የቡድን ሰባት ሀገራት በትግራይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ

የበለጸጉት ቡድን ሰባት ሀገራት መሪዎች በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ። መሪዎቹ ለሶስት ቀናት ያካሄዱትን ስብሰባ ሲያጠናቀቁ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ባወጡት ባለ 70 ነጥብ የአቋም መግለጫ፤ በትግራይ የቀጠለው ግጭት፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለጠኔ (famine) መጋለጥን ጨምሮ እየተፈጠረ ያለው ግዙፍ ሰብዓዊ አደጋ አሳስቦናል ብለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ጨምሮ የናጠጡ ሰባት የዓለም ሀገራት መሪዎች በደቡብ ምዕራብ ኢንግላንድ ባደረጉት የፊት ለፊት ስብሰባ አንገብጋቢ ብለው ከመከሩባቸው ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ውስጥ፤ በትግራይ የተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ አንዱ ነው። የሀገራቱ መሪዎች ዛሬ እሁድ ሰኔ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጡት የጋራ የአቋም መግለጫ “ጠብ ጫሪነት በፍጥነት እንዲቆም፣ በሁሉም አካባቢዎች የእርዳታ ድርጅቶች ያልተገደበ እንቅስቃሴ እንዲፈቀድላቸው እና የኤርትራ ወታደሮች በአፋጣኝ እንዲወጡ ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል።

የቡድን ሰባት ሀገራት መሪዎች በዚሁ መግለጫቸው፤ በትግራይ ክልል ተፈጽመዋል ያሏቸውን ወሲባዊ ጥቃቶችን ጨምሮ አሰቃቂ ድርጊቶችን አውግዘዋል። መሪዎቹ በክልሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የፈጸሙ አካላት ለፍትህ እንዲቀርቡም ጠይቀዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር የተጀመረውን ምርመራም በጸጋ እንደሚቀበሉ ገልጸዋል። 

“ጂ 7” በመባል የሚታወቁት የሰባቱ ሀገራት መሪዎች ይህን መግለጫ ከማውጣታቸው ከሶስት ቀን በፊት፤ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ በትግራይ ጉዳይ ተመሳሳይ አቋም የተንጸባረቀበት ስብሰባ አካሄደው ነበር። በቪዲዮ ኮንፍረንስ በተካሄደው በዚሁ ስብሰባ የተሳተፉ የአውሮፓ ህብረት እና የአሜሪካ ባለስልጣናት ባወጡት መግለጫ፤ በትግራይ እገዛ ለሚያስፈልጋቸው እርዳታ ይደርስ ዘንድ በግጭቱ የሚሳተፉ ሁሉም ወገኖች ተኩስ እንዲያቆሙ ጠይቀዋል። 

“የኢትዮጵያ መሪዎች ብሔራዊ እርቅ እና መግባባት የሚፈጥር ሰፊ እና አካታች የፖለቲካ ሂደት እንዲከተሉ ጥሪ እናቀርባለን”

– የቡድን ሰባት ሀገራት መሪዎች

የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ በዚሁ የጋራ መግለጫቸው፤ ተፈላሚ ወገኖች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ከመፈጸም እንዲቆጠቡ አሳስበዋል። የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ባለስልጣናት ከዚህ ቀደም ቃል በገቡት መሠረት፤ የኤርትራ ወታደሮች የትግራይ ክልልን ለቅቀው መውጣታቸውን ማረጋገጥ አለባቸው ብለውም ነበር። 

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዳደር ከምዕራባውያኑ በተከታታይ የሚቀርብበትን ወቀሳ፤ ማብራሪያ እና ማስተባበያ በመስጠት ለመከላከል እየሞከረ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ትናንት ቅዳሜ በቪዲዮ አማካኝነት በመስሪያ ቤታቸው ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ያሰራጩት መግለጫ፤ ለዚህ አንድ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዚሁ የቪዲዮ መልዕክታቸው “በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ውስጥ አንዳንድ ወገኖች በሰብዓዊነት ስጋት ሽፋን የኢትዮጵያን አንድነት ለማዳከም የጀመሩት ዘመቻ አሳዛኝ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። መንግስታቸው “የማሳነስ” ያሉትን አካሄድ እንደማይቀበል የገለጹት አቶ ደመቀ፤ ግለሰቦች እና አጋሮች “ጠቃሚ ያልሆኑ” ካሏቸው እንቅስቃሴዎች እንዲታቀቡ ጠይቀው ነበር። “አንዳንድ ተዋናዮች በሰብዓዊ እርዳታ ሽፋን ሽብርተኛውን [ቡድን] ለማስታጠቅ የጦር መሳሪያ ለማሳለፍ ለመሞከራቸው ተዓማኒ መረጃ አለን” ሲሉም ከስሰዋል። 

የኢትዮጵያ መንግስት የትግራይ ክልልን ያስተዳድር የነበረውን ህወሓትን በሽብርተኝነት መፈረጁ ይታወሳል። የቡድን ሰባት አገራት መሪዎች ግን በዛሬው መግለጫቸው “ሁሉም ወገኖች ለቀውሱ ብቸኛ መፍትሔ የሆነውን ተዓማኒ የፖለቲካ ሒደት እንዲከተሉ” ጥሪ አቅርበዋል። መሪዎቹ “ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ እና የፖለቲካ መብቶች የሚከበሩበት” መጻኢ ጊዜ ሲባል የኢትዮጵያ መሪዎች ሊከተሉት የሚገባውን ሂደትም በመግለጫቸው ጠቁመዋል። 

“የኢትዮጵያ መሪዎች ብሔራዊ እርቅ እና መግባባት የሚፈጥር ሰፊ እና አካታች የፖለቲካ ሂደት እንዲከተሉ ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል የ“ጂ 7” መሪዎች። የቡድን ሰባት ሀገራት ተብለው የሚጠሩት ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ጃፓን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካን ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)