የሙዚቃ አልበሞች ያላደመቁት የዘመን መለወጫ ዋዜማ

በአለምፀሀይ የኔዓለም

በሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ አዲስ ዓመት ሲቃረብ የሚጠበቅ አንድ ሁነት አለ – የአዳዲስ አልበሞች ለገበያ መቅረብ። በጣት በሚቆጠሩት የጳጉሜ ቀናት ለምርጫ እስኪያስቸግር ድረስ የሙዚቃ አልበሞች ተደራርበው የሚወጡበት ነበር።  

የሙዚቃ ገበያው እንደድሮው አይደለም በተባለለት ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ጊዜ እንኳ ከሐመልማል አባተ እስከ አቡሽ ዘለቀ፣ ከዘሩባቤል ሞላ እስከ ፀደንያ ብርሀኑ (ጸዲ) ያሉ ድምጻውያን አልበሞቻቸውን ለአድማጭ አድርሰዋል። ዘንድሮ ይህም ጠፍቷል። ምክንያቱ ደግሞ የኮሮና ወረርሽኝ ነው።  

የ2013 አዲስ ዓመት ማድመቂያ ይሆናል ተብሎ በአድናቂዎቹ ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የአብነት አጎናፍር አዲስ አልበም ነበር። የአድናቂዎቹ ጥበቃ አለምክንያት የመጣ አይደለም። የድምጻዊው አዲስ አልበም ሙሉ ስራው መጠናቀቁ በመገናኛ ብዙሃን ሲወራ ከመክረሙ ባሻገር በራሱ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይም ይህንኑ የሚያጠናክር መረጃ ለተከታታዮቹ አጋርቶ ነበር። 

አብነት ከሶስት ሳምንት በፊት በፌስ ቡክ ገጹ ባሰፈረው መልዕክት፤ አራተኛ አልበሙ በተለያዩ ምክንያቶች መዘግየቱን ጠቅሶ በቅርቡ ግን ለተከታዩቹ እና ደጋፊዎቹ እንደሚደርስ በእርግጠኛነት አስታውቆ ነበር። ለመዳረሻ በሚልም በአልበሙ ውስጥ ካካተታቸው ዘፈኖች ውስጥ “የጥሪ ደወል” የተሰኘው ስራውን ከእነ ሙዚቃ ቪዲዮው ለዕይታ አብቅቷል። ከሳምንት በኋላ ግን በአዲስ አልበም መምጣቱ ቀርቶ “ሆ ብዬ መጣሁ” የተሰኘ ሌላ ነጠላ ዜማ ለቅቋል። 

አልበሙ ለአዲስ አመት በዓል እንደማይወጣ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያረጋገጠው ድምጻዊ አብነት፤ ለገበያ የሚውልበት ጊዜ ላልተወሰነ ጊዜ ማራዘሙን ተናግሯል። አልበሙን እንዳሰበው ለአድማጭ እንዳያደርስ እክል የፈጠረበት የኮሮና ወረርሽኝ እንደሆነም ገልጿል። “ሲዲ መሸጡ ንክኪ ስላለውና አዲስ ሲስተም እስኪዘረጋ ደግሞ በነበረው መቀጠል የነበረብን ቢሆንም፤ ይህ ደግሞ ወረርሽኙን ሊያባብስ ስለሚችል ማራዘሙ ግድ ሆኖብናል” ሲል ድምጻዊው ምክንያቱን አስረድቷል።

“ሲዲ መሸጡ ንክኪ ስላለውና አዲስ ሲስተም እስኪዘረጋ ደግሞ በነበረው መቀጠል የነበረብን ቢሆንም፤ ይህ ደግሞ ወረርሽኙን ሊያባብስ ስለሚችል ማራዘሙ ግድ ሆኖብናል”

