ኢትዮ ቴሌኮም በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት 215.82 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ። ገቢው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ33.2 በመቶ ዕድገት ያሳየ ነው።
መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ለተመዘገበው ዕድገት እንደ አንድ ምክንያት የጠቀሰው የገቢ ምንጮቹ መስፋፋትን ነው። የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 16፤ 2018 በሰጡት መግለጫ፤ ከዚህ ቀደም የኩባንያው የገቢ ምንጮች በሞባይል ድምጽ፣ በዳታ እና በኔትወርክ ትስስር (interconnect) ላይ ብቻ የተገደቡ እንደነበሩ አስታውሰዋል።
ተቋሙ በ2018 በጀት ዓመት ላገኘው ገቢ ከፍተኛውን ድርሻ ካበረከቱ የአገልግሎት ዓይነቶች መካከል የዳታ እና ኢንተርኔት አገልግሎት ይጠቀሳሉ። ሁለቱ አገልግሎቶች ከተቋሙ ገቢ ያላቸው ድርሻ 31.1 በመቶ መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ እንዳገኘው የገለጸው ያልተጣራ ትርፍም፤ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ47.5 በመቶ ዕድገት ተመዝግቦበታል። ኩባንያው በ2018 በጀት ዓመት ያስመዘገበው ያልተጣራ ትርፍ 92.9 ቢሊዮን ብር ነው።
በአዲስ አበባው ሳይንስ ሙዚየም በተሰጠው የኢትዮ ቴሌኮም ዓመታዊ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት መግለጫ ላይ ሌላው ይፋ የተደረገው ጉዳይ የኩባንያው ደንበኞችን የተመለከተ ነው። የኢትዮ ቴሌኮም ጠቅላላ ደንበኞች ቁጥር 90.12 ሚሊዮን መድረሱን የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፤ ይህም ካለፈው አመት አንጻር የ8.3 በመቶ ዕድገት ያለው መሆኑን አስታውቀዋል።
በበጀት ዓመቱ የኩባንያው የሞባይል ድምጽ ተጠቃሚዎች ብዛት 66.95 ሚሊዮን መድረሱን፣ “ንቁ” የሞባይል ዳታ ተጠቃሚዎች ቁጥር ደግሞ ወደ 51.53 ሚሊዮን ከፍ ማለቱ በዛሬው መግለጫ ተጠቅሷል። የኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት የሆነውን “ቴሌ ብር” የሚጠቀሙ 8.54 ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞች በበጀት ዓመቱ ማፍራት መቻሉም ተገልጿል።

በ2018 በጀት ዓመት የተጠቃሚዎቹ ብዛት 60.6 ሚሊዮን በደረሰው “ቴሌ ብር” የተፈጸመው የግብይት መጠን 4.19 ትሪሊዮን ብር እንደሆነ የተቋሙ መግለጫ ያመለክታል። መተግበሪያው አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ በአጠቃላይ 9.13 ትሪሊዮን ብር የሚገመት ግብይት እንደተካሄደበት የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































