የቴሌኮም ጨረታ ሰነድ መቀበያ ቀነ-ገደብ ተራዘመ

ወደ ኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያ ለመግባት የሚወዳደሩ ኩባንያዎች የጨረታ ሰነድ የሚያስረክቡበት ቀነ-ገደብ ለተጨማሪ ቀናት ተራዘመ። ቀነ ገደቡ የተራዘመው ኢትዮጵያ ለውድድር ካቀረበቻቸው ሁለት የቴሌኮም አገልግሎት ማቅረቢያ ፈቃዶች አንዱን በእጃቸው ለማስገባት የሚወዳደሩ ኩባንያዎች ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት መሆኑን የኢትዮጵያ ኮሚዩኒኬሽን ባለሥልጣን ዛሬ አስታውቋል።

ባለስልጣኑ ለሰነድ ማስረከቢያው የሰጠው ቀነ-ገደብ የመጨረሻ ቀን ዛሬ ሰኞ መጋቢት 27 የነበረ ቢሆንም ለሁለተኛ ጊዜ መራዘሙ ግድ ሆኗል። ተጫራቾች ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸው የጠየቁት “የኮቪድ ወረርሽኝ በፈጠረው የገበያ ከባቢ ምክንያት” እንደሆነ ባለሥልጣኑ ዛሬ ባሰራጨው መረጃ ገልጿል። በጥያቄያቸው መሰረትም የመወዳደሪያ ሰነድ ማስገቢያው ቀን እስከ ሚያዝያ 18፤ 2013 ዓ.ም. መራዘሙን አመልክቷል።  

የኢትዮጵያ መንግሥት ለሁለት የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎች ፈቃድ ለመስጠት በያዘው ዕቅድ ጨረታ ያወጣው ባለፈው ህዳር 18፤ 2013 ነበር። ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን ተዘግቶ ወደቆየው የኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያ የሚያስገባው ይኸው ጨረታ፤ በመንግሥት “አገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ” ከተካተቱ አበይት እርምጃዎች ውስጥ አንዱ ነው። 

የውጭ ኩባንያዎች ለሁለቱ የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃዶች ፍላጎታቸውን የሚያሳውቁበት ሂደት በኢትዮጵያ በኩል ይፋ የተደረገው ግንቦት 13፤ 2012 ዓ.ም. ነበር። ይህንን ተከትሎም 12 የውጭ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ለመግባት ፍላጎታቸውን አሳይተዋል። 

የኢትዮጵያ ኮሚዩኒኬሽን ባለስልጣን በወቅቱ ባወጣው መረጃ እንዳለው፤ የፍላጎት መግለጫቸውን ካቀረቡት ውስጥ ዘጠኙ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ናቸው። በቴሌኮም ኦፕሬተርነት ዘርፍ ያልተሰማሩ ሁለት ኩባንያዎች በተመሳሳይ ፍላጎታቸውን በሰነድ ማቅረባቸውንም ባለስልጣኑ ገልጾ ነበር። በአንድ ኩባንያ ያቀረበው ሰነድ “ተሟልቶ ያልቀረበ” መሆኑም በጊዜው ተጠቅሷል። 

ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ለመግባት ከሚሹት ግዙፍ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪዎች መካከል የቮዳፎን፣ ቮዳኮም እና ሳፋሪኮም ኩባንያዎች ጥምረት ይገኝበታል። ሶስት ኩባንያዎች ሰነዳቸውን ያስገቡት “ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ” በሚል ጥምረት ስር ነው። በቮዳፎን የሚመራው ይኸው ዓለም አቀፍ ትብብር ጨረታውን አሸንፎ አንድ ፈቃድ በእጁ ካስገባ “ለንድፍ ግንባታ እና ሥራ ማስኬጃ” ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (DFC) የ500 ሚሊዮን ዶላር ብድር ተፈቅዶለታል። 

ከዚህ ጥምረት በተጨማሪ፤ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ኢቲሳላት፣ ከማዳጋስካር አክሲያን፣ ከደቡብ አፍሪካ ኤም.ቲ.ኤን፣ ከፈረንሳይ ኦሬንጅ የተባሉት ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን ገልጸዋል። ሳውዲ ቴሌኮም ኩባንያ፣ ቴሌኮም ደቡብ አፍሪካ፣ ሊኪውድ ቴሌኮም፣ ስኔይል ሞባይል እና ሌሎች ሁለት የቴሌኮም ኦፕሬተር ያልሆኑ ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን ካሳዩት ዝርዝር ተካተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)