ድምጻዊ አብነት አጎናፍር

ሙዚቃን ከሲዲ እና ካሴት ሽያጭ በማውጣት ወደ ኦንላይን ግብይት ለማምጣት እየጣረ ያለው “አውታር መልቲ ሚዲያ” የአብነት አይነት ስጋት የገባው አይመልስም። ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በቅርቡ አድማጭ ጆሮ ዘንድ የሚደርሱ አዳዲስ ነጠላ ዜማዎችን እና አልበሞችን እያስተዋወቀ ይገባል። በ“አውታር” የሙዚቃ ሽያጭ መተግበሪያ ላይ ብቻ ለገበያ ይቀርባሉ የተባሉ ሁለት አልበሞች በመሰሉ ፋንታሁን እና በኃይለሚካኤል ጌትነት (ኃይሌ ሩትስ) የተሰሩ ናቸው። 

በታዳጊነቷ ሙዚቃ የጀመረችው መሰሉ ከዚህ ቀደም አንድ አልበምና ከተለያዩ ሙዚቀኞች ጋር በጋራ በመሆን የሙዚቃ ስብስብ ያላት ሲሆን ሁለት ነጠላ ዜማዎችም አሏት። አዲሱ አልበሟን ያቀናበረው በዚህ አመት ህይወቱ ያለፈው የሙዚቃ አቀናባሪ፤ የግጥም እና ዜማ ደራሲ ኤልያስ መልካ ነው። ኤልያስ በህይወቱ የመጨረሻ ጊዜያት ከሰራቸው አልበሞች አንዱ እንደሆነ በተነገረለት በዚህ አልበም ከቅንብር በሻገርም በግጥም እና ዜማ ሙሉ ተሳትፎ ማድረጉን “አውታር መልቲ ሚዲያ” አስታውቋል።

ከስምንት ዓመት ቆይታ በኋላ በአዲስ አልበም እየመጣ ካለው ከኃይሌ ሩትስ አዳዲስ ስራዎች ጀርባም ኤልያስ መልካ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተነግሯል። የኤልያስ የቅርብ ጓደኛ የሆነው ኃይሌ ሩትስ “ቺጌ” የተሰኘውን የመጀመሪያ አልበሙንም የሰራው ከሁለገቡ የሙዚቃ ሰው ጋር ነበር። 

ኤልያስ እና ሃይሌ ሩትስ፤ ከሌሎቹ የሙዚቃ ባለሙያዎች ዮሐንስ በቀለ (ጆኒ ራጋ) እና ዳዊት ንጉሴ ጋር በጥምረት ያቋቋሙት “አውታር መልቲ ሚዲያ” የኮሮና ወረርሽኝ አደጋ የጋረጠበትን የሙዚቃ ገበያ በዚህ መልኩ ለመታደግ ቢፍጨረጨርም የተከተለው የሽያጭ መንገድ ግን ነባር የሙዚቃ አሳታሚዎች እና አከፋፋዮች ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል። በሙዚቃ አሳታሚነት ከ40 ዓመታት በላይ የሰሩት አቶ አብዲ መሀመድ “አልበሞች በድረ ገፅ ከተሸጡ በኋላ ወደ ሲዲ እና ካሴት ሽያጭ የሚያመሩበት መንገድ መፈጠሩ በሙዚቃ ቤቶች ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ይገኛል” ይላሉ።  

“አልበሞቹን በሲዲ ለመውሰድ የሚመጡት በዕድሜ የገፉ፣ ሲዲዎቹን ለታሪክ ማስቀመጥ የሚፈልጉ፣ አልያም አልበሞቹን በስጦታ ለማበርከት የሚፈልጉ ሰዎች ብቻ ናቸው” ሲሉ አቶ አብዲ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።  

“ፕላቲንየም ሪከርድስ” በተሰኘው የሙዚቃ አሳታሚ ድርጅታቸው የአረጋኸኝ ወራሽ፣ ኩኩ ሰብስቤ፣ መሐሙድ አህመድ እና መሰል አንጋፋ ድምፃውያንን አልበም ሲያሳትሙ የቆዩት አቶ አብዲ፤ ከኦንላይን የሙዚቃ ሽያጭ በተጨማሪ የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባቸዋል። የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ እንደሌላው ጊዜ አዲስ ነጠላ ዜማም ሆነ አልበም እነርሱ ጋር አለመምጣቱን የሚገልጹት የሙዚቃ አሳታሚው የስራ ዘርፋቸውን ለመቀየር እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ገልጸዋል። 

