የህገ መንግስቱ አንቀጽ 39 ጉዳይ በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ እያከራከረ ነው

በይፋ ከተከፈተ አንድ ሳምንት ባስቆጠረው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ተወካዮች፤ በስምንት ዋነኛ አጀንዳዎች በተከፋፈሉ ጉዳዮች ላይ እየተወያዩ ይገኛሉ። ከእነዚህ ዋነኛ አጀንዳዎች መካከል “የመንግስት አደረጃጀት እና ቅርጽ” እንዲሁም “የፖለቲካ ስርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ስርዓትን” የሚመለከተው ይገኝበታል።

በዚህ አጀንዳ ስር በንዑስ አጀንዳነት ከተያዙ የውይይት ጉዳዮች ውስጥ፤ “የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መብትን” የያዘው የኢፌዲሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 39 አንዱ ነው። በዚህ አንቀጽ በመጀመሪያ ረድፍ የተቀመጠው ድንጋጌ “ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ እና ህዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው” ይላል። 

ይህ በየጊዜው ክርክር የሚነሳበት ድንጋጌ፤ በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ እየተወያዩ በሚገኙ ተሳታፊዎች ዘንድ “አለመግባባት” ከፈጠሩ ጉዳዮች አንዱ ሆኗል። በዚህ ጉዳይ ላይ ከተወያዩ ንዑስ ቡድኖች ውስጥ የአንዱ አባል የሆኑት የቁጫ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን (ቁህዴፓ) ተወካይ አቶ ባንዲራ በላቸው፤ “አንቀጽ 39 የመብቶች ጥግ” መሆኑን በምክክሩ ወቅት መንጸባረቁን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

“አንቀጽ 39 ‘ይነሳ የሚሉ’ አሉ። ‘አይነሳ [የሚሉ አሉ]። ይህ የዜጎች መብት፣ የመብቶች ሁሉ ዋስትና ነው። ኢትዮጵያን እና ብሔረሰቦችን፣ የቋንቋ፣ የማንነት ጥያቄዎችን፣ መንግስታት ስልጣን ይዘው የህዝብ ጥያቄ በማይፈቱበት ጊዜ፤ ህዝቡ በመንግስት ላይ ጫና እንዲያሳድር ያስችላል። ይሄ አንቀጽ የጭቆና ዋስትና ነው። ነገር ግን እስካሁን መግባባት ላይ መድረስ አልተቻለም” ሲሉ የፓርቲው ተወካይ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን (ትዴፓ) በመወከል በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ላይ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት የፓርቲው ዋና ጸሐፊ አቶ ሙሉብርሃን ኃይሌ፤ በህዝቦች መካከል ልዩነት እየፈጠሩ ያሉ አንቀጾች ላይ ውይይት መደረጉን በበጎ ጎን የሚታይ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። እርሳቸው በሚገኙበት ንዑስ ቡድን “የአንቀጽ 39” ጉዳይ መነሳቱን የጠቆሙት አቶ ሙሉብርሃን፤ በዚህ ላይ እርሳቸው ያላቸው አቋም “አንቀጽ 39 መቀየር አለበት” የሚል መሆኑን አስረድተዋል።

በንዑስ ቡድናቸው “አንቀጹ ሙሉ ይነሳ” የሚል ሃሳብ ተቀባይነት ባያገኝም፤ “መገንጠል የሚለው ቃል መውጣት አለበት” የሚል ስምምነት ላይ መድረስ መቻሉን ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም “የፖለቲካ ድርጅት ‘በዘር መደራጀት መቆም አለበት’ የሚል ስምምነት ላይ ደርሰናል” ሲሉም አክለዋል።

በመንግስት አስተዳደር አጀንዳ ላይ በንዑስ አጀንዳነት የቀረበው ሌላው ጉዳይ የመሪዎች የስልጣን ዘመን መገደብን የሚመለከት ነው። የፌደራል እና የክልል መንግስታት መሪዎች የስልጣን ዘመን “በጊዜ መገደብ አለበት ወይስ መገደብ የለበትም?” በሚለው ላይ ውይይት መደረጉን የቁህዴፓው አቶ ባንዲራ ተናግረዋል።

እርሳቸው በሚገኙበት ንዑስ ቡድን፤ የአንድ መሪ የስልጣን ዘመን “ከሁለት ዘመን በላይ እንዳይበልጥ” በሚል ከስምምነት ላይ መደረሱን አስረድተዋል። መሪው “እምነቱን ባጣ እና በሚያጠፋበት ወቅት” የስልጣን ዘመኑ ባይጠናቀቅም ከኃላፊነቱ ሊወገድበት የሚችልበት አሰራር እና በህግ ሊጠይቅበት የሚችልበት ስርዓት እንዲዘረጋ ምክረ ሃሳብ ማቅረባቸውንም የቁህዴፓው ተወካይ አክለዋል። 

