በአዲስ አበባ ከተማ፣ ፒያሳ አካባቢ የሚገኙ እና ዕድሜያቸው ከ70 እስከ 100 ዓመት የሚጠጉ በቅርስነት የተመዘገቡ ህንጻዎች ፈረሱ። የፌደራል የቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለስልጣን በበኩሉ “ሲኒማ አምፒርን” ጨምሮ የፈረሱት ህንጻዎች “የቅርስ መመዘኛ መስፈርቶችን የሚያሟሉ አይደሉም” ብሏል።
በመዲናይቱ አራዳ ክፍለ ከተማ ከፈረሱ ህንጻዎች መካከል ሸዋ ሆቴል፣ በስተኋላ ላይ ወደ ሄርሞን ሆቴል የተለወጠው የአጼ ኃይለ ሥላሴ በጎ አድራጎት ድርጅት ህንጻ እንዲሁም ቢያድግልኝ ሆቴል ይገኙበታል። ትላንት ሰኞ ሰኔ 29፤ 2018 ዓ.ም. ረፋድ ላይ በቦታው የተገኘችው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ህንጻዎቹ ሙሉ ለሙሉ ፈርሰው ዙሪያቸው በአረንጓዴ ቆርቆሮ መታጠር መጀመሩን ተመልክታለች።
ከእነዚህ በተጨማሪ የወርቅ፣ የልብስ እና የህንጻ መሳሪያዎች መሸጫ ሱቆችም መፍረሳቸውን ታዝባለች። ህንጻዎቹ የፈረሱት ከሁለት ቀናት በፊት ቅዳሜ ሰኔ 27፤ 2018 እንደሆነ የዓይን እማኞች እና በአካባቢው ሱቆች የነበራቸው ባለቤቶች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ከፈረሱት የወርቅ ቤቶች በአንዱ የሚሰሩ ግለሰብ፤ እርሳቸው የሚሰሩበት መሸጫ ሱቅ የሚገኝበት “ሸዋ ሆቴል” በመባል የሚታወቀው ህንጻ እንደሚፈርስ ከአንድ ወር በፊት ተነግሯቸው እንደነበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። እኚሁ ግለሰብ ከወራት በፊት የኪራይ ውል ለማደስ ወደ ፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በሄዱበት ወቅት፤ ህንጻው የሚፈርስ በመሆኑ እስከዚያው ድረስ የወር ኪራይ እንዲከፍሉ እንደተነገራቸውም ጨምረው አስረድተዋል።
ዕድሜ ጠገቡ “ሸዋ ሆቴል” እንዲፈርስ የተወሰነው፤ በአጠገቡ ለተገነባው ዘመናዊ ህንጻ ማስፋፊያ እንዲውል መሆኑን እንደተነገራቸውም አመልክተዋል። እርሳቸው የጠቀሱት ህንጻ፤ ከአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ፊት ለፊት ተገንብቶ በመጠናቀቅ ላይ ያለውን “አራዳ ሌግዠሪ ሞልን” ነው።
በሁለት ሄክታር ሜትር ስፋት ላይ የተንጣለለው የገበያ ማዕከሉ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አቶ ማናዬ ሰንደቁ ከተባሉ ባለሃብት ጋር በአጋርነት የሚያስገነባው እንደሆነ ከአንድ ዓመት በፊት ተገልጾ ነበር። ግንባታው በከተማይቱ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጭምር በየጊዜው ክትትል ሲደረግበት የቆየው የገበያ ማዕከሉ፤ ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው ዕቃዎች የሚሸጡበት እንደሆነ ተነግሯል።

በገበያ ማዕከሉ አቅራቢያ ያሉ ህንጻዎች እና ሱቆች ላይ ከትላንት በስቲያ የተወሰደው የማፍረስ እርምጃ፤ “ድንገተኛ እንደሆነባቸው” በወርቅ መሸጫ ሱቁ የሚሰሩት ግለሰብ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በአካባቢው የሚሰሩ ሌላ ግለሰብ፤ ባለፈው ቅዳሜ በሸዋ ሆቴል ውስጥ በመዝናናት ላይ የነበሩ ሰዎች እንዲወጡ ተደርጎ ህንጻው መፍረሱን ሰምቼያለሁ ብለዋል።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው በዚያው አካባቢ ያሉ ሌላ ግለሰብ በበኩላቸው፤ የህንጻዎቹን መፍረስ በተመለከተ የአካባቢው ነጋዴዎች ቀደም ብሎ መረጃው ደርሷቸውእንደነበር ከራሳቸው አንደበት መስማታቸውንም ተናግረዋል። ከሁለት ሳምንት በፊት በስፍራው የሚገኝ አንድ የጫማ መደብር ሰራተኞች ዕቃዎቻቸውን ሲያጓጉዙ መመልከታቸውን ጠቁመዋል።
