ኢትዮ ቴሌኮም በስድስት ወራት ውስጥ 28 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

በሃሚድ አወል

ኢትዮ ቴሌኮም በ2014 በጀት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት 28 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ። ተቋሙ ያገኘው ገቢ በዕቅድ ከያዘው 86.4 በመቶውን ያሳካ እንደሆነ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ዛሬ ሰኞ ጥር 23 ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። 

ኢትዮ ቴሌኮም በዕቅድ ያስቀመጠውን ያህል ገቢ ማግኘት ያልቻለው በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ምክንያት እንደሆነ ዋና ስራ አስፈጻሚ ገልጸዋል። ተቋሙ ካሉት ስምንት ሺህ የሞባይል ጣቢያዎች ውስጥ 3,473 ያህሉ በጦርነቱ ምክንያት አገልግሎት አለመስጠታቸውን ለዚህ በማሳያነት ጠቅሰዋል። 

“በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ያለው ጦርነት በአጠረ ጊዜ ይፈታል የሚል እሳቤ አስቀምጠን ነበር። ሆኖም  ካሰብነው ውጭ ከትግራይ አልፎ በሌሎች ክልሎች ይህ ጦርነት መስፋቱ፤ በከፍተኛ ሁኔታ የዘረጋነውን የቴሌኮም መሰረተ ልማት በአግባቡ ለመጠገን እና ለማስተዳደር እንዲሁም ደንበኞቻችን መጠቀም እንዳይችሉ እንቅፋት ፈጥሯል” ሲሉ ተቋሙ የገጠመውን ችግር አስረድተዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም በጦርነቱ ምክንያት በመሰረት ልማቶቹ ላይ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት 4 ቢሊዮን ብር ገቢ ማጣቱን ስራ አስፈጻሚዋ አክለዋል። የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ባይከሰት፤ ተቋሙ 97.7 በመቶ ዕቅዱን ሊያሳካ ይችል እንደነበርም ጠቁመዋል። 

“ባለፈው የነበረው ስድስት ወር በጣም አስቸጋሪ ነው የነበረው። በአንዳንድ አካባቢዎች ተዘዋውረን ለመስራት፣ ጥገና ለማድረግ አስቸጋሪ የሆነበትም ጭምር ነው። ከዚያ አንጻር ስናየው ገቢው ጥሩ ነው ወይም አመርቂ ነው ብለን ነው የምንወስደው። አሁንም ከገጠመን ችግር አንጸር በሙሉ አቅማችን ‘ኦፕሬት’ ሳናደርግ ይህን ያህል ገቢ ማስገኘታችን በጣም ጥሩ ነው” ብለዋል ስራ አስፈጻሚዋ።

ኢትዮ ቴሌኮም በ2014 በጀት ዓመት ለማግኘት አቅዶ የነበረው ገቢ 70 ቢሊዮን ብር ነው። ተቋሙ የ2014 በጀት ዓመት እቅዱን ይፋ ባደረገበት ወቅት፤ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት 5.1 ቢሊዮን ብር ሊያሳጣው እንደሚችል አስታውቆ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)