“ህገ ወጥ የሲቪል ሰዎች ግድያ”፣ “የዘፈቀደ እና የተራዘመ እስር”፣ “አስገድዶ መሰወር እና ጠለፋ” እንዲሁም “ማሰቃየት እና ኢ-ሰብአዊ አያያዝ”፤ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ለሰብአዊ መብቶች ትግበራ “ዋና ዋና ስጋቶች” እንደሚሆኑ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ተነበየ። ኮሚሽኑ በነጻ ሚዲያ እና በጋዜጠኞች ላይ “እየጨመረ መጥቷል” ያለውን “ገደብ” እና በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ “ተጽዕኖ የሚያሳድሩ” ያላቸውን እርምጃዎች እንዲሁ በዋና ስጋትነት መድቧል።
መንግስታዊው የሰብአዊ መብት ተቋም ስጋቶቹን ይፋ ያደረገው፤ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ እስከ 2023 ዓ.ም ድረስ በሚተገብረው የስትራቴጂክ ዕቅድ ሰነድ ላይ ነው። በዚሁ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ኮሚሽኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 2፤ 2018 አዲስ አበባ በሚገኘው ዋና መስሪያ ቤቱ መክሯል።
ኢሰመኮ ዕቅዱን ያዘጋጀው በፍጥነት “በፍጥነት እየተለወጠ ላለው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ምላሽ ለመስጠት” እንደሆነ አመልክቷል። ከዚህ በተጨማሪም የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ “ወቅታዊም ሆነ አዳዲስ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም በሚያስችል ቁመና ላይ እንዲገኝ ለማድረግ” በማለም ዕቅዱ መዘጋጀቱም በሰነዱ ላይ ተጠቁሟል።

አዲሱ ሰነድ “በቀደመው ስትራቴጂክ ዘመን የተገኙ ልምዶችን ግምት ውስጥ ያስገባ”፣ “በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ምህዳር ላይ የተከሰቱ ለውጦችን የሚያንጸባርቅ” እና ኮሚሽኑ “በህግ ከተሰጠው ተልዕኮ ጋር እንዲጣጣም በማድረግ የተዘጋጀ” እንደሆነ ተገልጿል። ኢሰመኮ በህግ ከተሰጡት ተልዕኮዎች መካከል “የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን መመርመር” እንዲሁም “ተጠያቂነትን እና የሕግ የበላይነትን ለማጠናከር አስተዋጽኦ ማድረግ” የሚሉት ይገኙበታል።
ኢሰመኮ ባለፉት አራት ዓመታት ሲተገብረው በቆየው ስትራቴጂክ ዕቅድ “በአብዛኞቹ ዋና ተልዕኮዎቹ ጠንካራ ውጤቶችን ማስመዘገቡን” የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ አዴሎ ገልጸዋል። “በተለይም በሰብአዊ መብቶች ትምህርት፣ በአቤቱታ ቅበላ እና ምላሽ አሰጣጥ፣ በክትትል፣ በምርመራ፣ በህግና ፖሊሲ ማሻሻያ እንዲሁም በተቋማዊ ዕድገት ከፍተኛ አፈጻጸም አሳይቷል” ብለዋል አቶ ብርሃኑ።
የቀድሞው የተቋሙ ስትራቴጂክ ዕቅድ የሸፈነው ጊዜ “በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ እጅግ ፈታኝና የተለያዩ ለውጦች በብዛት ከተስተዋሉባቸው ወቅቶች አንዱ ነበር” ሲል ኢሰመኮ በአዲሱ ሰነዱ ላይ አስፍሯል። “ግጭት፣ መፈናቀል፣ ሰብአዊ ቀውሶች፣ የፖለቲካ ሽግግር እንዲሁም እያደገ የመጣው የህዝብ ተጠያቂነትን የማስፈን ጥያቄ ለሰብአዊ መብቶች መከበር ጉልህ እንቅፋቶችንም ሆነ ዕድሎችን ፈጥረዋል” ሲልም ሰነዱ ያለፉትን አራት ዓመታት ሁኔታ ገምግሟል።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ይኸው ሰነድ፤ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ገጽታ እና በቀጣዩ አምስት ዓመታት የሚኖሩ ጉዳዮችንም የዳሰሰ ነው። አዲሱ የስትራቴጂክ ሰነድ “በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ እንደ ግጭት፣ አስተዳደራዊ ተግዳሮቶች፣ የእኩልነት መጓደል፣ የህዝብ ቁጥር እድገት፣ የኢኮኖሚ ጫናዎች፣ የቴክኖሎጂ ለውጥና አካባቢያዊ ስጋቶችን በመሳሰሉ ጉዳዮች ውስብስብ መስተጋብር የሚወሰን ነው” ሲል ያስገንዝባል።
