የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት በኢትዮጵያ ወቅታዊ የደህንነትና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ተወያየ

በሐይማኖት አሸናፊ

የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት በኢትዮጵያ ወቅታዊ የደህንነት እና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ረቡዕ ጳጉሜ 4፤ 2012 አስቸኳይ ስብሰባ አካሄደ። ምክር ቤቱ ወቅታዊ የደህንነት ጉዳዮችን በዝርዝር ከተመለከተ በኋላ ስጋቶችን በተቀናጀ መልኩ መግታት የሚቻልበትን አቅጣጫ ማስቀመጡን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል። 

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት የሚመራው ይህ ምክር ቤት በዛሬ ስብሰባው በሀገሪቱ ላይ “የተቃጡ፣ የከሸፉ እና ጉዳት ያደረሱ የብሔራዊ ደህንነት ስጋቶችን በዝርዝር ዳስሷል” ተብሏል። “የሃገርን ሉዓላዊነት፣ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅና የህግ የበላይነትን ለማስከበር መከላከያን ጨምሮ ሁሉም የደህንነትና ጸጥታ ተቋማት እስካሁን እያደረጉት ያለውን ጥረትና መስዋዕትነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ምክር ቤቱ አረጋግጧል” ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ዛሬ ረፋዱን ባወጣው አጭር መግለጫ አመልክቷል።    

በህገ መንግስቱ አንቀፅ 55(1) መሰረት፣ በ1994 ዓ.ም በወጣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ የተቋቋመው የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት፤ የሃገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት ባልተጠበቀ ሁኔታ ከሚከሰቱም ሆነ አመጣጣቸው ሊታይ ከሚችል አደጋዎች እና ፈተናዎች በመጠበቅ ረገድ ተጨማሪ ዋስትና ሊያስገኝ በሚችል ለመቀየስ ታስቦ የተዋቀረ ነው። ምክር ቤቱ በዋናነት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማማከር የተቋቋመ ቢሆንም ይህ እንደተጠበቀ ግን ሌሎች ሶስት ተግባራን እንዲያከናውን በህግ ስልጣን ተሰጥቶታል። 

የመጀመሪያው ለሃገሪቱ ብሔራዊ የደህንነት ስጋት ምንጭ የሆኑ ሁኔታዎችን በመገምገም ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች ሃሳብ ማቅረብ ሲሆን ሁለተኛው ብሔራዊ ደህንነት ለማስጠበቅ የሚወሰዱ እርምጃዎችን የሚመለከቱ የአፈፃፀም መመሪያዎችን ማመንጨት ነው። ከዚህ በተጨማሪም ምክር ቤቱ ብሔራዊ ደህንነትን የሚመለከቱ ማናቸውም ጉዳይ ላይ እንደሚመክር በማቋቋሚያ ደንቡ ላይ ተቀምጧል። ምክር ቤቱ በህግ የተደነገገ ቋሚ የጉባኤ ማካሄጃ ሰሌዳ የሌለው ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማንኛውም ጊዜ ሊጠሩት እንደሚችሉም የተቋቋመበት ደንብ ያትታል። 

ፎቶዎች፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

ሰባት ቋሚ አባላት ያሉት የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ምክትላቸውን ጨምሮ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማጆር ሹሙን፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተሩን እንደዚሁም የውጭ ጉዳይ እና የመከላከያ ሚኒስትሩን ያቀፈ ነው። ከእነርሱ በተጨማሪም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የምክር ቤቱ አባል እና ጸሃፊ በመሆን ተካትተዋል።

በዛሬው የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ ምክትላቸው ደመቀ መኮንን፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ጄነራል አደም መሐመድ እና ምክትላቸው ጄነራል ብርሃኑ ጁላ እንዲሁም የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ደመላሽ ገብረሚካኤል መገኘታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባሰራጨቸው ፎቶግራፎች ታይቷል። በስብሰባው ላይ የምክር ቤቱ አባል የሆኑት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገዱ አንዳርጋቸው እና አዲሱ የመከላከያ ሚኒስትር ቀንዓ ያደታ መሳተፋቸውን ከፎቶግራፎቹ መረዳት ተችሏል።

የምክር ቤቱ አባል ያልሆኑት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንደሻው ጣሰው የዛሬውን ስብሰባው መታደማቸውም በፎቶግራፎቹ ተስተውሏል። በብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ማቋቋሚያ ደንብ ላይ ከቋሚ የምክር ቤቱ አባላት በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጨማሪ አባላትን የመሰየም ብሎም ማንኛውም ሰው ሙያዊ ምክሩን ለምክር ቤቱ እንዲለግስ በአስረጂነት መጋበዝ እንደሚችሉ ተቀምጧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)