በጋምቤላ ክልል ባለፈው ሁለት ሳምንት በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረ “ግጭት” እና “የጸጥታ መደፍረስ”፤ “የሰዎች ህይወት መጥፋቱን” እና “የአካል ጉዳት መድረሱን” የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። በክልሉ በሰዎች በህይወት መኖርን ጨምሮ ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳይደርሱ ለመከላከል “በቂ” የጸጥታ አካላት “በአስቸኳይ” እንዲሰማሩ እንዲደረግ ኮሚሽኑ ጠይቋል።
ኢሰመኮ ጥያቄውን ያቀረበው፤ በጋምቤላ የተለያዩ አካባቢዎች “የሚያገረሹ” ግጭቶች በክልሉ ነዋሪዎች ሰብአዊ መብቶች ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት በተመለከተ ዛሬ እሁድ ታህሳስ 12፤ 2018 ባወጣው መግለጫ ነው። ኮሚሽኑ በዚሁ መግለጫው፤ በክልሉ ውስጥ ባሉት ኢታንግ ልዩ ወረዳ፣ ጋምቤላ ወረዳ እና በጋምቤላ ከተማ ከህዳር 28 ጀምሮ የተፈጠሩ ግጭቶችን እየተከታተለ እንደሚገኝ ገልጿል።
የጋምቤላ ከተማ ፖሊስ አዛዥ የነበሩት ዋና ኢንስፔክተር ኡሞድ ኡጅሉን መገደል ተከትሎ በጋምቤላ ከተማ እና በአካባቢው ባሉት ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ግጭት ተፈጥሮ እንደነበር ኢሰመኮ በመግለጫው ጠቅሷል። የጋምቤላ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ባለፈው ማክሰኞ ታህሳስ 7፤ 2018 ከተገደሉ በኋላ በከተማይቱ ለቀናት የቆየ የተኩስ ልውውጥ ሲካሄድ እንደነበር ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረው ነበር።
ይህንኑ በዛሬው መግለጫው ያረጋገጠው ብሔራዊው የሰብአዊ መብቶች ተቋም፤ በዚህም ሳቢያ “የሰዎችን ህይወት መጥፋቱን” እና “የአካል ጉዳት መድረሱን” አስታውቋል። ሆኖም ኮሚሽኑ ባለፉት ቀናት በነበሩ ግጭቶች ምን ያህሉ ሰዎች እንደሞቱ እና እንደተጎዱ በመግለጫው ከመዘርዘር ተቆጥቧል።
በጋምቤላ ከተማ በነበረው ግጭት ምክንያት ባንኮች እና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ በርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት ማቋረጣቸውን እንደተገነዘበም ኢሰመኮ በመግለጫው አስፍሯል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች፤ በከተማይቱ በነበረው የጸጥታ መደፍረስ ምክንያት የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት መደበኛ እንቅስቃሴ መቆሙን ገልጸው ነበር።
ኢሰመኮ በዛሬው መግለጫው፤ በጋምቤላ ከተማ “የሰዎችን እና የመጓጓዣ አማራጮችን እንቅስቃሴ የሚገድብ” የሰዓት እላፊ በክልሉ መንግስት መጣሉንም አንስቷል። የክልሉ መንግስት መቀመጫ በሆነችው የጋምቤላ ከተማ፤ “በወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ” ምክንያት ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ በሚደረግ የተሽከርካሪ እና የሰው እንቅስቃሴ ላይ ክልከላ የተጣለው ህዳር 30፤ 2018 ነበር።
በጋምቤላ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭት እና የሰላም መደፍረስ “በፍጥነት በማስቆም” በሰዎች በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነት፣ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር፣ የንብረት፣ የስራ እንዲሁም ሌሎች ሰብአዊ መብቶች ላይ ተጨማሪ ጥሰቶች እንዳይደርሱ “መከላከል” እንደሚገባ ኢሰመኮ በመግለጫው አሳስቧል። ለዚህም በክልሉ “በቂ የጸጥታ አካላት” “በአስቸኳይ እንዲሰማሩ” እንዲደረግ ኮሚሽኑ ጠይቋል።
