ለጃዋር መሐመድ የሳተላይት መሳሪያ በመግጠም የተከሰሱ ባለሙያ ዋስትና ተፈቀደላቸው

በተስፋለም ወልደየስ

በአቶ ጃዋር መሐመድ መኖሪያ ቤት ህገ ወጥ የሳተላይት መሳሪያ በመግጠም የተከሰሱት አቶ ሚሻ አደም ዋስትና ተፈቀደላቸው። ተከሳሹ የ20 ሺህ ብር ዋስትና በማስያዝ በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ዛሬ ውሳኔ የሰጠው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው። 

የአቶ ሚሻን ክስ እየተመለከተ የሚገኘው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 20ኛ ወንጀል ችሎት ለዛሬ ረቡዕ ጳጉሜ 4፤ 2012 ቀጠሮ የሰጠው የተከሳሹ ጠበቆች ባቀረቡት ዋስትና ላይ ውሳኔ ለመስጠት ነበር። የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ “ለተከሳሹ የዋስትና መብት ሊፈቀድ አይገባም” በሚል ሶስት መከራከሪያ ነጥቦች እንዳነሳ ጠበቃ ከዲር ቡሎ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

የመጀመሪያው ተከሳሹ ያላቸውን የአሜሪካ ዜግነት የተመለከተ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አቶ ሚሻ “ቋሚ አድራሻ የላቸውም” በሚል የቀረበ እንደሆነ ጠበቃው ገልጸዋል። ሶስተኛው የአቃቤ ህግ መከራከሪያ ተከሳሹ በዋስትና ቢወጡ የኢንጀነሪንግ ሙያቸውን ተጠቅመው በምስክሮች ላይ ጫና ሊፈጥሩ ይችላሉ የሚል እንደሆነም ጠቁመዋል። አሁንም ቢሆን በምስክሮች ላይ ማስፈራሪያ እየደረሰ መሆኑን አቃቤ ህግ ለችሎት ማስረዳቱንም አክለዋል። 

የአቃቤ ህግን መከራከሪያ የተቃወሙት ጠበቆች በበኩላቸው ተከሳሹ የተጠረጠሩበት ወንጀል ከ10 እስከ 20 ዓመት ብቻ የሚያስቀጣ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የዋስትና መብት ሊከለክልበት የሚችለውን አግባብ ያሟላ አይደለም በሚል ተከራክረዋል። የዋስትና መብት የሚከለከለው አንድ ተከሳሽ የተጠረጠረበት ወንጀል ከ15 ዓመት በላይ የሚያስቀጣ ሲሆን እና ወንጀሉም ሞትን ያስከተለ ሲሆን ነው። 

አቶ ሚሻ በክሳቸው ላይ የተጠቀሰባቸው የቴሌኮም ማጭበርበር አዋጅ አንቀጽ ዘጠኝ “ህገ ወጥ የቴሌኮም ኦፕሬተርን ስለሚመለከቱ ወንጀሎች” የሚያትት ነው። በዚሁ አንቀጽ “ማንኛውም ሰው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ድርጅቱ ከዘረጋው የቴሌኮም መሰረተ ልማት ውጪ ማንኛውንም የቴሌኮም መሰረተ ልማት የዘረጋ እንደሆነ ከ10 እሰከ 20 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ ይደነግጋል። ከዚህም በተጨማሪ “አገልግሎቱን በሰጠበት ጊዜ ውስጥ ሊያገኝ ይችላል ተብሎ የሚገመተውን ገቢ አስር እጥፍ የሚሆን መቀጮ ይቀጣል” ሲል አዋጁ ያስቀምጣል።

የፌደራል አቃቤ ህግ ላይ ያቀረበው ክስ፤ ተከሳሹ “ኢትዮ ቴሌኮም የዘረጋውን መሰረተ ልማት ወደ ጎን በመተው፤ የቴሌኮም መሳሪያዎችን ከአሜሪካን ሀገር በማስመጣት በአቶ ጃዋር መሐመድ መኖሪያ ቤት ዘርግተዋል” ሲል ይወነጅላል። ተከሳሹ ዘርግተዋቸዋል ከተባሉ መሳሪያዎች ውስጥ በግለሰብ ደረጃ መያዝ የማይፈቀደውን ሮኬት ፕሪዝም ጂን 2 ሲስተም፤ ዩቢኪውቲ ኤጅ ራውተር እንዲሁም ከሳተላይት የሚመጣውን ሲግናል ለመሰብሰብና ቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ቪሳት ዲሽ በክስ ሰነዱ ላይ ተጠቅሰዋል። 

