በአማራ ክልል በተጣለ የእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት በባህር ዳር ያሉ የህዝብ ማመላለሻ አሽከርካሪዎች ስራቸውን አቁመው ዋሉ 

የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) የተሰኘው ታጣቂ ኃይል በአማራ ክልል ለአምስት ቀናት የሚቆይ የእንቅስቃሴ እገዳ መጣሉን ተከትሎ፤ ከባህር ዳር ወደ ተለያዩ ከተሞች የሚጓዙ አሽከርካሪዎች በዛሬው ዕለት ስራቸውን ማቆማቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። በጎንደር እና በደብረ ማርቆስ ከተሞች የሚገኙ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ መናኸሪያዎችም በተመሳሳይ በዛሬው ዕለት ምንም ዓይነት ስምሪት አለማስተናገዳቸውን የዓይን እማኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

አፋብን ከሁለት ቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ፣ ከዛሬ አርብ ግንቦት 21፤ 2018 ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት “ከአምቡላንሶች በስተቀር” ሁሉም መንገዶች ለተሽከርካሪ “ዝግ መደረጋቸውን” አስታውቆ ነበር። ንቅናቄው በተሽከርካሪዎች ላይ ገደቡን የጣለው፤ “የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ” ሲባል እንደሆነ በመግለጫው አመልክቷል። 

ታጣቂ ቡድኑ በዚሁ መግለጫው፤ በአማራ ክልል እና በሌሎች አካባቢዎች “የተፋፋመ ጦርነት” ባለበት ሁኔታ ገዢው ፓርቲ በመጪው ሰኞ ግንቦት 24 “የምርጫ ድግስ” ማዘጋጀቱን ኮንኗል። ምርጫው “ህዝቡን ባሳተፈ መንገድ እንደማይከናውን” እና “የምርጫ ሂደትን ለማሳካት የሚያበቃ አንዳችም ቅድመ ሁኔታ ያልተሟላ” መሆኑን ገዢው ፓርቲ እንደሚያውቅ የገለጸው አፋብን፤ ሂደቱን የሚያከናውነው “ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን እና ሌላውን ኢትዮጵያዊ ጭምር ለማታለል” እንደሆነ ወንጅሏል።

ከመከላከያ ሰራዊት ጋር የሚደረጉ ውጊያዎች “በበርካታ አካባቢዎች ከሌላው ጊዜ በባሰ ሁኔታ ተጠናክረው ቀጥለዋል” ሲል በመግለጫው ያስታወቀው አፋብን፤ ይህን ተከትሎ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት የጉዞ እገዳ የያዘውን “የጥንቃቄ መልዕክት” ማስተላለፍ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አብራርቷል። ይህን የእንቅስቃሴ እገዳ በመፍራት በባህር ዳር ከተማ የሚገኙ አሽከርካሪዎች በዛሬው ዕለት ከጉዞ ራሳቸውን አቅበው ውለዋል። 

በባህር ዳር ከተማ የሚገኘው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ዛሬ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ረፋዱ አራት ሰዓት ድረስ ባደረገው የመስክ ምልከታ፤ ወደተለያዩ ከተሞች ሕዝብ የሚያመላልሱ ሚኒባሶች እና አውቶቡሶች አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውን ታዝቧል። በከተማዋ በሚገኙት የጎንደር በር እና የጎጃም በር መናኸሪያዎችም ከሌላው ጊዜ ያነሱ ሚኒባሶች እና አውቶብሶች ያለ ስራ ቆመው ተመልክቷል። 

ሁለቱ መናኸሪያዎች አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ደብረ ማርቆስ፣ ጎንደር እና ደሴ ከተሞች የሚጓዙ የህዝብ ማመላለሻዎች እና መኪኖች ተሳፋሪዎችን የሚጭኑባቸው እና የሚያወርዱባቸው ናቸው። ከእነዚህ መናኸሪያዎች የሚነሱ ተሽከርካሪዎች፤ ከመዳረሻቸው አስቀድሞ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ለሚገኙ ነዋሪዎችም የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጣሉ። 

ከባህር ዳር ወደ ጎንደር እስቴ ወረዳ ተሳፋሪዎችን የሚያጓጉዝ “ሃይሩፍ” ሚኒባስ ባለቤት የሆኑ አንድ ግለሰብ፤ በዛሬው ዕለት የነበራቸውን ጉዞ መሰረዛቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ነግረውታል። ሚኒባሳቸውን በጎንደር በር መናኸሪያ ያቆሙት እኚሁ አሽከርካሪ፤ ከጉዟቸው የታቀቡት በአፋብን የተላለፈውን የእንቅስቃሴ ገደብ ማስጠንቀቂያ ሰምተው እንደሆነም አስረድተዋል። 

