በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ ከተማ የጸጥታ ኃይሎች “የወጣቶች አፈሳ” ማካሄድ መጀመራቸውን የዓይን እማኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። በመቐለ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ምድቦቻቸው እንዲመለሱ ጥሪ ሲደረግ የነበረ ቢሆንም፤ ዛሬ የታዩ እንቅስቃሴዎች በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ሲካሄድ የቆየው አፈሳ ወደ ክልሉ ዋና ከተማ በይፋ መድረሱን እንደሚጠቁም ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ የመረጃ ምንጮች አስረድተዋል።
በከተማው የታፈሱ ወጣቶች በህዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች ተጭነው ሲወሰዱ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች፤ በዛሬው ዕለት በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት ሲጋሩ ውለዋል። ከእነዚህ ተንቀሳቃሽ ምስሎች አንዱ በመቐለ ሰሜን ክፍለ ከተማ 05/06 ቀበሌ ከሚገኘው ዒላላ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደጃፍ የተቀረጸ ነው።
ይኸው ቪዲዮ ከትምህርት ቤቱ ደጃፍ የቆመ ነጭ እና አረንጓዴ ቀለም ያለው የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ እንዲሁም የጦር መሣሪያ ያነገቡ ሰዎች እና የተወሰኑ ወጣቶች ወጣ ገባ ሲሉ ያሳያል። ከአውቶቡሱ ጀርባ ተሰብስበው ሲመለከቱ የነበሩ ሰዎች ጩኸት እና ለቅሶም በተንቀሳቃሽ ምስሉ ይደመጣል።

ይህንን ጨምሮ በትምህርት ቤቱ አካባቢ ያለውን ሁኔታ የሚያሳዩት ተንቀሳቃሽ ምስሎች የተቀረጹት ዛሬ አርብ ሰኔ 26፤ 2018 ጠዋት እንደሆነ በቦታው የነበሩ አንድ የዓይን እማኝ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። በመቐለ ከተማ 05 በሚባለው ቀበሌ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት የዓይን እማኝ፤ ዛሬ ጠዋት አንድ ሰዓት አካባቢ ከቤታቸው የወጡት “ልጄ ልጄ” የሚል የጩኸት ድምጽ ሰምተው እንደነበር ተናግረዋል።
“ጠዋት አንድ ሰዓት ላይ ጩኸት ሰማን። እንዳለ ከቤት ሮጠን ወጣን። የህዝብ ባስ ሞልተው ሲሄዱ ነው ያየናቸው” የሚሉት እኚሁ የመቐለ ነዋሪ፤ የአካባቢው ህዝብ “እንዳለ ውጪ ቆመ ሲጠባበቅ” እንደነበር አስረድተዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች ሁለት ሰዓት መጠበቃቸውን የገለጹት የዓይን እማኝ፤ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ከመጣ በኋላ ወጣቶቹን “ጭነዋቸው ሲሄዱ” ቆመው መመልከታቸውን ገልጸዋል።
ወጣቶቹ በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ እንደሆነ የሚገምቱት የመቐለዋ ነዋሪ፤ ወደ መኪናው ከሚጭኑት ሰዎች መካከል የፖሊስ ዩኒፎርም የለበሱ ሰዎች እንደነበሩት የዓይን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። ወጣቶቹ “ሲታፈሱ” እንዳላዩ የገለጹት የዓይን እማኟ፤ ሆኖም የአካባቢው ነዋሪዎች የታፈሱት በሌሊት በተደረገ “የፓትሮል ቅኝት” እንደሆነ አክለዋል።
አውቶቡሱ ወጣቶቹን ይዞ መንቀሳቀስ ሲጀምር የአካባቢው ሰዎች ድንጋይ ጭምር ወርውረው ለማስቆም መሞከራቸውንና የፊቱን መስታወት እንደሰበሩ ማየታቸውን ነዋሪዋ ገልጸዋል። ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ሌላ የመረጃ ምንጭ አውቶቡሱ ወደ ዒላላ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያቀናው ወጣቶችን ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ለማጓጓዝ እንደሆነ አስረድተዋል።
ወጣቶቹ “ከተለያዩ የመቐለ አካባቢዎች የታፈሱ” እንደሆኑ እኚሁ በመቐለ የሚገኙ የመረጃ ምንጭ አስረድተዋል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገራት ሌላ የመቐለ ነዋሪ፤ የ18 ዓመት ወንድሟ ባለፈው ሰኞ “ሃይማኖታዊ ትምህርት ከሚከታተልበት መስጊድ ታፍሶ” ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ እንደተወሰደ ገልጻለች።
ወንድሟ በወታደሮች ሲወሰድ የመስጊዱ ዘበኛ እንደ ደወለላት የገለጸችው ነዋሪዋ፤ እርሱን ፍለጋ በአቅራቢያው ወደሚገኝ የፖሊስ ጣቢያ ብትሄድም ወደ ሌላ ቦታ እንደተወሰደ እንደተነገራት አስረድታለች። በማግስቱ ወንድሟ በዚያው ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ እንዳለ ብታረጋግጥም፣ መጀመሪያ “የለም” የሚል ምላሽ እንደተሰጣት እና ከቆይታ በኋላ ደግሞ መኖሩ እንደተነገራት አክላለች።

