በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ “ሁሉም የዲጂታል ሚዲያዎች” ወደ ምዝገባ ስርዓት እንዲገቡ ለማስቻል፤ በስራ ላይ ያለውን የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ እስከ ማሻሻል የሚደርስ “የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን” እያከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን አስታወቀ። መስሪያ ቤቱ “በበየነ መረብ የሚያጋጥሙ” ባላቸው “የስነምግባር እና የህግ ጥሰቶች” ላይ “አስተዳደራዊ እርምጃ” እንደሚወስድም አስጠንቅቋል።
ባለስልጣኑ ይህን ያስታወቀው ትላንት ቅዳሜ ሐምሌ 4፤ 2018 ምሽት ባወጣው መግለጫ ነው። መስሪያ ቤቱ በዚሁ መግለጫው፤ እንደ ፌስቡክ፣ ቲክቶክ፣ ዩቲዩብና የመሳሰሉት አውታሮችን በመጠቀም በኢትዮጵያ “የሚዲያ አገልግሎት የሚሰጡ” “አብዛኞቹ” ድርጅቶች እና ግለሰቦች፣ ከባለስልጣኑ የምዝገባ ምስክር ወረቀት ሳያገኙ “በመስራት ላይ” እንደሚገኙ አስታውቋል።
ይህ የሆነበት ምክንያት አሁን በስራ ላይ ያለው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ፤ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን የምዝገባ ስርዓትን “በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን” በማድረጉ እንደሆነ ባለስልጣኑ ጠቅሷል። በ2013 ዓ.ም የወጣው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ፤ በግል ወይም በድርጅት የበይነ-መረብ መገናኛ ብዙሃን ለማቋቋም የሚፈልግ የኢትዮጵያ ዜግነት ያለው ሰው “ባለስልጣኑ እንዲመዝግበው ማመልከት እንደሚችል” ተደንግጓል።

አመልካቾች በአዋጁ ላይ የተዘረዘሩ መስፈርቶችን አሟልተው ለባለስልጣኑ ካቀረቡ፤ መስሪያ ቤቱ ምዝገባውን አከናውኖ በ30 ቀናት ውስጥ የምስክር ወረቀት መስጠት እንዳለበት በአዋጁ ላይ ሰፍሯል። መስፈርቱን አሟልቶ ያስገባ አመልካች በ30 ቀናት ውስጥ ምላሽ ካላገኘ፤ የእውቅና የምስክር ወረቀት እስከሚሰጠው “መጠበቅ ሳያስፈልገው” ወደ ስራ መግባት እንደሚችልም በአዋጁ ተቀምጧል።
አዋጁ ለበየነ መረብ መገናኛ ብዙሃን “ምዝገባን በግዴታነት የሚያስቀምጥ አለመሆኑ”፤ በተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱ ዘንድ “በህግ ክፍተትነት” ተወስዷል። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በትላንቱ መግለጫው ያንጸባረቀውን ይህን አቋም፤ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በአዲስ አበባው ሂልተን ሆቴል በተካሄደ የውይይት እና የስልጠና መርሃ ግብር ላይም አንስቶት ነበር።
ለበይነ-መረብ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በተዘጋጀው በዚህ መርሃ ግብር ላይ ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ፤ በአዋጁ የተቀመጠው “በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ” የምዝገባ አካሄድ እንዲቀየር አዋጅ “ማሻሻያ” እንደሚያስፈልግ ተናግረው ነበር። “ሁሉም ሚዲያ ወደ ምዝገባ ስርዓት ይመጣል … ይሄም የአዋጅ ማሻሻያ ግድ ይለናል” ሲሉ ዋና ዳይሬክተሯ በመርሃ ግብሩ ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የአዋጁን ማሻሻያ “እየሰራንበት ነው” ያሉት ሃይማኖት፤ ይህንን በተመለከተን በባለስልጣኑ ቦርድ “greenlight” እንዳለም አመልክተዋል። የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ስራዎች “የመቆጣጠር” እና “የመገምገም” ኃላፊነት ያለበት፤ ይህ ቦርድ ዘጠኝ አባላት ያሉት ነው። ቦርዱን በዋና ሰብሳቢነት የሚመሩት የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎትን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሬድዋን ሁሴን ናቸው።
