“ኢትዮጵያ ውስጥ ኮሽ ሲል የሚነቁ፤ የጠላትነት ስሜት ያላቸው ሀገራት አሉ” – ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

“ኢትዮጵያ ውስጥ ኮሽ ሲል፤ ያደፈጡ፣ የሚነቁ፣ የዘመናት ያልተቋረጠ የጠላትነት ስሜት ያላቸው ሀገራት አሉ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። ኢትዮጵያ “በቀጣይ” አዲስ ህገ መንግስት ሊኖራት እንደሚችልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥቆማ ሰጥተዋል።

አብይ ይህን ፍንጭ የሰጡት ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 8፤ 2018 ዓ.ም. በይፋ በተከፈተው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። በአዲስ አበባ በሚገኘው በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በተካሄደው በዚሁ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ የአፍሪካ ህብረት እና የኢጋድ ተወካዮች እንዲሁም የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ተገኝተዋል። 

ለአንድ ወር ያህል በሚቆየው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ፣ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ አራት ሺህ ተሳታፊዎችም የዛሬው የመክፈቻ መርሃ ግብር ታዳሚዎች ነበሩ። እነዚህ ተሳታፊዎች በቡድኖች ተከፋፈለው የተወያዩባቸውን አጀንዳዎች፤ በጉባኤው ማጠቃለያ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የሚያስረክቡ ይሆናል።

ኮሚሽኑ በምክክር ጉባኤው የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን እንዲሁም ምክረ ሀሳቦቹ በተግባር ላይ ሊውሉ የሚችሉበትን ሰነድ የሚገልጽ ሰነድ በማዘጋጀት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለአስፈጻሚ አካሉ እና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ሌሎች የመንግስት አካላት የማቅረብ ኃላፊነት በአዋጅ ተጥሎበታል። ከሀገራዊ ውይይቶች የሚገኙ ምክረ ሃሳቦችን ተግባር ላይ እንዲያውል የሚጠበቀው የኢፌዲሪ መንግስት ነው። 

የኢፌዲሪ መንግስትን በመወከል በዛሬው የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ ከሀገራዊ ጉባኤው የሚጠበቁ ጉዳዮችን እና በምክክሩ ይሳካሉ ብለው የሚጠብቋቸውን ጉዳዮች አንስተዋል። “አሁን የምንመካከረው ስለ ትላንትናው አይደለም። የትላንትን ችግር ፈተን ለነገ መልካም መሰረት ለማኖር ነው” ሲሉ አብይ ከሀገራዊ ጉባኤው የሚጠበቀውን አመልክተዋል።

አብይ በዚሁ ንግግራቸው፤ ሀገራዊ ምክክሩን ተከትሎ የህገ መንግስት ማሻሻያ ሊኖር እንደሚችል ጥቆማ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ጉዳዩ ፍንጭ የሰጡት የአሜሪካ ህገ መንግስትን ለማጽደቅ ከ239 ዓመት በፊት ተሰብስበው የነበሩ ተወካዮችን፤ ከአሁኑ ሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች ጋር በማነጻጸር ነው።

“የአሜሪካ ህገ መንግስት በ55 ሰዎች ቢሰራም ልባም ነበሩና ለምዕተ ዓመታት የሚቆይ ስራ ሰርተዋል። የእኛ አራት ሺህ ሰዎች ከእነሱ በላይ፣ ከእነሱ በተሻለ ጊዜ ይበልጥ ልባም ሆነው፣ ሁሉን ወገን፣ መላው ኢትዮጵያን የሚሰበስብ ምክክር ቢያደርጉ፤ በቀጣይ የሚኖረን ህገመንግስት ከዚህ ቀደም እንደለመድነው የመጣ ሁሉ የሚቀደው ሳይሆን፤ እኛ በአራት ሺህ ጀምረናል፣ በ10 ሺህ ምክክር ሳይደርግ፤ አንድም ሰው መቀየር አይችልም ማለት ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተናግረዋል። 

የመንግስት አደረጃጀት ስርዓት እና የህገ መንግስት ማሻሻያ በሀገራዊ ምክክር ላይ እንዲቀርቡ በአጀንዳነት የተያዙ ጉዳዮች መካከል እንዳሉበት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባለፈው ሰኔ ወር አጋማሽ አስታውቆ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከሳምንት በፊት በፓርላማ ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ፤ እርሳቸው የሚመሩት ገዢው ብልጽግና ፓርቲ “በስልጣን ላይ ያለ መንግስት ለሁለት የስልጣን ዘመን ብቻ እንዲቆይ” የሚያስችል አጀንዳ ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ማቅረቡን ገልጸው ነበር። 