በዛሬው የችሎት ውሎ የአቶ ሚሻን ዜግነት በተመለከተ ለቀረበው መከራከሪያ ጠበቆች የሰጡት ምላሽ፤ “የአንድ ሰው ዜግነት ለዋስትና መገደብ ምክንያት ሊሆን አይገባውም” የሚል እንደነበር አቶ ከዲር ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት በወንጀል ተጠርጥረው ለተከሰሱ ተጠርጣሪዎች ዋስትና እንደሚፈቅድ ለፍርድ ቤቱ ያስታወሱት ጠበቆች “አቃቤ ህግ ከህግ አውጪ በላይ ለህግ አሳቢ ሊሆን አይገባም” ሲሉ መከራከራቸውን አቶ ከዲር ተናግረዋል። 

ጠበቆቹ፤ ተከሳሹ ለሁለት ዓመት ያህል በኢትዮጵያ መኖራቸውን እና ፖስፖርታቸውም በፖሊስ እጅ እንደሚገኝ በማንሳት በዚህ ምክንያት ዋስትና መከልከል እንደማይገባው መከራከራቸውን ተናግረዋል። አቃቤ ህግ ባቀረበው የክስ ሰነድ ላይ የተከሳሹ አድራሻ ከእነ ክፍለ ከተማው እና ቤት ቁጥሩ ተቀምጦ ሳለ የአድራሻው ጉዳይ በመከራከሪያነት መቅረቡ “አግባብ አይደለም” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸውንም ጠቅሰዋል። 

በዘጠኝ ዓመቱ ከሀገሩ የወጣው እና ለረጅም ጊዜያት በውጭ ሀገር የቆየው ሚሻ፤ ምስክሮችን አግኝቶ ጫና የሚያስፈራራበት ስልጣንም ሆነ እውቂያ እንደሌለው ጠበቆቹ በተጨማሪ መከራከሪያነት አንስተዋል። “አቃቤ ህግ ያቀረበው በተለይ ግለሰቡ ቢወጣ በሙያም በተለያዩ ነገሮች ጫና ያፈጥራል የተባለው አግባብ አይደለም። ምክንያቱም ሙያ የእውቀት እና የክብር መለኪያ እንጂ የሰው መብት መገደቢያ ምክንያት ተደርጎ ህጉ አላስቀመጠውም” የሚል ክርክር ለፍርድ ቤቱ ማቅረባቸውን ጠበቃ ከዲር አብራርተዋል። 

አቃቤ ህግ ያቀረባቸው መከራከሪያዎች “ደንበኛችንን አስሮ ለማስቀመጥ ብቻ ያቀረባቸው እና ተቀባይነት የሌላቸው የህግ ምክንያቶች ስለሆኑ ውድቅ ሊደረጉ ይገባል የሚል ምክንያት ነው ያቀረብነው”

ጠበቃ ከዲር ቡሎ

አቃቤ ህግ ያቀረባቸው መከራከሪያዎች “ደንበኛችንን አስሮ ለማስቀመጥ ብቻ ያቀረባቸው እና ተቀባይነት የሌላቸው የህግ ምክንያቶች ስለሆኑ ውድቅ ሊደረጉ ይገባል የሚል ምክንያት ነው ያቀረብነው” ሲሉ ጠበቃው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአቃቤ ህግን መከራከሪያ ውድቅ በማድረግ ተከሳሹ በ20 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈታ ትዕዛዝ መስጠቱን አቶ ከዲር ገልጸዋል። 

ፍርድ ቤቱ፤ አቃቤ ህግ በአቶ ሚሻ ላይ የሚመሰክሩ ምስክሮች ማንነት እንዳይገለጽ ላቀረበው አቤቱታ፤ የተከሳሽ ጠበቆች የሚሰጡትን አስተያየት ለማድመጥ ለመስከረም 6፤ 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት የዛሬውን የችሎት ውሎ አጠናቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)