ከአንድ ወር በኋላ ለሚጀምረው የ2019 በጀት ዓመት፤ የ2.34 ትሪሊዮን ብር በጀት መዘጋጀቱን የፌደራል መንግስት አስታወቀ። ካለፈው ዓመት በጀት በ410 ቢሊዮን ብር ገደማ ያህል የጨመረው የመጪው ዓመት በጀት፤ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልኳል።
በጀቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያስተላለፈው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው። ምክር ቤቱ ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 2፤ 2018 ባደረገው መደበኛ ስብሰባው፤ በቀረበለት የበጀት መጠን ላይ “በሰፊው መወያየቱን” የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
የ2019 የፌዴራል መንግስት በጀት የተዘጋጀው፤ የሀገሪቱ የአስር አመት መሪ የልማት ዕቅድ አካል የሆነውን የመጪዎቹ አምስት ዓመታት “የማክሮ ኢኮኖሚ እና የፊሲካል ማዕቀፍን መሰረት በማድረግ” መሆኑን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል። ከመጪው ዓመት ጀምሮ እስከ 2023 ዓ.ም ድረስ ያለውን ጊዜ የሚሸፍነው ይህ ማዕቀፍ፤ በስራ ላይ እንዲውል የተወሰነው በዛሬው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ነው።
የዘንድሮውን ዓመት በጀት አፈጻጸም “መነሻ በማድረግ” መዘጋጀቱ የተነገረለት የ2019 በጀት፤ የፌደራል መንግስት የመደበኛ እና ካፒታል ወጪዎችን፣ ለክልሎች የሚደረገውን ድጋፍ እንዲሁም ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ የተመደበውን ድጋፍ ያካተተ ነው። በመጠናቀቅ ላይ ባለው በጀት ዓመት ለመደበኛ ወጪ 1.2 ትሪሊዮን ብር፣ ለካፒታል ወጪዎች ደግሞ 415 ቢሊዮን ብር ተመድቦ ነበር።
በ2018 በጀት ዓመት ለክልሎች እና ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እንዲከፋፈል ተበጅቶ የነበረው የገንዘብ መጠን 314.8 ቢሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል። በዚህ የበጀት ድጋፍ ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አለመካተቱ በወቅቱ አነጋግሮ እንደነበር አይዘነጋም።
በ21 በመቶ ገደማ የጨመረው የመጪውን ዓመት በጀት ምን ያህሉ ለክልሎች፣ ለመደበኛ እና ለካፒታል ወጪዎች እንደተመደበ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መግለጫ በዝርዝር አላቀረበም። ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር መሰረት፤ የበጀቱን ዝርዝር የገንዝብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የስልጣን ዘመኑ በዚህ ወር ለሚጠናቀቀው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀጣዩቹ ቀናት ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




























