በደሴ ከተማ የሰዓት ዕላፊ ገደብ ተጣለ

በሃሚድ አወል

በደሴ ከተማ የሰዎች እና ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ላይ ከዛሬ ጀምሮ የሰዓት ገደብ መጣሉን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ። የሰዓት ገደቡ የተጣለው ከሰሜን ወሎ ተፈናቅለው ወደ ደሴ የገቡ ሰዎች ቁጥር በመብዛቱ መሆኑን የከተማዋ ከንቲባ አቶ አበበ ገብረ መስቀል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ከዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 4፤ 2013 ጀምሮ ተግባራዊ በሚሆነው የሰዓት ዕላፊ ገደብ መሰረት በተለምዶ ባጃጅ ተብለው የሚጠሩ የባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት እንዲሆን መወሰኑን አቶ አበበ ገልጸዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች እና የሌሎች ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ደግሞ እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት ብቻ እንዲሆን መደረጉንም የደሴ ከተማ ከንቲባ አስረድተዋል። 

በሰሜን ወሎ አካባቢ ባለው ውጊያ ምክንያት ከአካባቢው ተፈናቅለው ወደ ደሴ ከተማ የገቡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የጠቆሙት ከንቲባው፤ ይህም ለሰዓት ገደቡ መጣል ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ይገልጻሉ። “ከትናንትና ጀምሮ በጣም በርካታ ተፈናቃዮች [ወደ ደሴ] ገብተዋል” የሚሉት አቶ አበበ፤ ሁኔታው “ለክትትል የሚያስቸግር” ነው ይላሉ። “በዚህ መንገድ የምንቀጥል ከሆነ፤ ሰርጎ ገቡንም ምኑንም ለመከታተል አንችልም” ሲሉ የተፈናቃይ መብዛት የከተማዋን ደህንነት ለማስጠበቅ አስቸጋሪ እንዳደረገው ያብራራሉ።

ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎችን ይዘው ወደ ከተማዋ የመጡ ተፈናቃዮች መኖራቸውን የሚናገሩት አቶ አበበ፤ የተወሰኑት ባጃጆች እና ተሽከርካሪዎች ሊብሬ እና ፍቃድ የሌላቸው መሆናቸውን ደርሰንበታል ብለዋል። ከህብረተሰቡ የተሰረቁ ባጃጆች መኖራቸውን ጥቆማ ደርሶናል የሚሉት ከንቲባው፤ “ባጃጆችን ለጊዜው አቁመናቸዋል። ከስራ እንቅስቃሴ ውጭ ናቸው። አጣርተን ስንጨርስ ወደ ስራ እናሰማራቸዋለን” ሲሉ የተሽከርካሪዎቹ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ጥቆማ ሰጥተዋል። 

ወደ ደሴ የመጡ ተፈናቃዮችን ሁኔታ በተመለከተ የተጠየቁት ከንቲባው፤ የከተማው አስተዳደር ባቋቋመው ኮሚቴ አማካኝነት በተመረጡ ትምህርት ቤቶች እንዲያርፉ መደረጋቸውን ተናግረዋል። በየቤተሰቦቻቸው እና ሆቴሎች ውስጥ ያረፉ ተፈናቃዮች መኖራቸውንም አክለዋል። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሶስት የደሴ ከተማ ነዋሪዎችም ከሰሜን ወሎ በርካታ ተፈናቃዮች ወደ ደሴ ከተማ መምጣታቸውን አረጋግጠዋል። ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የወሎ ዩኒቨርስቲ መምህር ተፈናቃዮቹ ከቆቦ፣ ከወልድያ እና መርሳ አካባቢ የመጡ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

የተወሰኑ ተፈናቃዮች ተሽከርካሪዎቻቸውን ይዘው ወደ ደሴ በመምጣታቸው፤ በከተማይቱ የትራፊክ መጨናነቅ እንዲከሰት ማድረጉን የዩኒቨርስቲ መምህሩ አስረድተዋል። የከተማይቱ ነዋሪዎች እንደ ካፌ እና ምግብ ቤት ባሉ የአገልግሎት መስጫ ቦታዎች እንደ ልብ አገልግሎት ለማግኘት መቸገራቸውንም በተጨማሪነት አንስተዋል።   

ወደ ደሴ የሚመጡ ተፈናቃዮች ቁጥር ማሻቀብን ተከትሎ በምግብ አቅርቦቶች እና የኪራይ ቤቶች ላይ “የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ መከሰቱን”ም የከተማዋ ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በዳቦ ንግድ ላይ የተሰማራ አንድ የከተማዋ ነዋሪ፤ በኩንታል ሶስት ሺህ ብር ሲሸጥ የነበረው ዱቄት አሁን እስከ አምስት ሺህ ብር እየተሸጠ መሆኑን ጠቁሟል። ይኸው ነዋሪ በኪራይ ቤቶች ረገድም ተመሳሳይ የዋጋ ጭማሪ መስተዋሉን ያስረዳል። 

እንደ ነዋሪው ገለጻ በፊት እስከ 1,500 ብር ይከራዩ የነበሩ ቤቶች አሁን ሶስት ሺህ ብር እየተጠየቀባቸው ነው። አንድ ስሟ እዳይጠቀስ የፈለገች ነዋሪም፤ በከተማይቱ “የኪራይ ቤቶች ዋጋ በእጥፍ ጨምሯል” ስትል የሌላኛውን ነዋሪ ገለጻ አጠናክሯለች። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)