እነዚህ ሁኔታዎች በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ፣ ተጠያቂነትን በማረጋገጥ እንዲሁም በአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ ኃላፊነት ባለባቸው ተቋማት ላይ “ጉልህ ጫና” እንደሚያሳድሩ ያትታል። የሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎቹ “በአንድ ጊዜ ተመሳሳይ ሰዎችን እና ማህበረሰቦችን በመንካት” “የተደራረቡ የተጋላጭነት እና የመገለል ሁኔታዎች” እንደሚፈጥሩም ሲልም በስትራቴጂክ ሰነዱ ላይ ሰፍሯል።
ሰነዱ ከመጪው 2019 ዓ.ም. ጀምሮ በሚከተሉት አምስት ዓመታት፤ በሰብአዊ መብቶች ትግበራ ላይ “ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖራቸዋል ተብለው የሚጠበቁ” በሚል የዘረዘራቸው አምስት ጉዳዮችን ነው። ከተጽዕኖ አሳዳሪ ጉዳዮች መካከል በቀዳሚነት የተጠቀሰው፤ “ግጭት፣ የጸጥታ ችግር እና መፈናቀል” ነው።

በዚህ ጉዳይ ስር “ዋና ዋና ስጋቶች” በሚል ከተዘረዘሩት ውስጥ “ህገ ወጥ የሲቪል ሰዎች ግድያ”፣ “የዘፈቀደ እና የተራዘመ እስር”፣ “አስገድዶ መሰወር እና ጠለፋ” እንዲሁም “ማሰቃየት እና ኢ-ሰብአዊ አያያዝ” ይገኙባቸዋል። “የታጠቁና የጸጥታ አካላት መበራከት”፣ “ከግጭት ጋር የተያያዘ ወሲባዊ ጥቃት”፣ “በሲቪል ሰዎች እና መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች” እንዲሁም “የሀገር ውስጥ መፈናቀል” በዋና ስጋትነት የተቀመጡ ሌሎች ጉዳዮች ናቸው።
በከፍተኛ ተጽዕኖ አሳዳሪነት የተጠቀሰው ሌላው ጉዳይ “የሲቪክ ምህዳር፣ የሚዲያ ነጻነት እና የህዝብ ተሳትፎ” ነው። በዚህ ረገድ ኢሰመኮ በቀዳሚ ስጋትነት ያስቀመጠው፤ በነጻ ሚዲያ እና በጋዜጠኞች ላይ “እየጨመረ” መጥቷል ያለውን “ገደብ” ነው። በዚህ ጉዳይ ስር በዋና ስጋትነት ከተለዩት መካከል፤ ጋዜጠኞችን፣ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾችን፣ የሲቪል ማህበረሰብ አካላትን፣ ሴት ማህበራዊ አንቂዎች እና አናሳ ድምጾችን “ኢላማ ያደረጉ” ናቸው የተባሉ የበይነ መረብ “ትንኮሳ፣ ማስፈራራት እና በስም ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች” ይገኙበታል።
ኢሰመኮ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ በተለይም በሰብአዊ መብቶች ላይ “ተጽዕኖ የሚያሳድሩ” ያላቸውን “የቁጥጥር፣ የአስተዳደር እና የአሰራር” እርምጃዎችንም ኮሚሽኑ እንዲሁ በዋና ስጋትነት ለይቷል። “ለነጻ ሲቪክ ተሳትፎ እና ለህዝባዊ ተሳትፎ የጠበበ ምህዳር”፣ “ዋልታ ረገጥነት (polarization) እና “እየቀነሰ የመጣ አመኔታ”፣ “የተሳሳቱ እና ሆን ተብለው የሚሰራጩ የተዛቡ መረጃዎች” በተመሳሳይ በዋና ስጋትነት ተመድበዋል።