ባለፈው ቅዳሜ በስፍራው እንደነበር የገለጸ ሌላ የዓይን እማኝ፤ በዕለቱ ሲኒማ አምፒርን ጨምሮ በአካባቢው ያሉ መደብሮች ዕቃ ሲያወጡ በተመሳሳይ መመልከቱን ማረጋገጫ ሰጥቷል። በትላንትናው ዕለት ወደ ቦታው ሲመለስ በአካባቢው የነበሩ ህንጻዎች ፈርሰው ማየቱንም የዓይን እማኙ አክሏል።

በሳምንቱ መጨረሻ በህንጻዎቹ ላይ የተካሄደው የማፍረስ እርምጃ፤ ከሁለት ዓመት በፊት በፒያሳ እና በአራት ኪሎ አካባቢዎች በርካታ የንግድ ሱቆች እና የመኖሪያ ቤቶች እንዲፈርሱ ካደረገው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ ነው። በወቅቱ በአካባቢው “በቅርስነት ተመዘግበው” የነበሩ ህንጻዎች መፍረሳቸው፤ ከስነ ህንጻ ባለሙያዎች እና ከቅርስ ተቆርቋሪዎች ከፍተኛ ትችት አስከትሎ ነበር።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በወቅቱ በሰጡት መግለጫ፤ በአካባቢው ላይ ያሉ ቅርሶች “በጥናት መለየታቸውን” ገልጸው ነበር። “ቅርስ ህግ አለው። እንደ ፌደራል የቅርስ ባለስልጣን አለ። የከተማችን ባህል እና ቱሪዝም ቅርስን ይንከባከባል፤ ቅርስን ይጠብቃል። እነኚህን አካተናል” ሲሉ ከንቲባዋ በወቅቱ ተናግረዋል።
“እነ ሲኒማ ኢትዮጵያን፣ እነ ሀገር ፍቅርን፣ ሲቲ ኮንቬንሽንን፣ የእነ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴን ቤት፣ የቀድሞ ማዘጋጃ [ቤትን] እነኚህን እና የመሳሰሉትን ባሉበት ነው የምናድሰው። እዚህ አካባቢ ሲኒማ ሲያይ የነበረው፣ በጎልማሳነትም ሆነ በእርጅና ዕድሜ ውስጥ ያለው፣ የዛሬው ወጣትም ይገናኝበታል። ይሄንን በምንም አይነት ማህበረሰባችንን አናሳጣም። የበለጠ ሳቢ፣ ዘመኑን የሚመጥን አድርገን፣ አድሰን በቅርብ ቀን ለአገልግሎት ክፍት የምናደርጋቸው ነው የሚሆኑት” ሲሉም አዳነች በዚሁ መግለጫቸው ተናግረዋል።

አዳነች እንዳሉትም በፒያሳ የሚገኙት ሲኒማ ኢትዮጵያ እና ሲኒማ አምፒር፤ የከተማው አስተዳደር ተግባራዊ ባደረገው የህንጻ ገጽታ ታድሰው አገልግሎት መስጠት ቀጥለው ነበር። ሆኖም ከከንቲባዋ መግለጫ አንድ ዓመት ከሶስት ወራት በኋላ በ1920 ዓ.ም የተገነባው እና ሲኒማ አምፒር ያለበት ህንጻ እንዲፈርስ ተደርጓል።
ሲኒማ አምፒር የሚገኝበት እና “ስቴሪዮ ክለብ” በሚል ስም የሚታወቀው ህንጻ፤ የአዲስ አበባ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ “የቅርስ ቤት” በሚል ከመዘገባቸው መካከል ይገኝበታል። የቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው በበኩላቸው መስሪያ ቤታቸው ለፈረሱት ህንጻዎች “የቅርስ ቤት” የሚል ዕውቅና አለመስጠቱን እና ህንጻዎቹም የቅርስነት መስፈርት የማያሟሉ እንደሆኑ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስተባብለዋል።
ባለስልጣኑ አንድን ቅርስ ለመመዝገብ ምዝገባ የሚያከናውነው፤ በ2015 ዓ.ም. በወጣ መመሪያ መመዘኛ መስፈርት መሰረት መሆኑን አቶ አበባው ተናግረዋል። ህንጻዎችን በቅርስነት ለመመዘን ከሚታዩት መስፈርቶች መካከል 30 በመቶው በአርክቴክቸር ላይ የሚመሰረት ሲሆን ታሪካዊነቱ ደግሞ 30 በመቶውን እንደሚይዝ ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።
ህንጻው ከመጀመሪያው ጀምሮ የነበረው “መሠረታዊ ይዘቱ” (authenticity) ተጠብቋል ወይስ “በሂደት ተሻሽሎ (ሞዲፋይ ተደርጎ) ቅርጹን አጥቷል?” የሚለውም በዝርዝር እንደሚታይ አቶ አበባው አስረድተዋል። በመመዘኛው መሰረት 49 ከመቶ እና ከዚያ በታች ውጤት ያገኘ ህንጻ ቅርስ ሊባል እንደማይችል ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።