“እኔ ከማውቃቸው የሙዚቃ አሳታሚዎች ውስጥ ከ10 በላይ የሚሆኑት በዚሁ ወረርሽኝ ምክንያት ስራው ስለተቀዛቀዘ ዘግተዋል። እኔም ይህንን ዘግቼ ሌላ ስራ የመጀመር እቅድ ነው ያለኝ”

አብዲ መሀመድ- የፕላቲንየም ሪከርድስ ባለቤት

“እኔ ከማውቃቸው የሙዚቃ አሳታሚዎች ውስጥ ከ10 በላይ የሚሆኑት በዚሁ ወረርሽኝ ምክንያት ስራው ስለተቀዛቀዘ ዘግተዋል” የሚሉት የ“ፕላቲንየም ሪከርድስ” ባለቤት “እኔም ይህንን ዘግቼ ሌላ ስራ የመጀመር እቅድ ነው ያለኝ” ሲሉ የኮሮና ወረርሽኝ በሙዚቃ ኢንዱስትሪው ላይ ያደረሰውን ጉዳት ያስረዳሉ። 

የሙዚቃ አሳታሚነት ስራዎች ከቀየሩ ግለሰቦች መካከል አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ፅጌ በላቸው ስራው “በኮሮና ምክንያት እጅግ በመቀዛቀዙ እኛም ኪሳራ ውስጥ ገብተናል” ይላሉ።“ጥሩ ጊዜ እስኪመጣ የማሳተሙን ስራ ትቼ ወደ ሌላ የስራ ዘርፍ ተዘዋውሬያለሁ” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ፒያሳ አራዳ ህንፃ ስር የሚገኘው ማስተር ሳውንድ የተሰኘው የሙዚቃ አሳታሚ ድርጅታቸው በአሁኑ ወቅት የሴቶች ልብስ መሸጫ ሆኗል። 

ሙዚቃዎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራውና “የወዝ ወዝ አዲስ” የራዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ እና አቅራቢው ኪንግስተን ኃይሉ (ዲጄ ኪንግስተን) የኮሮና ወረርሽኝ የሙዚቃውን እንቅስቃሴ በእጅጉ እንደጎዳው ይናገራል። አልበማቸውን ሰርተው የጨረሱ ድምጻውያን “ጥሩ ጊዜ እስኪመጣ ይዘው ቁጭ ብለዋል” የሚለው ዲጄ ኪንግስተን በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት እና በአገሪቱ ላይ ባጋጠመው አለመረጋጋት ምክንያት ህዝቡ ሙዚቃ የመስማት ፍላጎቱ በመቀነሱ ምክንያት የሙዚቀኞች ገቢ መቀነሱን ያብራራል።  

አብዛኞቹ ሙዚቀኞች አዲስ ነገር ለማውጣት አዲስ አመትን ከሌሎቹ በዓላት በተለየ መልኩ እንደሚመርጡት የሚናገረው ዲጄ ኪንግስተን የዚህም ምክንያቱ “ሁሉም በአንድነት መንፈስ ሳይከፋፈል የሚያከብረው በዓል በመሆኑ ነው” ይላል። ህዝቡ በበዓል ወቅት አዲስ ሙዚቃም ገዝቶ የመስማት ልምድ እንዳለው የሚጠቅሰው ዲጄ ኪንግስተን በዚያን ወቅት የሚኖራቸው “ጥሩ መንፈስ”ም ጊዜውን ተመራጭ እንደሚያደርገው ያብራራል። በዘንድሮው የአዲስ አመት በዓል ግን የሙዚቃው ዘርፍ እንቅስቃሴ “በጣም ተቀዛቅዟል” ሲል ቀደም ሲል ከነበሩ ጊዜያት ጋር አንጻጽሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)