ወንድሟ በተያዘበት ጊዜ የለበሰው ጀለቢያ ስለነበር፤ የክረምቱን ብርድ የሚቋቋምበት “ልብስ እና ሱሪ” እንዲያመጡ እንደታዘዙ ነዋሪዋ ተናግራለች። በጣቢያው የሚገኙት ፖሊሶች ወንድሟ የተያዘው “መታወቂያ ስላልያየዘ” መሆኑን እንደነገሯት እና “የሰፈር ልጅ ስለሆነ ችግር የለም። ጠዋት ይመለሳል” በማለት እንዳረጋጓት ገልጻለች።
ከማክሰኞ ጀምሮ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ብትመላለስም ወንድሟን ማግኘት ያልቻለችው ነዋሪዋ፤ በስተኋላ ላይ ወደ ወታደር ማሰልጠኛ ጣቢያ መወሰዱን እንደሰማች አስረድታለች። ወንድሟ ያለበትን ቦታ የነገሯት እርሱ ከተወሰደበት የወታደር ማሰልጠኛ ታመው ወደ መቐለ የመጡ ወጣቶች እንደሆነም አመልክታለች።
ይህንን ተከትሎ ከመቐለ ከተማ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ደንገላት የተባለ ቦታ ትላንት ሐሙስ ያቀናችው ነዋሪዋ፤ በስፍራው ከደረሰች በኋላ ከርቀት ወንድሟን ማየቷን ተናግራለች። ወንድሟ ጸጉሩን መላጨቱን እንደተመለከተች የጠቀሰችው የመቐለ ነዋሪዋ፤ ሆኖም ልታነጋግረው አለመቻሏን ገልጻለች።

የማሰልጠኛው ጠባቂዎች በዚያ የሚገኙ ሌሎች ወጣቶች “ጠያቂ የለንም ብለው ያስባሉ” በሚል ምክንያት ወንድሟን ቀርባ እንዳታወራ እንደከለከሏትም አክላለች። ወታደራዊ ማሰልጠኛው ወጣ ባለ አካባቢ ላይ እንደሚገኝ የጠቆመችው የመቐለዋ ነዋሪ፤ ከወንድሟ ጋር በርካታ ወጣቶችን በስፍራው ላይ መመልከቷን ተናግራለች።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው አራተኛ የመቐለ ነዋሪ፤ በወጣቶቹ ላይ የተካሄደውን አፈሳ በመፍራት ባለቤታቸውን መደበቃቸውን ገልጸዋል። በ2013ቱ ጦርነት የተሳተፉ ባለቤታቸው ተፈልገው ባለመገኘታቸው፤ ከአንድ ሳምንት በፊት በቀበሌ አስተዳደር ተጠርተው የት እንዳሉ መጠየቃቸውን አስረድተዋል።
ባለቤታቸው ወደ አዲስ አበባ መሄዳቸውን የተናገሩት የመቐለ ነዋሪ፤ የቀበሌው አስተዳደር ኃላፊዎች ካሉበት እንዲያመጧቸው ትዕዛዝ እንደሰጧቸው ተናግረዋል። የቀበሌው ኃላፊዎች ባለቤታቸው ቀድሞ ወደነበረበት ወታደራዊ አሃድ መመለስ እና የወታደራዊ ስልጠና መውሰድ እንዳለበት እንደነገሯቸውም ጠቅሰዋል። ኃላፊዎቹ “ዓይናችንን አናነሳም። እንከታተላቸዋለን” በማለት እንዳስፈራሯቸውም አክለዋል።
እኚሁ የመቐለ ነዋሪ ከሰሞኑ ብቻ የእርሳቸው ጎረቤት የሆኑ ሁለት ወጣቶች መታፈሳቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አሁን ያለው ሁኔታ በሰዎች መካከል የነበረውን መተማመን እንደሸረሸረ የገለጹት የመቐለ ነዋሪ “የሚወስድሽ ጎረቤትሽ፤ የሚያሳፍስሽ ዘመድሽ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
በትግራይ ክልል ለወታደራዊ ግዳጅ የሚፈለጉ ወጣቶች አፈሳ መካሄድ የጀመረው ካለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ ጀምሮ እንደሆነ ሀገር በቀል እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ባወጧቸው ሪፖርቶች አረጋግጠዋል። የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ ከሚደረግባቸው የትግራይ ክልል አካባቢዎች መካከል አዲግራት፣ አዲጉደም እና ዛላንበሳ ከተሞች እንደሚገኙበት “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ባለፈው ወር ያነጋገረቻቸው ከአፈሳ ያመለጡ ወጣቶች ገልጸው ነበር።
በክልሉ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እየተካሄደ መሆኑን ሂውማን ራይትስ ዎች እና የአውሮፓ ህብረት ባለፉት ሳምንት ባወጧቸው መግለጫዎች ተችተዋል። ለትችቶቹ ምላሽ የሰጠው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና የፓርቲው ሹማምንት ግን “ወረራ ለመከላከል መዘጋጀት አለብን አልን እንጂ አፈሳ አላካሄድንም” ሲሉ አስተባብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