ከስራ አመራር ቦርዱ በተጨማሪ የተወካዮች ምክር ቤትም አዋጁን ለማሻሻል በሚደረጉ ስራዎች ላይ “ለመተባበር ፈቃደኛ መሆናቸውን” መግለጻቸውን ሃይማኖት በባለፈው ሳምንቱ መርሃ ግብር ላይ ጠቁመዋል። በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በኩል በአዋጅ ማሻሻያዎች ላይ መካተት የሚገባቸውን “አንዳንድ መስፈርቶች” አሟልቶ ማቅረብ እንደሚጠበቅ ዋና ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል።
የትላንቱ መግለጫም ይህንኑ የዋና ዳይሬክተሯን ማብራሪያ አስተጋብቷል። “ባለስልጣኑ ያልተመዘገቡ የዲጂታል ሚዲያዎች ወደ ክትትልና ድጋፍና እንዲሁም ሃላፊነትና ተጠያቂነት የሚገቡበትን የአሰራር ስርአት እያጎለበተ ይገኛል” ያለው መግለጫው፤ መስሪያ ቤቱ “አዋጅ እስከ ማሻሻል የሚደርስ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን” እያከናወነ እንደሆነ አመልክቷል። በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ የተወሰኑ አንቀጾች ላይ ባለፈው ሚያዝያ ወር ማሻሻያ መደረጉ አይዘነጋም።

የትላንቱ መግለጫ ከበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን የምዝገባ ስርዓት በተጨማሪ በይዘቶቻቸው ላይ የሚደረገውን ክትትል እና ቁጥጥር ጉዳይንም አንስቷል። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዋጅ በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት፤ መገናኛ ብዙኃን የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች “የአገሪቱን ህግ፣ የመገናኛ ብዙሃን አዋጁን እና የጋዜጠኝነት ሙያና ስነምግባርን አክብረው እየሰሩ ስለመሆናቸው ክትትል” እንደሚያደርግ በመግለጫው ጠቅሷል።
የህግ እና የስነምግባር ጥሰት በሚፈጽሙ የሚዲያ ተቋማት ላይ “አስተዳደራዊ ውሳኔዎች” እየወሰደ እንደሆነ የገለጸው ባለስልጣኑ፤ “በበይነ መረብ በሚያጋጥሙ” ተመሳሳይ ጥሰቶች ላይም ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል። መስሪያ ቤቱ “የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ እንዲሁም የህዝብና የሀገር ደህንነትን የሚጎዱ ዘገባዎችን” የሚያሰራጩ ባላቸው አካላት ላይም “ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ” ጉዳያቸውን “ለህግ አስፈጻሚ አካል የማቅረብ ስራ እንደሚሰራም” አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ባለፈው ጥር እና የካቲት ወር በወሰዳቸው እርምጃዎች፤ “ዋዜማ ሬድዮ” እና “አዲስ ስታንዳርድ” የበየነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ማገዱ ይታወሳል። ባለስልጣኑ ለ“ዋዜማ ሬድዮ” የሰጠውን የስራ የምዝገባ የምስክር ወረቀት እንዲመልስ ያደረገው፤ ተቋሙ የሚያሰራጨው ዘገባዎች የኢትዮጵያን “ብሔራዊ ጥቅም የሚጻረሩ”፣ “ሚዛናዊነት የሚጎድላቸው”፣ “የሙያ ስነምግባርን የጣሱ” እና “የአንድ ወገን ዘገባ ብቻ የተንጸባረቁባቸው ሆነው ተገኝተዋል” በሚል ውንጀላ ነበር።
“የሚዲያ ስነ-ምግባርን፣ የኢትዮጵያን ህጎች እና የሀገርንና የህዝብን ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ዘገባዎችን በተደጋጋሚ በማሰራጨት ላይ ይገኛል” የሚል ክስ የቀረበበት የ“አዲስ ስታንዳርድ” የበይነ መረብ መገናኛ ምዝገባ፤ በተመሳሳይ መልኩ ባለፈው የካቲት ወር አጋማሽ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ተሰርዟል። የ“አዲስ ስታንዳርድ” ምዝገባ መሰረዝ የተቃወመው የመገናኛ ብዙሃኑ አሳታሚ ጃኬን ፐብሊሺንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፤ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶ ሂደቱን በመከታተል ላይ ይገኛል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































