮፓ ህብረት በአሳሳቢነት ከጠቀሳቸው ሰሞነኛ ጉዳዮች አንዱ፤ ህወሓት “ትይዩ የክልል ምክር ቤት” ማቋቋሙን ነው። ህወሓት በጳጉሜ 2012 ዓ.ም. በተደረገ አወዛጋቢ ምርጫ የተመረጠውን የትግራይ ክልል ምክር ቤት “ወደ ስራ እንዲመለስ” የወሰነው ባለፈው ሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ ነበር።
የክልሉ ምክር ቤት በዚሁ ወር መጨረሻ ላይ ባደረገው የመጀመሪያ ስብሰባው፤ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልን የክልሉ ፕሬዝዳንት አድርጎ ሾሟል። የዶ/ር ደብረጽዮን ሹመት፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን ለአንድ ዓመት ያህል በፕሬዝዳንትነት ሲመሩ የቆዩት የሌተናል ጄነራል ታደሰ የፕሬዝዳንትነት የስልጣን ዘመን እንዲያበቃ ምክንያት ሆኗል።
ዶ/ር ደብረጽዮን ወደ ትግራይ ክልል መሪነት ከመመለሳቸው ሶስት ሳምንት አስቀድሞ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሌተናል ጄነራል ታደሰን የስልጣን ዘመን ለተጨማሪ አንድ ዓመት አራዝመው ነበር። በትግራይ ዳግም ጦርነት ለመቀስቀስ ምክንያት እንዳይሆን ተሰግቶ የነበረውን ይህን ክስተት ተከትሎ የአውሮፓ ህብረት ባወጣው መግለጫ፤ በክልሉ “ሌላ አጥፊ ግጭት እንዳይከሰት መከላከል እጅግ አስፈላጊ እና የማይታለፍ ጉዳይ ነው” ብሎ ነበር።
በትግራይ ክልል ያለው “ውጥረት በአስቸኳይ እንዲረግብ” በሚያዝያ መግለጫው ጥሪ ያቀረበው የአውሮፓ ህብረት፤ የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነትን አደጋ ላይ ከሚጥሉ “ማናቸውም ድርጊቶች መቆጠብ እንደሚገባ” አሳስቧል። በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ በዛሬው መግለጫው፤ በህወሓት በኩል ከሰሞኑ የተወሰዱ እርምጃዎች በጥቅምት 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ የተፈረመውን ስምምነት ድንጋጌዎች “የጣሰ” እንደሆነ አስታውቋል።
የህብረቱ ልዑክ ለዚህ በማሳያነት የጠቀሰው ሌላኛው የህወሓት እርምጃ፤ በትግራይ ክልል ባለፉት ወራት ሲካሄድ የቆየው “የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላን” ነው። ካለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ ጀምሮ በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በውጊያ ሊሳተፉ የሚችሉ ወጣቶችን በግዳጅ የመልመል እና በአፈሳ ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ የማጋዝ እንቅስቃሴዎች ሲካሄዱ እንደነበር የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እና መገናኛ ብዙሃን ሲያስታውቁ ቆይተዋል።
በትግራይ “የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ ለማካሄድ ያስችላል” የተባለ አወዛጋቢ ህግ ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ በክልሉ ምክር ቤት መጽደቁም አይዘነጋም። የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላው በህወሓት በኩል “በተናጠል” እየተደረገ መሆኑን የአውሮፓ ህብረት ልዑክ በዛሬው መግለጫው ጠቅሷል።
የህብረቱ ልዑክ በትግራይ ክልል ላለው ወቅታዊ የፖለቲካ ችግር መፍትሔው በሁሉም ወገኖች መካከል የሚደረግ “ውይይት” እንደሆነ በመግለጫው አመልክቷል። እነዚሁ ወገኖች የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነትን በተጨባጭ ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ውይይቶችን “በአስቸኳይ” በድጋሚ እንዲጀምሩም ጥሪ አቅርቧል።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ የዛሬው መግለጫውን ያጠቃለለው፤ በቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ለሚደረገው “የማሸማገል ጥረቶች” ድጋፉን በመግለጽ ነው። የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ የሆኑት ኦባሳንጆ፤ ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ መቐለ ተጉዘው በትግራይ ክልል ያለው ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ከዶ/ር ደብረጽዮን ጋር ተነጋግረዋል።
ኦባሳንጆ እና የአፍሪካ ህብረት ለሚያደርጉት ጥረቶች ተመሳሳይ ድጋፏን የገለጸችው አሜሪካ፤ በትግራይ ክልል ያለውን ችግር ለመፍታት እየተካሄዱ ያሉ የሰላም ሂደቶችን “የሚያደናቅፉ” ላለቻቸው አካላት ማሳሰቢያ ሰጥታለች። ሀገሪቱ አዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲዋ በኩል በትላንትናው ዕለት ባወጣችው መግለጫ፤ እነዚህ አካላት በአፍሪካ ህብረት ለሚመራው የውይይት ጥረት “በአስቸኳይ ትብብር” እንዲያደርጉ አሳስባለች።
ኤምባሲው በዚሁ መግለጫው፤ በትግራይ ክልል ያሉ የፖለቲካ እና የሲቪል ማህበረሰብ መሪዎች “በፖለቲካዊ ውይይት” መሳተፍ እንደሚገባቸውም መልዕክት አስተላልፏል። እነዚሁ መሪዎቹ የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነትን “ሙሉ ለሙሉ” ተግባራዊ ማድረጋቸው “እጅግ አስፈላጊ” መሆኑንም አጽንኦት ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)






























