ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከፌደራል መንግስት ጋር የሚደራደር ከሆነ በአዲስ አበባ ከተማ ሳይሆን “በሌላ ሶስተኛ ሀገር” እንደሚሆን ለአሜሪካ ማሳወቁን የፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ተናገሩ። የአሜሪካ መንግስት “ቪዛ መከልከል ይቅር እና ሌላ ቢያደርግም”፤ “የትግራይ ህዝብ ህልውናን ለማረጋገጥ” ህወሓት “እስከ መጨረሻ እንደሚታገል” ኃላፊዋ ገልጸዋል።
“ሞንጆሪኖ” በሚለው የቅጽል ስማቸው ይበልጡኑ የሚታወቁት ፈትለወርቅ ይህንን የገለጹት፤ ትላንት ማክሰኞ ሰኔ 23፤ 2018 በመቐለ ከተማ በሚገኘው የህወሓት ጽህፈት ቤት ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ነው። በትላንቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል የፕሪቶሪያ ስምምነት ሁኔታ፣ የጦርነት ስጋት፣ የወጣቶች አፈሳ፣ የአሜሪካ ቪዛ እገዳ እንዲሁም ትግራይን በተመለከተ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ያወጧቸው መግለጫዎች ይገኙበታል።
ሁለቱ አካላት ባለፈው ሳምንት በየፊናቸው ባወጧቸው መግለጫዎች፤ የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት ተፈጻሚ መሆን እንዳለበት በአጽንኦት አሳስበዋል። በደቡብ አፍሪካዊቷ ፕሪቶሪያ ከተማ በጥቅምት 2015 ዓ.ም በህወሓት እና ፌደራል መንግስት ተወካዮች የተፈረመው የግጭት ማቆም ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች “በአፋጣኝ” ወደ ውይይት እንዲመለሱም ጥሪ አቅርበዋል።
የፕሪቶሪያ ስምምነት “መፍረሱን” በተደጋጋሚ በሚያወጣቸው መግለጫዎች ያሳወቀው ህወሓት፤ ለዚህም ዋነኛው ተጠያቂ የፌደራል መንግስት መሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል። የህወሓት ጽህፈት ቤት ኃላፊ በትላንቱ መግለጫቸው፤ የፕሪቶሪያ ስምምነትን “የፌደራል መንግስት እንደ መሳርያ ነው የተጠቀመበት” ሲሉ ተመሳሳይ አቋም አንጸባርቀዋል።
“የፕሪቶሪያ ውል እንዲፈጸም ህወሓት ጥረት አድርጓል። ውሉን የሚጥሱ በርካታ ነገሮች ቢሰሩም፤ ‘የፕሪቶርያ ስምምነት ፈርሷል’ ሳይል በትእግስት ቆይቷል። በዚህ ጉዳይ ህወሓት እንደ ፓርቲ ትልቅ ትልቅ መስዋእትነት ከፍሏል” ሲሉም ፈትለወርቅ ለፓርቲው ልሳናት እና ለክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋዜጠኞች ተናግረዋል።
እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ የአውሮፓ ህብረት ባለፈው ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ፤ ህወሓት ከሰሞኑ እየወሰዳቸው የሚገኙ እርምጃዎች “የፕሪቶሪያ ስምምነት ድንጋጌዎችን የሚጥስ ነው” ሲል ተችቷል። ሃያ ሰባት ሀገራትን በአባልነት ያቀፈው ህብረቱ ለዚህ በማሳያነት ከጠቀሳቸው ጉዳዮች አንዱ ህወሓት “ትይዩ የክልል ምክር ቤት” ማቋቋሙን ነው።
ፈትለወርቅ ለእዚህ ጉዳይ በሰጡት ምላሽ “የአውሮፖ ህብረት ‘ትይዩ ምክር ቤት አትመስርቱ’ ብለዋል። የትኛው ምክር ቤት ነው ትይዩ የሚሆነው? አልገባንም። የመረጃ ክፍተት ነው ወይስ ሌላ ግልጽ አልሆነልንም” ብለዋል። ህወሓት ባለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ፤ “ትግራይን የሚወክል ሌላ ምክር ቤት ኖሮ አያውቅም” በማለት የህብረቱን ትችት ውድቅ አድርጓል።