አሽከርካሪው እገዳውን ተላልፈው ቢንቀሳቀሱ፤ በታጣቂ ቡድኑ “እርምጃ ሊወሰድብን ይችላል” የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል። በዛሬው ዕለት ከባህር ዳር ወደ ፍኖተ ሰላም መጓዝ የነበረበት አንድ የህዝብ ማመላለሻ ሹፌርም፤ ያለውን ተመሳሳይ ስጋት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ አጋርቷል። 

“የተላለፈውን እገዳ ፈርተን ስንቆም፤ የመንግስት ስምሪቶች በቅጣት እያስፈራሩን ነው። እገዳውን ጥሰን ብንወጣ አደጋ ይደርስብናል። አይ ብለን ፈርተን ብንቀመጥ ደግሞ እዚህ መናኸሪያ ውስጥ መስራት አንችልም። በአጠቃላይ አጣብቂኝ ውስጥ ነን ያለነው” ሲል አሽከርካሪው ያለበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ያስረዳል።

ይህንን ሃሳብ እንደ እርሱ በጎጃም በር መናኸሪያ ቆመው የሚሆነውን የሚጠባበቁ ሌሎች ሹፌሮችም አስተጋብተዋል። በጎንደር በር መናኸሪያ በቡድን ሆነው ቆመው ዘጋቢያችን ያገኛቸው አሽከርካሪዎችም፤ ተመሳሳይ አስተያየት አላቸው። እነዚህ አሽከርካሪዎች በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል በሁሉም አቅጣጫዎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች “በአጣብቂኝ ሁኔታዎች የተሞሉ” በመሆናቸው ላይ ይስማማሉ።

ለአጣብቂኙ አንዱ ማሳያ በዛሬው ዕለት ስራቸውን ባቆሙ አሽከርካሪዎች ላይ የጎንደር በር መናኸሪያ የስምሪት ሰራተኞች ሲያስተላልፉት የነበረው ትዕዛዝ ነው። ሰራተኞቹ መዳረሻቸውን አዘዞ፣ ጭምባ፣ እስቴ፣ ሐሙሲት፣ አዲስ ዘመን እና ሰቆጣ ያደረጉ ተሽከርካሪዎችን ታርጋ በድምጽ ማጉያ በመጥራት ማስጠንቀቂያ ሲሰጡ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ አድምጧል።

ይኸው ማሳሰቢያ “ተሽከርካሪዎቹ ወደ ሥራ ገብተው መስመራቸውን የማይሸፍኑ ከሆነ በቀጣይ የነዳጅ ወረፋ ተጠብቆላቸው እንደማይስተናገዱ” እና “ለሚወሰድባቸው የትኛውም ተጨማሪ እርምጃ ኃላፊነቱን ራሳቸው እንደሚወስዱ” የሚያስጠንቅቅ ነው። ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ በጎጃም በር መናኸሪያ ባሉ የስምሪት ሰራተኞችም በዛሬው ዕለት ሲተላለፍ አርፍዷል።

የህዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች እና ሚኒባሶች ማስጠንቀቂያ ጭምር ተሰጥቷቸው ወደ ስራ ባለመመለሳቸው፤ በተጓዦች ላይ ጫና አሳድሯል። በባህር ዳር መናኸሪያዎች ውስጥ ለቆሙ ተሽከርካሪዎች ስምሪት እስኪሰጥ ድረስ፤ በትኬት መቁረጫ መስኮቶች ትኬት ለመቁረጥ የተሰለፉ በርካታ ተጓዦችን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክቷል። 

በዛሬው ዕለት ወደ የቤተሰቦቻቸው ለመጓዝ አቅደው የነበሩ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም፤ በእንቅስቃሴ እገዳው ምክንያት ተችግረው ታይተዋል። በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዋና ግቢ በር ላይ ተሰብስበው የነበሩ አስር ገደማ የሚሆኑት እነዚህ ተማሪዎች፤ ቤተሰቦቻቸው ወደሚገኙባቸው ከተሞች የሚሄዱ ተሽከርካሪዎች በማጣታቸው ምክንያት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቸው ለመመለስ ተገድደዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)