አሜሪካ በምሥራቅ አፍሪካ አሳሳቢ ላለቻቸው ችግሮች መፍትሔ የሚያፈላልጉ አዲስ ልዩ ልዑክ ሾመች

አሜሪካ፤ የትግራይ ግጭት እና የታላቁ የህዳሴ ግድብ ውዝግብን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ አሳሳቢ ላለቻቸው ወቅታዊ ችግሮች መፍትሔ የማፈላለግ ኃላፊነት የተጣለባቸው አዲስ ልዩ ልዑክ ሾመች። የ62 አመቱ ጄፍሪ ፌልትማን የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ሆነው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን መሾማቸውን ዛሬ አርብ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። 

አዲሱ ልዩ መልዕክተኛ ከሚያተኩሩባቸው ጉዳዮች መካከል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን “በተለይ አሳሳቢ” ያሏቸው “የትግራይ ግጭትን ጨምሮ በቅጡ ያልረጋ የኢትዮጵያ ሁኔታ፣ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል እየተባባሰ የመጣው ውጥረት እና የታላቁ የህዳሴ ግድብ ውዝግብ” ይገኙበታል። ብሊንከን እንዳሉት“ሹመቱ እርስ በርስ ለተሳሰሩ የፖለቲካ፣ የጸጥታ እና የሰብዓዊ ቀውሶች መፍትሔ ለማበጀት የሚደረገውን ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ ጥረት ለመምራት አስተዳደሩ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።”

አዲሱ ልዩ መልዕክተኛ ከሚያተኩሩባቸው ጉዳዮች መካከል የትግራይ ግጭትን ጨምሮ በቅጡ ያልረጋ የኢትዮጵያ ሁኔታ፣ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል እየተባባሰ የመጣው ውጥረት እና የታላቁ የህዳሴ ግድብ ውዝግብ ይገኙበታል

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር “ስትራቴጂካዊ ቀጠና” ሲሉ በጠሩት የአፍሪካ ቀንድ፤ አሁን ያለው ወቅት አካባቢው “በጥልቅ ለውጥ ውስጥ የሚያልፍበት” እንደሆነ ጠቁመዋል። በቀጠናው “እየተባባሰ የመጣው ግጭት የጋረጠውን አደጋ በማስቀረት በትውልድ አንድ ጊዜ የሚገኙ የለውጥ ዕድሎችን ለማገዝ” በአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት ደረጃ ተገቢውን ትኩረት መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

አዲሱ ተሿሚ ጄፍሪ ፌልትማን በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በከፍተኛ ኃላፊነት ሰርተዋል። ልዩ መልዕክተኛው በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ላይ በዘርፈ ብዙ ዲፕሎማሲ፣ ድርድር እና ሽምግልና ያላቸውን የአስርት አመታት ልምድ በመጠቀም ለአፍሪካ ቀንድ ውስብስብ ጉዳዮች አሜሪካ መፍትሔ ለማበጀት የምትከተለውን “ስትራቴጂ” እንደሚቀይሱ እና ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ተገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)