በቀጣዩቹ አምስት አመታት በሰብአዊ መብቶች ትግበራ ላይ “ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖራቸዋል” ከተባሉት ጉዳዩች መካከል “ተጠያቂነት እና የፍትህ ተደራሽነት” ይጠቀሳል። “መዋቅራዊ የእኩልነት መጓደል” እንዲሁም ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎቶችን፣ ጥበቃና ፍትህን ለማግኘት የሚያጋጥማቸው እንቅፋቶች፣ የአየር ንብረት ለውጥና አካባቢያዊ ጫናዎች፣ ቴክኖሎጂና ወቅታዊ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ቀሪዎቹ በስትራቴጂክ ሰነዱ የሰፈሩ ተጽዕኖ አሳዳሪ ጉዳዮች ናቸው።
“የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ተግዳሮቶች ውስብስብ፣ እርስ በርስ የተሳሰሩ እና ተለዋዋጭ ናቸው” የሚለው ኢሰመኮ፤ ችግሮቹ “በተናጠል በሚደረጉ የመፍትሔ ጥረቶች ብቻ ሊፈቱ እንደማይችሉ” በስትራቴጂክ ሰነዱ አመልክቷል። ለችግሮቹ መፍትሔ ሊበጅ የሚችለው “ተቋማትን በማጠናከር”፣ “ተጠያቂነትን በማሻሻል”፣ “ተሳትፎን በማስፋፋት” እና ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መከሰት መንስኤ የሆኑ “መሰረታዊ ምክንያቶችን በመፍታት” እንደሆነ በሰነዱ ላይ አስገንዝቧል።
የሰብአዊ መብት ተቋሙ በህግ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት እና በአዲሱ ስትራቴጂው ለለያቸው ተግዳሮቶች ምላሽ ለመስጠት፤ “ዝርዝር ተግባራቱን የሚመሩ እና “ቅድሚያ የሚሰጣቸው” ያላቸውን አምስት ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ለይቷል። ከእነዚህ መካከል ቅድሚያ የተሰጠው የፖሊሲ እና የህግ ማሻሻያ ነው።
“በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ተለዋዋጭ እና ብዙ ጊዜም ሊገመት የማይችል ነው”
የሰብአዊ መብቶችን ተገዢነት ማጠናከር በሁለተኛነት ሲቀመጥ የሰብአዊ መብቶች ግንዛቤ ማስጨበጥ እና የአቅም ግንባታ ሶሰተኛ ደረጃን ይዟል። “የፍትህ ተደራሽነት፣ ተጠያቂነት እና መፍትሔ”፤ በኢሰመኮ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ዝርዝር አራተኛ ደረጃን አግኝቷል። ኢሰመኮን “ነጻ፣ ውጤታማ እና ዘላቂ ተቋም በማድረግ ማጠናከር” የሚለው ጉዳይ በመጨረሻነት ተቀምጧል።
“በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ተለዋዋጭ እና ብዙ ጊዜም ሊገመት የማይችል ነው” የሚለው ኢሰመኮ፤ የአምስት ዓመት እቅዱ አፈጻጸም “ከኮሚሽኑ ቀጥተኛ ቁጥጥር ውጪ በሆኑ ምክንያቶች ተጽእኖ ሊገጥመው” እንደሚችል ስጋቱን በስትራቴጂክ ሰነዱ ላይ አስፍሯል። “ግጭት እና የጸጥታ ችግር የማህበረሰቦች ተደራሽነት ላይ ተጽዕኖ ሊያደርጉ፣ የክትትልና የምርመራ ተግባራትን እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረግ ተሳትፎን ሊገድቡ ይችላሉ” ሲልም ኮሚሽኑ አክሏል።
ኢሰመኮ እነዚህን እውነታዎች በመገንዘብ “የስጋት ቅነሳ እና ከተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር የሚላመድ አካሄድን” እንደሚከተል አስታውቋል። ኮሚሽኑ ስጋቶችን በመደበኛነት እንደሚገመግም፣ በአሰራር ሂደት የሚደረጉ ለውጦችን እንደሚከታተል እንዲሁም “አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ” አካሄዶቹን እንደሚያስተካክልም ገልጿል። መስሪያ ቤቱ አዲሱን የስትራቴጂክ ዕቅድ የነደፈው ለወቅታዊ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ምላሽ ለመስጠት ብቻ ሳይሆን፤ ኮሚሽኑ “አዳዲስ ጉዳዮችን ለይቶ እንዲፈታ ለማስቻል ጭምር” መሆኑንም አመልክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