“በቅርቡ ስራውን በድጋሚ የጀመረው፤ አንድ የተመረጠ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ብቻ ነው ያለው። ምንም እንኳን ምክር ቤቱ ቀደም ብሎ የተመረጠ ቢሆንም፤ ስራውን በድጋሚ ከመጀመሩ በፊት በመላው ትግራይ በሚገኙ ከተሞች እና የገጠር ማህበረሰቦች ውስጥ ሰፊ ምክክሮች ተካሄደዋል” ሲልም ህወሓት በቅርቡ የወሰደውን እርምጃ በመግለጫው ተከላክሏል።
የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በጳጉሜ 2012 ዓ.ም. በተደረገ አወዛጋቢ ምርጫ የተመረጠውን የትግራይ ክልል ምክር ቤት “ወደ ስራ እንዲመለስ” የወሰነው ባለፈው ሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ ነበር። ምክር ቤቱ የተመረጠበትን ምርጫ፤ የፌደራል መንግስት “እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸናና እና ተፈጻሚነት የሌለው ነው” ሲል በወቅቱ ውድቅ ማድረጉ አይዘነጋም።
ከክልል ምክር ቤት ማቋቋም በተጨማሪ “የፕሪቶሪያ ስምምነት ድንጋጌዎች ይጥሳል” በሚል የአውሮፓ ህብረት ያነሳው ጉዳይ ህወሓት “የተናጠል የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላን” ተግባራዊ ማድረጉን ነው። የህወሓት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ይህንን የህብረቱን ትችት ቢያስተባብሉም፤ ወደፊት ሊመጣ ለሚችል ጦርነት “መዘጋጀት” እንደሚያስፈልግ ግን ተናግረዋል።
“ጠላት ጦርነት የማካሄድ ፍላጎት ይዞ ሙሉ አቅሙን አሰልፎ መምጣት ከጀመረ፤ ትግራይ መዘጋጀት አለባት። ‘ሊመጣብን የሚችልን ወረራ ለመከላከል መዘጋጀት አለብን’ የሚል ውይይት ስንጀምር አፈሳ ጀመሩ ብለው ዘመቻ ከፈቱ። አፈሳ ብንፈልግ በየቀኑ በርካታ ወጣቶች አውቶብስ ተሳፍረው እየሄዱ ነው። ካልፈለገ ምንም ማድረግ አትችልም። አምኖ ነው መታገል ያለበት” ሲሉ ፈትለወርቅ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።
ባለፉት ሳምንታት በወጡ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሪፖርቶች እና የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች የተካተቱ የዓይን እማኞች ምስክርነቶች ግን እርሳቸው የሚሉትን የሚቃረን ነው። የዓይን እማኞቹ ካለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ ጀምሮ በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በውጊያ ሊሳተፉ የሚችሉ ወጣቶችን በግዳጅ የመመልመል እና በአፈሳ ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ የማጋዝ እንቅስቃሴዎች ሲካሄዱ እንደነበር አጋልጠዋል።
ፈትለወርቅ በትላንቱ መግለጫቸው፤ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ “ወደ ጦርነት አትግቡ፣ ሰላም አታደናቅፉ” ማለታቸውን በመጥቀስ የፓርቲያቸውን ምላሽ አሳውቀዋል። “አውሮፖ ህብረትም ይሁን አሜሪካ፤ ያጠፋውን ትተው፣ ወንጀል እየፈጸመ ያለውን ትተው፣ እየተበደለ ያለውን ነው ለመቅጣት እየሞከሩ ያሉት። ይህ ትክክል አይደለም ብለን ገልጸንላቸዋል” ሲሉ በህወሓት በኩል የተሰጠውን ምላሽ አብራርተዋል።