የአገው ብሔራዊ ሸንጎ (ሸንጎ) ፕሬዝዳንት አቶ አላምረው ይርዳው፤ በንዑስ ቡድናቸው “የመንግስት ስልጣን ዘመን መገደብ አለበት” የሚል ሃሳብ መቅረቡን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ለሀገራዊ ምክክሩ ካቀረባቸው አጀንዳዎች መካከል “የስልጣን ዘመን” ጉዳይ አንዱ መሆኑን አስታውቆ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሁለት ሳምንት በፊት በፓርላማ በነበራቸው የጥያቄ እና መልስ ቆይታ ላይ፤ በፕሬዝዳንትነት የሚመሩት ፓርቲ “በስልጣን ላይ ያለ መንግስት ለሁለት የስልጣን ዘመን ብቻ እንዲቆይ” የሚል አጀንዳ ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ማቅረቡን አረጋግጠዋል። አብይ ፓርቲያቸው ያቀረበውን አጀንዳ “ታላቅ እርምጃ”፣ “ለሀገር የሚጣል ጡብ” እና “መሰረት ነው” ሲሉ በዚሁ ስብሰባ ላይ አሞካሽተዋል።

በሀገራዊ ምክክሩ “የመንግስት አደረጃጀት እና ቅርጽን” በሚመለከተው አጀንዳ ስር ከተካተቱ 17 ንዑስ አጀንዳዎች መካከል “የኢትዮጵያ የመንግስት አደረጃጀት ምን ይመስል?” የሚለው ይገኝበታል። ለዚህ ጉዳይ በአማራጭነት የቀረቡት “ፕሬዝዳንታዊ፣ ፓርላመንታዊ እና ከፊል ፕሬዝዳንታዊ” የሚሉ   የመንግስት ስርዓት አይነቶች ነው።

የዶንጋ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ዶህዴፓ) ተወካይ አቶ አለሙ ከበደ በዚህ ጉዳይ ላይ ንዑስ ቡድናቸው “ሰፊ ውይይት” ማድረጉን ገልጸዋል። ከውይይቱ በኋላ “ለኢትዮጵያ ለፌደራል ስርዓቱ የሚጠቅመው ፓርላመንታዊ ነው የሚለውን እንደ ቡድን ወስነናል” ሲሉ አቶ አለሙ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተነሳው ሌላው ንዑስ አጀንዳ፤ የመንግስት አስተዳደር  የተመለከተ ነው። በዚህ ረገድ ለሀገራዊ ምክክሩ ተሳታፊዎች በተሰራጨው ሰነድ ላይ በመሪ ጥያቄነት የቀረቡት አማራጮች “አሃዳዊ (unitary)፣ ፌደራላዊ (federal) ወይስ ኮንፌደራላዊ (confederation)”  የሚሉት የመንግስት አስተዳደር ቅርጾች ናቸው። 

በዚሁ ሰነድ ላይ “ሀገሪቱ የፌደራላዊ ስርዓት ሀገሪቱ የምትከተል ከሆነ የትኛው ፌደራል ስርዓት አይነት ለኢትዮጵያ ተገቢ ነው?” የሚል ጥያቄም ለውይይት ቀርቧል። “አሁን ያለውን የፌደራል ስርዓት ምንም ማሻሻያ ሳይደረግበት እናስቀጥል ወይንስ አሁን ያለው የፌደራል ስርዓት ድክመቶች ተገምግመው ማሻሻያ ይደረግበት?” የሚሉ ተከታይ ጥያቄዎችም በሰነዱ ላይ ተካትተዋል። ሀገሪቱ “የተለየ ስርዓት ሞዴል ትከተል ወይ?” የሚለውም ሌላው በአማራጭነት የቀረበ ጥያቄ ነው።

በእርሳቸው ንዑስ ቡድን በእነዚህ ጉዳዮች ላይ “ሰፊ የሆነ ክርክር እና ውይይት” መደረጉን አቶ አለሙ ገልጸዋል። ከውይይቱ በኋላም ቡድናቸው የፌደራል ስርዓቱ መቀጠል እንዳለበት መስማማት ላይ እንደደረሰም አመልክተዋል። 