በዚህ መሰረት “ሸዋ ሆቴልም” ሆነ “ሲኒማ አምፒር” የቅርስ መመዘኛ መስፈርቱን እንደማያሟሉ ወይም qualify እንደማያደርጉ አቶ አበባው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አንድ ቤት ወይም ህንጻ “መስፈርቱን ያሟላል ወይስ አያሟላም” የሚለውን ባለሙያ በጥናት እንደሚገመግም የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ባለስልጣኑ የቅርስ ህንጻ በመሆናቸው የማይነኩ ቤቶችን ዝርዝር ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደሰጠም አክለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ “የቅርስ ቤት ነው” በማለት የሚሰጠው ዕውቅና፤ በምን መስፈርት “ተመዝኖ እንደሚሰጥ አናውቅም” ብለዋል አቶ አበባው። ከተቀመጠው መመሪያ እና ከባለስልጣኑ “ዕውቅና ውጭ” የሚሰጥ ስያሜን በተመለከተም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማሳወቃቸውንም አስረድተዋል።
“የቅርስ ቤት ነው ተብሎ ሲሰጥ ስታንዳርድ አለው። እሱን እንኳ አይጠብቁም” ያሉት አቶ አበባው፤ “አንዱ ትልቅ አድርጎ ሲሰራው ሌላው ደግሞ ትንሽ አድርጎ ይሰራዋል። ይህም ማለት ዝም ብለው reproduce እያደረጉት ነው” ሲሉ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተሩ ተችተዋል።
በ1956 በወጣው የቅርስ አዋጅ የተጠቀሰው “ዕድሜው 100 ዓመት የሞላው ሁሉ ቅርስ ነው” የሚለው ድንጋጌ በኋላ ላይ በወጡት አዋጆች መሻሩን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አንድን ነገር ዕድሜ ብቻውን ቅርስ እንደማያስብለው አስረድተዋል። በቅርስ መመዘኛ መስፈርት ዕድሜ አንዱ element እንደሆነ የሚገልጹት አቶ አበባው፤ በመስፈርቱ ያለው ድርሻ አምስት በመቶ ብቻ መሆኑንም አክለዋል።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የሚፈልጉ የስነ ህንጻ ባለሙያ ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም። አንድ ህንጻ በቅርስነት ለመጠበቅ የግድ በቅርስነት መመዝገብ እንዳማይጠበቅበት የሚገልጹት የስነ ህንጻ ባለሙያው፤ “በመመዘኛ ነጥብ እየሰጠን ነው” የሚለው ሃሳብ ጭምር ብዙ ቦታዎች ላይ ክርክር የሚያስነሳ እንደሆነ ያስረዳሉ።
“ቅርስ የድሮ ብቻ አይደለም። ሞደርን ሄሪቴጅም አለ። እነዚህን ከአርክቴክቸራል ብቃታቸው፣ ከከተማ ትዝታነታቸው እና ከከተማዋ ዕድሜ ጋር አብረው በመሄዳቸው፤ የከተማው የዕድገቷ ናቸው። አሁን አንዳንዶች አሁን ያስጀመሩት ይመስላቸዋል። ነገር ግን ብዙ ባለሙያዎች በዚህ ጉዳይ ላይ መነጋገር አይፈልጉም። አደጋ ስላለው ነው” ሲሉ የስነ ህንጻ ባለሙያው ሃሳባቸውን ያብራራሉ።
“ከተማ ቀጣይነት ያለው ነገር ነው። ከተማ የድሮውን እያሻሻለ፣ አንዳንዱን እየቀየረ፣ አዳዲስ እየጨመረ፣ በእነዚህ relationship ነው የሚያድገው” የሚሉት የስነ ህንጻ ባለሙያው፤ ቀደም ሲል “ሲኒማ ኢምፓየር” የነበረውን ቦታ ለአሁን ጊዜ እንዲጠቅም “adapt አድርጎ” መጠቀም መቻሉን ለእዚህ በማሳያነት ያነሳሉ።
በፒያሳ አካባቢ ከ1920ዎቹ መጨረሻ እስከ 1950ዎቹ አጋማሽ የተሰሩ እና የከተማዋ “ሜሞሪዎች” የነበሩ ህንጻዎች ከዓመት በፊት መፍረሳቸውን በቁጭት የሚያስታውሱት ባለሙያው፤ “ይሄ ከተማ ምንም የለውም። ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ ማረጋገጫ ምን ማሳያ አለው? ‘ድሮ እንዲህ ነበርን፣ አሁን እንዲህ ነው’ ለማለት ምን ማሳያ አለው?” ሲሉ ባለሙያው ይጠይቃሉ። ህንጻዎቹ “ከቅርስነት ባለፈ የከተማዋ modernisation ምልክቶች በመሆናቸው” እነሱን ለማፍረስ “የቅርስ ምዝገባን” በምክንያትነት መጥቀስ ተገቢ እንዳልሆነ በማስረዳት አስተያየታቸውን አጠቃልለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