“የብልጽግና ስርዓት ለረዥም ጊዜ ለጦርነት ሲዘጋጅ ቆይቷል” ያሉት የህወሓት ጽህፈት ቤት ኃላፊ፤ ይህንኑ ያሳያሉ ያሏቸውን መረጃዎች ለጋዜጠኞቹ አጋርተዋል። “በአሁኑ ሰዓት ከምዕራብ ትግራይ ጀምሮ እስከ ምስራቅ ትግራይ ያለው በሙሉ፤ አለ የሚባል ጦሩን ሁሉ አከማችቶ ነው ያለው። ሙሉ ዕዞቹን አሰልፎ ነው ያለው። እግረኛ ተዋጊ ብቻ ሳይሆን ሜካናይዝድ ኃይል ጭምር በምስራቅ እና ምዕራብ በኩል አሰልፎ ይገኛል” ሲሉ ፈትለወርቅ ወንጅለዋል።
የመከላከያ ሰራዊት ጄነራሎችም “የጦርነት ዝግጅታቸውን” በተለያየ መንገድ እንደሚገልጹ እና በትግራይ ክልል “የማያቋርጥ የድሮን ቅኝት እየተካሄደ መሆኑን” የህወሓት ጽህፈት ቤት ኃላፊ በተጨማሪ ማሳያነት ጠቅሰዋል። “ይህ ሆኖም እኛ ታግሰን ነው ያለነው” ያሉት ፈትለወርቅ፤ “በቀጠናው ሰላም እንዲሰፍን ፍላጎት ያላቸው” እንደ አሜሪካ ያሉ ወገኖች “ማስፈራራት ሳይሆን” ከህወሓት ጋር “አብሮ መስራት” እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

የህወሓት ጽህፈት ቤት ኃላፊ “ማስፈራራት” ያሉትን ጉዳይ በግልጽ ባያብራሩም፤ አሜሪካ በህወሓት አመራሮች ላይ በቅርቡ የወሰደችውን የቪዛ እገዳ ግን በትላንቱ መግለጫቸው አንስተዋል። አሜሪካ “አክራሪ” ባለቻቸው የህወሓት አባላት እና የቅርብ ቤተሰቦቻቸው ላይ የቪዛ ገደብ መጣሏን ያሳወቀችው የዛሬ ሁለት ሳምንት ገደማ ነው።
“የአሜሪካ ቪዛ ክልከላ ትርጉሙ ፖለቲካዊ ነው…እንኳን ወደ አሜሪካ ወደ አዲስ አበባ መሄድ እንደማንፈልግ ያውቃሉ። እናነጋግራችሁ ብለውንም እኛ ወደ አዲስ አበባ አንሄድም ብለናቸዋል። መነጋገር መደራደር ካለብንም በሌላ ሶስተኛ ሀገር ሄደን ነው የምንደራደረው እንጂ ወደ አዲስ አበባ እንሄድም ብለናቸዋል። አይደለም ቪዛ ይዘን ወደ አሜሪካ ልንሄድ ወደ አዲስ አበባም እንደማንሄድ ያውቃሉ” ሲሉ ፈትለወርቅ ተናግረዋል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በዚሁ መግለጫው የተጠቀመበት “አክራሪ (hardliner)” የሚለው አገላለጽ የህወሓት አመራርን “ለመከፋፈል የተደረገ ነው” የሚል እምነት ያላቸው ፈትለወርቅ፤ “መለያየት ቢፈልጉም አይሆንላቸውም” ሲሉ ተደምጠዋል። “በህወሓት ውስጥ የተለያየ አመራር የለንም። እንደ ህወሓት የምንታወቅበት ነገር አለ። የመርህ ሰዎች ነን። ህወሓት በመርህ ይቆማል። ወደ ነፈሰው አይነፍስም” ሲሉም ፓርቲያቸውን ተከላክለዋል።
“እኛ ‘በሉአላዊነታችን አንደራደርም’ ብለናል። አሁንም አንደራደርም። ቪዛ መከልከል ይቅር እና ሌላ ቢያደርጉም በሉአላዊነታችን አንደራደርም። በትግራይ ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎቶች ላይ አንደራደርም። የትግራይ ህዝብ ህልውና ለማረጋገጥ በሚደረግ ጸረ-ጄኖሳይድ ትግል አንደራደርም። እስከ መጨረሻ እንታገላለን”
“እኛ ‘በሉአላዊነታችን አንደራደርም’ ብለናል። አሁንም አንደራደርም። ቪዛ መከልከል ይቅር እና ሌላ ቢያደርጉም በሉአላዊነታችን አንደራደርም። በትግራይ ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎቶች ላይ አንደራደርም። የትግራይ ህዝብ ህልውና ለማረጋገጥ በሚደረግ ጸረ-ጄኖሳይድ ትግል አንደራደርም። እስከ መጨረሻ እንታገላለን” ሲሉም ፈትለወርቅ የፓርቲያቸውን አቋም አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































