ጠቅላይ ፍርድ ቤት በእነ እስክንድር ነጋ እና በእነ ጃዋር መሐመድ መዝገቦች የቀረቡለትን ይግባኞች ለመመልከት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ

በቅድስት ሙላቱ   

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የምስክር አሰማም ሂደትን በተመለከተ፤ በእነ እስክንድር ነጋ እና በእነ ጃዋር መሐመድ መዝገቦች ከጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የቀረቡለትን ይግባኞች ለመመልከት ለሚያዝያ 15፤ 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ። ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠው በሁለቱም መዝገብ ያሉ ተከሳሶች ጠበቆች ባቀረቧቸው ጥያቄዎች ነው።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ይግባኝ ችሎት በእነ እስክንድር መዝገብ ለዛሬ ቀጥሮ የነበረው፤ “የዐቃቤ ህግ ምስክሮች አሰማም ሂደት በግልጽ ችሎት ይካሄድ” በሚል በቀረበለት ይግባኝ ላይ ሁለቱንም ወገኖች ለማከራከር ነበር። ክርክሩ ለዛሬ ይግባኝ የተባለው የስር ፍርድ ቤት የምስክሮች አሰማም ሂደት በግልጽ ችሎት ይሁን ብሎ መወሰኑን ምክንያት በማድረግ ሲሆን፤ ጉዳዩ በይግባኝ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲደርስ ፍርድ ቤቱ “ጊዜያዊ ችሎት ላይ ይግባኝ አይባልም” በማለት ውድቅ አድርጎት ነበር። 

ጉዳዮ ወደ ሰበር ሰሚ ከሄደ በኋላ ግን ችሎቱ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲመለስ እና ክርክር እንዲደረግ በመወሰኑ ነበር የይግባኝ ሰሚ ችሎቱ ጉዳዩ ለመመልከት ለዛሬ የቀጠረው። የዛሬውን ክርክር ተከሳሾች ባሉበት ማረሚያ ቤት ሆነው በፕላዝማ ቴሌቪዥን እንዲከታተሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም፤ የፕላዝማ ግንኙነቱ ሳይሰራ ቀርቷል። 

ይህንን ተከትሎም የእነ እስክንድር ጠበቃ “ተከሳሾች በሌሉበት መከራከር” አንችልም በማለቱ፤ የይግባኝ ችሎቱ ክርክሩን ለማካሄድ ለሚቀጥለው ሳምንት አርብ ሚያዝያ 15 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። ችሎቱ በተመሳሳይ ሁኔታ በእነ ጃዋር መሐመድ መዝገብ ከዐቃቤ ህግ የቀረበለትን ይግባኝ በዛሬው ዕለት ለመመልከት ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም የይግባኝ ክርክሩን ለሌላ ጊዜ አስተላልፎታል። 

ዐቃቤ ህግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያለው፤ የእነ ጃዋርን ክስ እየተመለከተ ያለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በምስክር አሰማም ሂደት ላይ የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ነው። ይግባኝ የቀረበበት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ፤ ዐቃቤ ህግ በእነ አቶ ጃዋር ላይ የቆጠራቸው 146 ምስክሮች በግልጽ ችሎት እንዲያሰማ ትዕዛዝ የተሰጠበት ነበር። 

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይህ ውሳኔ እንዳይፈጸም ባለፈው አርብ እግድ አስተላልፏል። ፍርድ ቤቱ በሁለቱም ወገኖች የሚቀርቡ ክርክሮችን ለመስማት ለዛሬ ቀጠሮ ቢሰጥም፤ የተከሳሽ ጠበቆች እግዱ እንዳልደረሳቸው ትላንት ተሰይሞ ለነበረውና የእነ ጃዋርን መደበኛ ክስ ለሚመለከተው ችሎት ገልጸው ነበር። 

በዛሬው የጠቅላይ ፍርድ ቤት የችሎት ውሎ ደግሞ፤ ጠበቆች ለደንበኞቻቸው መጥሪያ እንዳልደረሳቸው አስረድተዋል። ተከሳሾቹ መጥሪያው ደርሷቸው ክርክሩን ይከታተሉ ዘንድ ጠበቆቹ ተለዋጭ ቀጠሮ በመጠየቃቸው፤ ችሎቱም ይህንኑ ተቀብሎ ለሚያዝያ 15 ቀጥሯል።

በዛሬው ችሎት የእነ እስክንድርም ሆነ የእነጃዋር ጠበቆች፤ ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች በፕላዝማ እንዲከታተሉ ማድረጉን ተቃውመዋል። ጠበቆቹ አካሄዱ “የፍርድ ስርዓቱንም ያስተጓጉላል” የሚል ተቃውሞ ቢያቀርቡም፤ ፍርድ ቤቱ ግን አሁን ባለው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በአካል እንዲገኙ ማድረግ እንደማይችል ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)