ምርጫ ቦርድ በጋዜጠኞች ላይ ያስቀመጠው የቃለ መሃላ ግዴታ “የሳንሱር መሣሪያ ነው” ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ተቸ

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ሊካሄድ ጥቂት ቀናት በቀሩት 7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ዋዜማ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋዜጠኞች ምርጫውን ለመዘገብ የዕውቅና ባጅ ከመውሰዳቸው በፊት እንዲፈርሙ ያስገደደው “የቃለ መሃላ” ስርዓት በነፃው ፕሬስ ላይ የተጣለ “የቁጥጥር እና የሳንሱር መሣሪያ ነው” ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ተቸ።

ተቋሙ ዛሬ አርብ ግንቦት 21 ባወጣው አስቸኳይ መግለጫ፣ ምርጫ ቦርድ ጋዜጠኞች የቦርዱን መመሪያዎች እንዲያከብሩና “ስለቦርዱ የተሳሳተ መረጃ መስጠት በህግ የሚያስጠይቅ” መሆኑን አውቃለሁ” የሚለውን ደንብ አምነው እንዲቀበሉ ያስቀመጠው ይሄው መሃላ፣ ሰፊ ትርጓሜ የሚሰጡና ለሳንሱር በር የሚከፍቱ ቃላት የሞሉበት መሆኑን ገልጿል።

የአምነስቲ የምሥራቅና የደቡብ አፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተር ቲገሬ ቻጉታ ይሄንን የምርጫ ቦርድ አካሄድ ሲተቹ “በምርጫ ወቅት የፕሬስ ነፃነት እና የመረጃ ፍሰት ወሳኝ ናቸው። ይህ በምርጫ ቦርድ የተጠየቀው መሃላ፣ ስለ መጪው ምርጫ በሕዝብ ፊት በሚደረጉ ውይይቶች ላይ ቁጥጥር ለማድረግ የተዘረጋ ግልጽ መሣሪያ ነው፤ ቦርዱ የማይመቹ መረጃዎችን ሳንሱር እንዲያደርግ ወይም የትኛው እውነት የትኛው ሐሰት እንደሆነ በራሱ እንዲወስን ሥልጣን ይሰጠዋል” ብለዋል።

አምነስቲ አክሎም፣ ምርጫው ጥቂት ሳምንታት ሲቀሩት በመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት (ለምሳሌ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሬድዋን ሁሴን እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ዳንኤል ክብረትን በመጥቀስ) እና በኢትዮጵያ ሚዲያ ባለሥልጣን (ኢሚባ) በኩል ገለልተኛ ጋዜጠኝነትን “የአገር ደኅንነት ስጋት” አስመስሎ የመፈረጅ የተሳሳተ ዘመቻ መክፈቱ፣ መንግሥት ሥልጣኑን ለማጠናከር አምባገነናዊ አካሄዶችን እየተጠቀመ መሆኑን ያሳያል በማለት ትችት ሰንዝሯል።

በተጨማሪም ባለፉት ወራት እንደ አዲስ ስታንዳርድ እና ዋዜማ ሬዲዮ ያሉ ሚዲያዎች መታገዳቸውን እንዲሁም የሮይተርስ ጋዜጠኞች ፍቃድ መሰረዙን ያነሳው መግለጫው፣ የፀጥታው ድባብ እና የስልክ ጠለፋ ፍርሃት በጋዜጠኞች ላይ “ራሳቸውን በራሳቸው ሳንሱር የማድረግ (Self-censorship)” ከፍተኛ ማነቆ መፍጠሩንና ተቃዋሚ ፖለቲከኞችም ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ለመነጋገር መሸሻቸውን ይፋ አድርጓል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)