ተሰናባቾቹ የፓርላማ አባላት ላቀረቧቸው ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከነገ በስቲያ ምላሽ ሊሰጡ ነው  

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከነገ በስቲያ ማክሰኞ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት፤ የ2018 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም እና የቀጣዩን ዓመት በጀት አስመልክቶ ከተሰናባቾቹ የፓርላማ አባላት ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ እንደሚሰጡ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የፓርላማ አባላቱ ጥያቄዎቻቸውን እንዲያስገቡ ቀነ ገደብ የተሰጣቸው እስካለፈው ሰኞ እኩለ ቀን ድረስ እንደነበር ምንጮቹ ገልጸዋል።

በ2008 ዓ.ም የወጣው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሰራር እና የአባላት ስነ ምግባር ደንብ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚያዝላቸው ፕሮግራም መሰረት የመንግስትን የስራ አፈጻጸም ሪፖርት በዓመት ሁለት ጊዜ ለፓርላማው ማቅረብ እንዳለባቸው ይደነግጋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የፌደራል መንግስት የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ሪፖርትን ለተወካዮች ምክር ቤት የላኩት ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ ላይ ነበር።

በተመሳሳይ መልኩ የበጀት ዓመቱ ዋና ዋና ስራዎች አፈጻጸም ሪፖርት ባለፈው ሳምንት አርብ ለፓርላማ አባላት ደርሷቸዋል። በ32 ገጽ የተዘጋጀው “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ይህ ሪፖርት፤ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ ልማት፣ በፍትህ እና አስተዳደር ዘርፎች ያሉ የስራ ክንውኖች በዝርዝር የያዘ ነው። 

ሪፖርቱ የሰላምና ደህንነት ግንባታ ስራዎች፣ የውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አፈጻጸሞችንም ዳስሷል። የሰባተኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ ጉዳይም በሪፖርቱ በአጭሩ ተካትቷል። እነዚህን ጉዳዮች የያዘውን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሪፖርት ለፓርላማ አባላት የላከው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት፤ ይህን በመንተራስ በጹሁፍ የተዘጋጁ ጥያቄዎች እስከ ሰኞ ሰኔ 22፤ 2018 እንዲቀርቡ ቀነ ገደብ ሰጥቷል።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ አባል፤ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን እንዲሁም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የተመለከቱ ጥያቄዎችን በጽሁፍ ማስገባታቸውን ገልጸዋል። ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ካቀረቧቸው ጥያቄዎች መካከል በአምስት አመት ውስጥ ተቀባይነት ያገኙት ሁለት ጊዜ ብቻ መሆኑን የጠቆሙት እኚሁ የፓርላማ አባል፤ በአሁኑም የመመረጥ ዕድል ማግኘታቸው ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው አስረድተዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሰራር እና የአባላት ስነ ምግባር ደንብ፤ የፓርላማ አባላት የሚያቀርቡትን ጥያቄ “መርምሮ የመቀበል” ወይም ውድቅ “የማድረግ ስልጣን” የሰጠው ለአፈ ጉባኤው ነው። ባለፉት አራት ዓመታት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በመሯቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ስብሰባዎች፤ በአማካይ 20 አባላት ጥያቄ እንዲያቀርቡ ይፈቀድላቸዋል።

በስድስተኛው ዙር አጠቃላይ ምርጫ የተመረጡ የፓርላማ አባላት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በተገኙበት በመጪው ማክሰኞ ሰኔ 30 የሚያካሄዱት “መደበኛ ስብሰባ” የመጨረሻቸው ይሆኗል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሐምሌ ወር ጀምሮ እስከ መስከረም የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ ድረስ ለእረፍት እንደሚበተን በአሰራር እና የአባላት ስነ ምግባር ደንቡ ላይ ተደንግጓል።

በዚህ ጊዜ ውስጥ የሚከሰቱ የተወካዮች ምክር ቤት መመልከት የሚገባው ጉዳይ የሚከሰት ከሆነ፤ አስቸኳይ የፓርላማ ሰብሰባ ሊጠራ ይችላል። ፓርላማው በመጪው ማክሰኞ በሚያካሄደው 30ኛ መደበኛ ስብሰባው፤ በተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርበውን የዓመቱ ማጠቃለያ ሪፖርት ላይ በተጨማሪነት ውይይት ያደርጋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)