• ላለፉት 26 ቀናት ጋዜጠኛው ያለበት ቦታ እንደማይታወቅ ቤተሰቦቹ ለፍርድ ቤት ገልጸዋል
በሃሚድ አወል
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የአሐዱ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ዜና አርታኢ የሆነው ክብሮም ወርቁን ከእስር መፍታቱን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ። የጋዜጠኛው ቤተሰቦች በበኩላቸው ክብሮም ከ26 ቀናት በፊት በፍርድ ቤት ከእስር እንዲለቀቀ ቢወሰንለትም እስካሁንም ያለበትን እንደማያውቁ ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል።
ጋዜጠኛው “ጭራሹኑ ከእስር አልተፈታም” የሚል እምነት ያላቸው የክብሮም ቤተሰቦች፤ ጉዳዩን ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወሰዱት ባለፈው ህዳር ወር አጋማሽ ነበር። በክብሮም ጠበቃ አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ አማካኝነት ለፍርድ ቤቱ የቀረበው አቤቱታ፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን “የፍርድ ቤት ውሳኔ ባለማክበር፣ ግለሰቡን በኃይል አስገድዶ በመያዝ ከእስር ቤት እንዳይፈታ ከልክሏል” የሚል ነው።
በዚህ መሰረት ጠበቃው “አካልን ነጻ የማውጣት” (habeas corpus) አቤቱታ በመመስረት ጋዜጠኛው ከእስር እንዲፈታ ለፍርድ ቤት አቤት ብለዋል። የጋዜጠኛ ክብሮም ጠበቃ “ፍርድ ቤት ግለሰቡ በዋስትና እንዲፈታ ቢወሰንም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ግለሰቡን ፈትቶ አላስረከበኝም” በማለት ነበር አካልን ነጻ የማውጣት አቤቱታ ያቀረቡት።
ጠበቃው በመጀመሪያ አቤቱታቸውን ያቀረቡት ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የፍትሃብሔር ችሎት ነበር። አቤቱታው የቀረበለት ችሎቱ “የዋስትና መብቱ የተጠበቀለትን ግለሰብ፤ በአካል ነጻ ማውጣት አቤቱታ እንዲፈታ ሊጠየቅ አይችልም” በማለት አቤቱታውን ውድቅ አድርጎት ነበር። የጋዜጠኛው ጠበቃ በዚህ የፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብለዋል።
የጋዜጠኛውን ክስ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ህዳር 28፤ 2014 መመልከት የጀመረው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን “ግለሰቡን ለምን እንዳልፈታው መልስ ይዞ እንዲቀርብ” ለዛሬ ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዛሬ ታህሳስ 4፤ 2014 ለፍርድ ቤቱ በጽሁፍ ባቀረበው መልስ “[ተጠርጣሪው] በኮሚሽኑ በሚገኙ የተጠርጣሪ ማቆያም ሆነ በኮሚሽኑ እውቅና ስር የሌለ” መሆኑን ገልጿል። የፖሊስ ኮሚሽኑን ወክለው ፍርድ ቤት የተገኙት ነገር ፈጅም፤ ጋዜጠኛው ህዳር 9፤ 2014 ከእስር መፈታቱን እና በአዲስ አበባ ፖሊስ ቁጥጥር ስር የሌለ መሆኑን በቃል አስረድተዋል።
የጋዜጠኛው ጠበቃ አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ በበኩላቸው ፖሊስ ጋዜጠኛውን ፈትቻለሁ ባለበት ዕለት፤ ደንበኛቸው አለመፈታቱን ለፍርድ ቤት ተናግረዋል። ጋዜጠኛው በቁጥጥር ስር ሲውል ፖሊስ በኤግዚብትነት የያዛቸው የጋዜጠኛው የድምጽ መቅጃ፣ የሞባይል ስልክ፣ የባንክ ደብተር እና ሌሎች ንብረቶች አሁንም በፖሊስ እጅ እንደሚገኙ ከመርማሪ ፖሊስ ማረጋገጣቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
በችሎቱ ላይ የተገኙት የጋዜጠኛው አባትም በፍርድ ቤት የተወሰነውን 15 ሺህ ብር የዋስትና ገንዘብ ከከፈሉ በኋላ ልጃቸው በትዕዛዙ መሰረት አለመፈታቱን ተናግረዋል። ፖሊስ ክብሮምን ፈትቸዋለሁ ባለበት ቀንም፤ ከኮሚሽኑ ቅጥር ግቢ በሚኒባስ ተሸከርካሪ ወደ ሌላ ስፍራ ስለመወሰዱ መረጃ እንዳላቸውም አስረድተዋል። አቶ ወርቁ አብርሃ ልጃቸውን ለአንድ ወር ገደማ እንዳላዩት እና የት እንዳለ እንደማያውቁም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ዛሬ ታህሳስ 4፤ 2014 በጽህፈት ቤት በኩል በሶስት ዳኞች የተሰየመው ችሎት ሁለት ቀጠሮዎችን በመስጠት የዕለቱን የችሎት ውሎ አጠናቅቋል። ፍርድ ቤቱ የይግባኝ ባይ ጠበቃ በፖሊስ መልስ ላይ፤ የመልስ መልስ በሬጂስትራር በኩል እንዲያቀርቡ ለነገ በስቲያ ረቡዕ ታህሳስ 6 ትዕዛዝ ሰጥቷል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን መልስ እና የይግባኝ ባይን የመልስ መልስ ለመርመርም ለታህሳስ 12 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ጋዜጠኛ ክብሮም “ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት” ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለው ከ47 ቀናት በፊት ጥቅምት 16፤ 2014 ነበር። ክብሮም ለመጀመሪያ ጊዜ በ15 ሺህ ብር ዋስትና እንዲፈታ በፍርድ ቤት የተወሰነለት ደግሞ ከአንድ ወር በፊት ህዳር 3፤ 2014 ነው።
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ባስተላለፈው በዚህ ውሳኔ ላይ፤ ፖሊስ ህዳር 6 የይግባኝ አቤቱታ አቅርቧል። አቤቱታው የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ይግባኝ ሰሚ ችሎትም፤ በማግስቱ ህዳር 7 ቀን የፖሊስን አቤቱታ ውድቅ በማድረግ የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ማጽናቱ ይታወሳል።
ጋዜጠኛ ክብሮም በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው በአርታኢነት በሚሰራበት አሐዱ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ተረኛ በነበረበት ቀን፤ በጣቢያው ጋዜጠኛ በተሰራ ዜና ምክንያት ነው። ዜናው በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የምትገኘው የሀይቅ ከተማ በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋሏን የሚገልጽ ሲሆን በዚህም ምክንያት ዜናውን የሰራችውን ሉዋም አታክልቲ እና አርታኢዋ ክብሮም በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርገዋል።
ጋዜጠኛ ሉዋም ዜናው በተላለፈበት ዕለት ጥቅምት 12፤ 2014 በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለች ሲሆን፤ የዜናው አርታኢ ክብሮም ከአራት ቀናት በኋላ ታስሯል። ሉዋም ከ21 ቀናት እስር በኋላ የዛሬ ወር ህዳር 3፤ 2014 በ10 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር መፈታቷ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)