ትላንት ቅዳሜ በጋምቤላ ከተማ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ፤ የመከላከያ ሰራዊት ማዕከላዊ ዕዝ ጸጥታ በማስከበር ስራ ላይ መሰማራቱ ተገልጿል። በውይይቱ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ሙላቱ ጀልዱ፤ የህብረተሰቡን ሰላም በሚያውኩ አካላት ላይ “የህግ ማስከበር ስራ” “በትኩረት እየተሰራ” መሆኑን መናገራቸውን የክልሉ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
በዚሁ ውይይት ላይ ተሳታፊ የነበሩ ነዋሪዎች፤ “ግጭት እና ሁከት የሚፈጥሩ” ያሏቸው አካላት “በህግ ተጠያቂ” እንዲሆኑ ጠይቀዋል ተብሏል። ኢሰመኮ በዛሬው መግለጫው፤ በክልሉ በበተለያዩ ጊዜያት የሚፈጠሩ ግጭቶችን “በዘላቂነት ለማስቆም” እና “ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ” መደረግ ያለባቸውን ጉዳዮችን አንስቷል።

በጋምቤላ ክልል በግጭት የተሳተፉ እንዲጠየቁ እና ተመሳሳይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ወደፊት እንዳይከሰቱ ለመከላከል፤ የፌዴራሉ እና የክልሉ መንግሥታት “ተገቢ እርምጃዎችን ሊወስዱ ይገባል” ብሏል ኢሰመኮ በመግለጫው። የክልሉ መንግስት ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፤ “የጦር መሳሪያ” ይዘው በሚገኙ እና በሚንቀሳቀስ ግለሰቦች እና ቡድኖች ላይ የጸጥታ ኃይሎች “አስፈላጊውን እርምጃ” እንደሚወስዱ አስጠንቅቆ ነበር።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ፤ በጋምቤላ ክልል የሚከሰቱ ግጭቶች እና የሰላም መደፍረሶች፤ በክልሉ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ለማሻሻል የሚደረጉ “ጥረቶችን” እና “እርምጃዎችን” “እየተፈታተኑ” እንደሆነ መናገራቸው በዛሬው የኮሚሽኑ መግለጫ ተጠቅሷል። ኮሚሽኑ ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ ለፌዴራሉ እና ለክልሉ መንግሥታት የሰጣቸው “ምክረ ሐሳቦች” በተሟላ ሁኔታ እንዲፈጸሙ ማድረግ እንደሚገባ ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።
በክልሉ በግጭቶች እና ጥቃቶች ላይ “ተሳታፊ የሆኑ” ቡድኖች እና ግለሰቦች ላይ “ተገቢውን የወንጀል ምርመራ በማድረግ”፤ ተጠያቂነት የማረጋገጥ ጥረቶችን “የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል” እንደሚያስፈልግ አቶ ብርሃኑ አሳስበዋል። በጋምቤላ ከተማ እና በተወሰኑ ወረዳዎች በተከሰቱ ግጭቶች “እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ ወንጀለኞችን”፤ የጸጥታ አካላት “በቁጥጥር ስር እያዋሉ” መሆኑን የጋምቤላ ክልል መንግስት ባለፈው ሐሙስ ባወጣው አጭር መግለጫ አስታውቆ ነበር።

የጋምቤላ ክልልን ህዝብ ግጭት ውስጥ በማስገባት “የራሳቸውን እኩይ ዓላማ ለማስፈጸም እየሰሩ የሚገኙ” አካላት እንዳሉ በትላንቱ ውይይት ላይ የተናገሩት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ጋትሉዋክ ሮን፤ “እነዚህን አካላት በመለየት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ እየተከናወነ ነው” ማለታቸውን የክልሉ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)






























