በሃሚድ አወል
አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ይፋዊ የምስረታ በዓል ህዳር 13፤ 2014 እንደሚካሄድ የክልሉ አደራጅ ኮሚቴ ጸሃፊ አቶ ምትኩ ታምሩ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የክልሉ የምስረታ ስነ ስርዓት የሚካሄደው፤ የካፋ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ቦንጋ ከተማ እንደሆነም ገልጸዋል።
አስራ አንደኛው ክልል በመሆን ባለፈው ሳምንት ፌደሬሽኑን የተቀላቀለው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፤ ይፋዊ ምስረታውን የሚያካሄደው ከነባሩ የደቡብ ክልል ጋር የስልጣን ርክክብ ካካሄደ 20 ቀናት በኋላ ነው። በምስረታ ስነ ስርዓቱ ላይ የአዲሱ ክልል ህገ መንግስት በህገ መንግስት አጽዳቂ ኮሚቴ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ከክልሉ ህገ መንግስት መጽደቅ በኋላ፤ ከነባሩ የደቡብ ክልል በመውጣት የአዲሱን ክልል ምክር ቤት የሚቀላቀሉ አባላት አፈ ጉባኤ እንደሚመርጡ አቶ ምትኩ ጠቁመዋል። በነባሩ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ከቤንች ሸኮ፣ ካፋ፣ ዳውሮ፣ ምዕራብ ኦሞ እና ሸካ ዞኖች እንዲሁም ኮንታ ልዩ ወረዳ የተመረጡ 52 ተወካዮች ነበሩ።
የአዲሱ ክልል ምክር ቤት የምስረታ ጉባኤውን የሚያካሂደው፤ ከደቡብ ክልል ምክር ቤት ወጥተው አዲሱን ክልል በሚቀላቀሉት በእነዚህ ተወካዮች መሆኑን አቶ ምትኩ አስረድተዋል። አፈ ጉባኤ ከተመረጠ በኋላ ቀጣዩ ተግባር ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ የአዲሱን ክልል አስፈጻሚ አካላት መሰየም እንደሚሆን የአደራጅ ኮሚቴው ጸሃፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል።
ከአስራ ሶስት ቀናት በኋላ በሚካሄደው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምስረታ ስነ ስርዓት ላይ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችን ጨምሮ ከፍተኛ የፌደራል መንግስት ባለስልጣናት እንደሚገኙ አቶ ምትኩ ገልጸዋል። በተጋባዥነት የሚገኙ እንግዶች የሚያደርጓቸው ንግግሮች እና የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች የምስረታ መርሃ ግብሩ አንድ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
አስራ አንደኛው የኢትዮጵያ ክልል ምስረታ እውን የሆነው መስከረም 20፤ 2014 በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ውጤት መሰረት ነው። በደቡብ ክልል ስር በነበሩ አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ በተካሄደው በዚህ ህዝበ ውሳኔ፤ ድምጽ ለመስጠት ከወጡ የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል 96 በመቶው የአዲሱን ክልል መመስረት ደግፈዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህዝበ ውሳኔውን ውጤት ተቀብሎ ያጸደቀው የድምጽ መስጠት ሂደቱ በተከናወነ በወሩ ነበር። ከዚህ ስብሰባ አራት ቀናት በኋላ አስቸኳይ ጉባኤውን ያካሄደው የደቡብ ክልል ምክር ቤት፤ ከአዲሱ ክልል ጋር ባለፈው ሳምንት የስልጣን ርክክብ አድርጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)