አብይ በዛሬው ንግግራቸውም “ኢትዮጵያ በዚህ ጉባኤ መሰረት ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ባህልን ታጸናለች” ሲሉ ተደምጠዋል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ “በኃይለ ቃል ጀምሮ በኃይል እርምጃ የሚደመደም” እንደሆነ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ይህንን ስብራት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ማቆም ይገባናል” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በጉባኤ መክፈቻ ንግግራቸው፤ ለወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ምላሽ የመሰሉ ገለጻዎችንም ተጠቅመዋል። “በውስጣችን ያሉ ችግሮች እኛው ጀምረን፣ እኛው የምንጨርሳቸው ብቻ አይደሉም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በኢትዮጵያ ያሉ ችግሮችን ለማባባስ “የሚያንዣብቡ” ያሏቸውን በስም ያልጠቀሷቸውን ጠላቶች ተጠያቂ አድርገዋል።    

“ኢትዮጵያ ውስጥ ኮሽ ሲል፤ ያደፈጡ፣ የሚነቁ፣ የዘመናት ያልተቋረጠ የጠላትነት ስሜት ያላቸው ሀገራት አሉ። የኢትዮጵያን ታሪክ ከጉንደት እስከ ጉራዕ፣ ከአድዋ እስከ ማይጨው፣ ከካራማራ እስከ ባድመ እያንዳንዱን ብትፈትሹት፤ ስንገነባ ያደፈጡ፣ ስንጨቃጨቅ ዕድል ጊዜ ጠብቀው፣ ጣልቃ ሽብልቅ እየገቡ መሻቶቻችንን እንዳንከውን የሚያደርጉ ኃይሎች አሉ” ብለዋል አብይ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ በማሳያነት የጠቀሱት፤ ኢትዮጵያ “ቀይ ባህርን ያጣችበት” ያሉትን አካሄድ ነው። አካሄዱን “እኩይ ታሪካዊ ክስተት” ሲሉ የጠሩት አብይ፤ ለዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ አለ ያሉትን “ስንፍና” ተጠያቂ አድርገዋል።    

“ሁልጊዜም ጥቅማችንን አሳልፈን የምንሰጠው፤ ስንገነባ ያልነበሩ፣ ስንሻኮት፣ ስንጣላ የሚያንዣብቡ አሞሮች ስላሉ ነው። አሞራ ሲታረድ ይመጣል፣ ሲገነባ የለም”

“ኢትዮጵያ ለሺህ ዘመናት ያስተዳደረችውን፣ በባለቤትነት የያዘችውን፣ ለራሷም ለከባቢውም መጠቀሚያ ያኖረችውን ቀይ ባህር፤ ያልተመረጠ መንግስት፣ ያልተወያየ መንግስት፣ በሸፍጥ ኢትዮጵያን የጂኦግራፊ እስረኛ እንዲያደርግ ያደረገበት ዋና ምክንያት በውስጥ ያለን ስንፍና እንጂ የኢትዮጵያ መሻትና ጥቅም ማስቆም የሚችል ኃይል ስለነበረ፣ ስላለ፣ ስለሚኖር አይደለም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀይ ባህርን ጉዳይ አብራርተዋል።

“ሁልጊዜም ጥቅማችንን አሳልፈን የምንሰጠው፤ ስንገነባ ያልነበሩ፣ ስንሻኮት፣ ስንጣላ የሚያንዣብቡ አሞሮች ስላሉ ነው። አሞራ ሲታረድ ይመጣል፣ ሲገነባ የለም። ህዳሴን ስንገነባ እኛ ጋር ያልነበሩ፣ ከተሞቻችን ሲያሸበርቁ እኛ ጋር ያልነበሩ፣ ልማት ስንጀምር እኛ ጋር ያልነበሩ እርስ በእርስ ስንጨቃጨቅ ግብ ከየት መጡ ሳይባሉ፣ ጥይት ሲያቀብሉ፣ ብር ሲያቀብሉ፣ በሚዲያ ፕሮፖጋንዳ ሲያደርጉ ይታያል” ሲሉም አብይ አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)