የተወረሩ የአፋር አካባቢዎች ሳይለቀቁ ከትግራይ ኃይሎች ጋር የሚደረግ ድርድርን እንደማይቀበል የአፋር ህዝብ ፓርቲ አስታወቀ

በሃሚድ አወል

የትግራይ ኃይሎች “በወረራ” ከያዟቸው የአፋር አካባቢዎች ሳይወጡ እና ለክልሉ ህዝብ ስጋት የማይሆኑበት ደረጃ ሳይረጋገጥ፤ ከዚህ ቡድን ጋር “የሚደረግ ወይንም ሊደረግ የታሰበ ድርድር ካለ” እንደማይቀበል የአፋር ህዝብ ፓርቲ (አህፓ) አስታወቀ። ፓርቲው፤ የአፋር ክልል መንግስት በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጅ እና “ጠንከር ያለ” ኮማንድ ፖስት እንዲያደራጅም ጠይቋል።

ፓርቲው ይህን ያለው፤ በአጎራባች የአፋር ወረዳዎች ላይ የትግራይ ኃይሎች “እያካሄዱት ነው” ስላለው “መጠነ ሰፊ ወረራ” ባወጣው መግለጫ ነው። በአህፓ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በኩል ትላንት አርብ ጥር 20 የወጣው ይኸው መግለጫ፤ የትግራይ ኃይሎች ከጥር 15 ጀምሮ ከ40 ሺህ እስከ 50 ሺህ የሚገመቱ ታጣቂዎቹን ለወረራ ማሰለፋቸውን ይገልጻል። 

የትግራይ ኃይሎች በአፋር ክልል “በወረራ በያዟቸው አካባቢዎች እጅግ ዘግናኝ የሆኑ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን” ፈጽመዋል ሲል ፓርቲው በመግለጫቸው ከስሷል። ከዚህ በተጨማሪም “ለአርብቶ አደሩ የኑሮ ዋስትና የሆኑትን እንስሳት በጥይት በመፍጀት የእብሪታቸውን መጠን በይፋ አሳይተዋል” ሲል ፓርቲው አማጽያኑን ወንጅሏል። አባላት እና ደጋፊዎቹም ለዘመቻ በሚፈለጉበት መስክ ለሚደረግላቸው ጥሪ ዝግጁ እንዲሆኑ አሳስቧል።

የአፋር ክልል ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ከአምስት ቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ የህወሓት ኃይሎች በአፋር ክልል ባደረሱት ጥቃት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውቆ ነበር። የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በዚሁ መግለጫው፤ የህወሓት ኃይል “በኪልበቲ ረሱ በተለያዩ ቦታዎች የአፋር ክልልን ወሰን ጥሶ በመግባት በአብአላ፣ በመጋሌ እና በበራህሌ በኩል በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጦርነት በመክፈት በርካታ ንጹሃንን ለጉዳት ዳርጓል” ብሏል። 

የአፋር ህዝብ ፓርቲ በትላትናው መግለጫው፤ “ወራሪ እና አሸባሪ” ሲል የጠራው የትግራይ ኃይል ከያዛቸው የአፋር አካባቢዎች እስካልወጣና ከባድ መሳሪያዎቹ ለአፋር ሕዝብ ስጋት ወደማይሆኑበት ደረጃ መውረዱ እስካልተረጋገጠ ድረስ ከዚህ ቡድን ጋር የሚደረግ ወይም ሊደረግ የታሰበ ድርድርን “እንደማይቀበል” አስታውቋል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ድርድሩ የሚካሄድ ከሆነ ግን “እንደ ሀገራዊ ክህደት የሚቆጥር” መሆኑን በጥብቅ አሳስቧል።  

የአፋርን ችግር “በመንግስት መግለጫዎች ጭምር ችላ ለማለት ሲሞከር እያስተዋልን ነው” ሲል ቅሬታውን የገለጸው  ክልላዊው ፓርቲ፤ በመላው ሀገሪቱ ታውጆ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ በሚኒስትሮችም ምክር ቤት መወሰኑንም ተቃውሟል። “የፌዴራል መንግስት አውጆት የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማንሳት ያቀረበው ሀሳብ የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ያላገናዘበ በመሆኑም በተለይ በአፋር እና አማራ ክልሎች ላይ እንዲቆይ እናሳስባለን” ሲል የአዋጁ ተፈጻሚነት በሁለቱ ክልሎች እንዲቀጥል ፓርቲው ጠይቋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት “የሃገርን ህልውና እና ሉዐላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል” በሚል ተደነግጎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተፈጻሚነት እንዲያጥር የወሰነው ከሶስት ቀናት በፊት ነበር። ለስድስት ወራት ተደንግጎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ የተወሰነው አዋጁ እንዲታወጅ “የግድ አስፈላጊ እንዲሆን አድርጎ የነበረው ሁኔታ የተቀየረ በመሆኑ እና ስጋቱን በመደበኛው የሕግ ማስከበር ስራ መከላከልና መቆጣጠር የሚቻልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ” መሆኑን ምክር ቤቱ አስታውቆ ነበር። 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈጻሚነትን ቀሪ በሚያደርገው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ባለፈው ረቡዕ ጥር 18፤ 2014 ተወያይቶ ውሳኔ ያስተላለፈው የሚኒስትሮች ምክር ቤት፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይጸድቅ ዘንድ ማስተላለፉ በወቅቱ ተገልጿል። የአፋር ህዝብ ፓርቲ በትላንቱ መግለጫው፤ የአፋር ክልላዊ መንግስት በክልሉ ተፈጻሚነት የሚኖረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጅ ይፋዊ ጥያቄ አቅርቧል። ከዚህ በተጨማሪም የክልሉ መንግስት “በአካባቢው ጠንከር ያለ ኮማንድ ፖስት እንዲያደራጅ” ፓርቲው ጠይቋል።  

በትግራይ ክልል ከአስራ አምስት ወራት በፊት የተቀሰቀሰው ጦርነት፤ ወደ አጎራባች የአፋር እና አማራ ክልሎች ከተስፋፋ ስድስት ወራትን አስቆጥሯል። ባለፉት ወራት በአፋርም ሆነ በአማራ ክልሎች በተካሄዱ ውጊያዎች፤ በርካታ ውድመት መድረሱን የየክልሎቹ ኃላፊዎች በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል። በጦርነቱ ምክንያት በአፋር ክልል ብቻ ከ70 በላይ የጤና ተቋማት ጉዳት እንደደረሰባቸው የክልሉ ጤና ቢሮ መግለጹ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)