“እንደ ሀገር ፌደራላዊ ስርዓትን መከተል አለብን። ፌደራላዊ ስርዓቱ ከዚህ በፊት ያለውን አንዳንድ ድክመቶቹን አሻሽሎ፤ የመንግስት ስርዓት አመቺነትን፣ ቋንቋን መሰረት ያደረጉ፣ የህዝብን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ መስፈርቶችን ተከትሎ፤ በውስጡ ያለውን ደካማ ጎን ካስተካከለ ለኢትዮጵያ ይጠቅማል በሚል ውይይት አድርገናል” ሲሉም የቦህዴፓው ተወካይ የምክክሩ ይዘት አብራርተዋል። 

የሸንጎው አቶ አላምረው በበኩላቸው በእርሳቸው ንዑስ ቡድን በነበረው ውይይቱ ላይ በሁሉም ጉዳይ መስማማት ላይ አለመደረሱን እና በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ልዩነት መኖሩን ተናግረዋል። የፌደራል ስርዓትን በተመለከተ በንዑስ ቡድናቸው የነበረውን ውይይት ሲገልጹም፤ “በአሁን ሰዓት ባለው ሁኔታ የብሔር ፌደራሊዝምን ማስቀረት አይችልም። ሌላ ችግር ነው የሚያመጣው። ነገር ግን አንድ ክልል ‘በአንድ ብሔር ስም መጠራት የለበትም። በወል ስም መጠራት የለበትም’ የሚል ሀሳብ ቀርቧል” ሲሉ አስረድተዋል።

የትዴፓው ዋና ጸሐፊ አቶ ሙሉብርሃን በበኩላቸው በመንግስት አስተዳደር ቅርጽ ላይ በእርሳቸው ንዑስ በተደረገ ውይይት ላይ “አሃዳዊ” በሚለው ሀሳብ ላይ ልዩነት መፈጠሩን እና የተሳሳተ ግንዛቤ መኖሩን ገልጸዋል። “አሃዳዊ የሚለው ጨፍለቃ እና ጨቋኝ ተደርጎ ተወስዷል። ይህ ስህተት [ነው]” የሚሉት የፓርቲው ተወካይ፤ በዚህ ላይ በሌሎች መሪ ጥያቄዎች ላይ ውይይት መደረጉን በበጎ መልኩ ጠቅሰዋል።

በዚህ መልኩ በንዑስ ቡድኖች የሚቀርቡ ሃሳቦች የመጨረሻ ውሳኔዎች አይደሉም። ንዑስ ቡድኖቹ በውይይቶቻቸው ላይ የደረሱባቸውን የስምምነት እና የልዩነት ሃሳቦች፤ በአምስት ቦታ ለተከፈሉት እና በውስጣቸው 50 አባላት ለሚይዙ ቡድኖች ያቀርባሉ። 

እነዚህ ቡድኖች የተወያዩባቸውን የተለያዩ ንዑስ አጀንዳዎች ደግሞ 250 አባላት ላሉት ተመካካሪዎች ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። በዚህ መልኩ የተሰበሰቡት አጀንዳዎች፤ እያንዳንዳቸው 500 አባላት ለያዙ ስምንት ቡድኖች ለውሳኔ ይቀርባል። ስምንቱ ቡድኖች የደረሱበትን ውሳኔ፤ ለቀሪው 3,500 ተመካካሪዎች በማቅረብ ውሳኔ ይሰጥበታል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 16፤ 2018 በሰጡት መግለጫ፤ በጉባኤው ለተደራጁ ስምንት ቡድኖች አጀንዳዎችን በተመለከተ በምሁራን ደረጃ ገለጻ መደረጉን ተናግረዋል። የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎቹ ከነገ ጀምሮ 50 አባላት ባሉት ቡድን ተከፍለው አጀንዳዎችን በማቅረብ ውይይት እንደሚያደርጉበትም አስረድተዋል።

እስካሁን ያለው የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት “ጥሩ እየሄደ” መሆኑን ያመለከቱት ፕሮፌሰር መስፍን፤ “በ10 እና 50 አባላት ስሜታችን ወጥቶ አላለቀም። ወደ አመክንዮ የምንገባው ከ50 በላይ ስንሄድ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። ዋና ኮሚሽነሩ በዛሬው መግለጫቸው የምክክሩን አጀንዳዎች የተመለከቱ የተወሰኑ ጥያቄዎች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ እየቀረቡ መሆኑንም አንስተዋል። 

“ተሳታፊዎች ሞባይል የላቸውም። ይህም የሆነበት የራሱ ምክንያት አለው። ይሁን እንጂ አልፎ አልፎ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚደረጉ ልጥፎች አሉ። በተለይ ከዚህ ውስጥ ከሆነ ጥንቃቄ ያስፈልጋል” ሲሉ ዋና ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)