በበእምነት ወንድወሰን
በትግራይ ክልል በነበረው ውጊያ ምክንያት የመንገደኞች መጓጓዣ አገልግሎቱን አቋርጦ የነበረው የሽሬ እንደስላሴ አየር ማረፊያ በረራዎችን ማስተናገድ ሊጀምር ነው። አየር ማረፊያው ስራውን የሚጀምረው ከረቡዕ ሰኔ 9፤ 2013 ጀምሮ እንደሆነ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ክፍል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል።
የሽሬ እንደስላሴ አየር ማረፊያ ስራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም መስዑድ አየር ማረፊያው ስራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። “አየር ማረፊያችን በቅርቡ ሥራ ስለሚጀምር ዝግጅት አድርጉ ተብለን በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀስን ነው የምንገኘው። ሆኖም ይሄነው የተባለ ቀን ግን እስካሁን ግልጽ አልተደረገልንም” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን በ2007 ዓ.ም ግንባታው ተጀምሮ ከሁለት ዓመት በኋላ ወደ ስራ የገባው የሽሬ እንደስላሴ አየር ማረፊያ በሳምንት 24 በረራዎችን ያስተናግድ ነበር። ከሽሬ ከተማ በደቡብ አቅጣጫ የሚገኘው ይሄው አየር ማረፊያ፤ የኮቪድ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ በቀን የሚያስተናግዳቸው በረራዎች ከስድስት ወደ ሶስት እና ሁለት ዝቅ ብለው እንደነበር ስራ አስኪያጁ ያስረዳሉ።
በትግራይ ክልል ውጊያ መቀስቀሱን ተከትሎ ሙሉ ለሙሉ ስራውን አቁሞ የነበረው አየር ማረፊያው፤ ከነገ በስቲያ ወደ ስራ ሲመለስ በየቀኑ በረራዎችን እንደማያስተናግድ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚሰሩ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ገልጸዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያወጣውን የበረራ መርሃ ግብር የተመለከቱት ምንጮች፤ ወደ አየር ማረፊያው የሚደረጉት በረራዎች በሳምንት ሶስት ጊዜ ብቻ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የሽሬ እንደስላሴ አየር ማረፊያ ለበረራ ዝግ በነበረበት ወቅት ዘረፋ እንደተካሄደበት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የገለጹት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች፤ ስራውን እንደገና ለመጀመር የሚያስችሉ ዕቃዎች ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ከመቐለ ከተማ ሲጓጓዙ እንደነበር አመልክተዋል። አየር ማረፊያው ዘረፋ ተካሄዶበታል ቢባልም፤ በውጊያ ወቅት ውድመት እንዳልደረሰበት ስራ አስኪያጁም ሆነ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን መስሪያ ቤት ከፍተኛ ኃላፊ ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው “በትግራይ ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ሁኔታ የሽሬ እና ሁመራ አየር ማረፊያ ጣቢያዎች ላይ ምንም አይነት ጉዳት አልደረሰባቸውም” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ሁለቱ አየር ማረፊያዎች ስራ ለመጀመር እና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)