የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የአማራ እና አፋር ክልሎችን ዛሬ እንደሚጎበኙ አስታወቁ። ከትላንት በስቲያ እሁድ መቐለ ደርሰው የተመለሱት ኦባሳንጆ፤ ትላንት ምሽት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ አቅርበዋል።
ባለፈው ሐሙስ አዲስ አበባ የደረሱት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፤ ወደ መቐለ ከመጓዛቸው በፊት ከፕሬዝደንት ሳህለ-ወርቅ ዘውዴ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት ሽመልስ አብዲሳ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን ትናንት ምሽት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ውይይት ላይ አስረድተዋል።
ከአዲስ አበባ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ውይይቱን የተቀላቀሉት ልዩ ልዑኩ “እየተባባሰ በመጣው ውጊያ፣ ውጥረቱን ማርገብ በሚቻልበት መንገድ እና ለውይይት መንገድ በሚመቻችበት አካሔድ” ላይ ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ባለስልጣናት እና ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት ጋር ያደረጓቸው ውይይቶች “ፍሬያማ” እንደነበሩ አብራርተዋል። በትግራይ የተቀሰቀሰው ውጊያ የተስፋፋባቸውን የአማራ እና የአፋር ክልሎችን ዛሬ ማክሰኞ የመጎብኘት ዕቅድ እንዳላቸውም አስታውቀዋል።
ኦባሳንጆ ወደ መቐለ ተጉዘው ከትግራይ ክልል ባለስልጣናት ጋር መነጋገራቸውንም ለጸጥታው ምክር ቤት ገልጸዋል። የአፍሪካ ህብረት ልዩ ልዑኩ በመቐለ ቆይታቸው ከሕወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጋር መገናኘታቸውን የትግራይ ክልል መገናኛ ብዙሃን በምስል አስደግፈው ባሰራጩት መረጃ አሳይተዋል።
የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት፤ በአዲስ አበባ እና በመቐለ ባደረጓቸው ውይይቶች ባለስልጣናቱ “ልዩነቶቻቸው ፖለቲካዊ መሆናቸውን እና ፖለቲካዊ መፍትሔ እንደሚሹ በተናጠል መስማማታቸውን” ለጸጥታው ምክር ቤት አስረድተዋል። ኦባሳንጆ 15 አባላት ያሉት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት፤ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ህወሓት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ፖለቲካዊ ውይይት እንዲጀምሩ ጠንካራ ግፊት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የአፍሪካ ህብረት ልዩ ልዑኩ ከዚህ በተጨማሪም ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ በአፋጣኝ አጠቃላይ የተኩስ እና ግጭት ማቆም ላይ እንዲደረስ እንዲሁም በአፋጣኝ ያለ ገደብ የሰብዓዊ ዕርዳታ እንቅስቃሴ እንዲፈቀድ ጥሪ እንዲደረግም አሳስበዋል። ኦባሳንጆ በሳምንቱ መጨረሻ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ጉዳይ እና የወታደሮች መውጣትን በሚመለከት ሁሉንም ወገኖች የሚያረካ አንዳች መርሐ ግብር በእጃችን ይኖራል ብለን እንጠብቃለን ሲሉ ጥረታቸው የሚገኝበትን ደረጃ በጥቂቱም ቢሆን ጠቆም አድርገዋል።
ይሁንና “ያለን ዕድል ትንሽ፤ ጊዜውም አጭር ነው” የሁኔታውን አሳሳቢነት ገልጸዋል። ኦባሳንጆ ስጋታቸውን በገለጹበት በትላንትናው ዕለት፤ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቃባይ ኔድ ፕራይስም ተመሳሳይ ሐሳብ አንጸባርቀዋል። የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ስብሰባ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ቃል አቃባዩ በሰጡት ዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ፤ አሜሪካ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በትብብር ሰርቶ ለግጭቱ መፍትሔ ለማበጀት ያለው “ዕድል ጠባብ ነው” የሚል እምነት እንዳላት ጥቆማ ሰጥተዋል።
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ጄፍሪ ፌልትማን፤ ከአፍሪካ ህብረት አቻቸው ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ጋር ትላንት ሰኞ ምሽት ለመገናኘት ቀጠሮ እንደነበራቸው ፕራይስ ገልጸዋል። ቃል አቀባዩ እንዳሉት የሁለቱ ልዩ ልዑካን ውይይት “በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት” የሚያደርጉት ጥረት አካል ነው።
እየተባባሰ ለመጣው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መፍትሄ ለማፈላለግ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ፌልትማን፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር ባለፈው አርብ ጥቅምት 26 ተገናኝተው መነጋገራቸውን ቃል አቃባዩ አረጋግጠዋል። ፌልትማን በማግስቱ ወደ ናይሮቢ አቅንተው ከኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር የተገናኙ ሲሆን ትላንት ሰኞ በድጋሚ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)