የፖለቲካ መሪዎች ከግጭት ቀስቃሽ እና ሰብዓዊነት ከጎደላቸው ንግግሮች እንዲቆጠቡ 20 የሲቪል ማህበራት ጥሪ አቀረቡ

⚫ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተቋረጡ የመገናኛ ዘዴዎች ወደነበሩበት እንዲመለሱም ጠይቀዋል  

በተስፋለም ወልደየስ

በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም የፖለቲካ መሪዎች እና ተዋናዮች ከግጭት ቀስቃሽ እና ሰብዓዊነት ከጎደላቸው ንግግሮች እንዲቆጠቡ 20 የሲቪል ማህበራት ጥሪ አቀረቡ። ማህበራቱ ከዚህም በተጨማሪ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተቋረጡ እና የተገደቡ የመገናኛ ዘዴዎች ወደነበሩበት እንዲመለሱ እና ለህብረተሰቡ የመረጃ ተደራሽነት እንዲረጋገጥ ጠይቀዋል።

የሲቪል ማህበራቱ ይህን ጥያቄ ያቀረቡት በዛሬው ዕለት እየተከበረ ያለውን የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን ምክንያት በማድረግ ባቀረቡት ግልጽ ጥሪ ነው። ኢትዮጵያ የደቦ ጥቃት፣ በይነ ማኅበረሰባዊ ግጭቶች እና ጦርነትን ያካተተ “የፈተና ጊዜ እያሳለፈች ነው” ያሉት የሲቪል ማህበራቱ፤ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ይረዳ ዘንድ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት መከበር እንዳለበት አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ካሉት ግጭቶች የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት “የከፋ” እንደሆነ በግልጽ ጥሪያቸው ላይ የጠቀሱት ማህበራቱ፤ በዚህም ሳቢያ በርካታ ንፁኃን ዜጎች ለስቃይ መዳረጋቸውን አስታውቀዋል። በጦርነቱ የተከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ የተለያዩ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች ባደረጓቸው “ክትትሎች እና ምርመራዎች”፤ አንዳንዶቹ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች “የጦር ወንጀሎች እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ተብለው የተቀመጡትን ድንጋጌዎች የሚያሟሉ ሊሆኑ ይችላሉ” ማለታቸውን የሲቪል ማህበራቱ አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ ለተከሰቱ ግጭቶች መባባስ፣ ብሔርን መሠረት ላደረገ ጥቃት፣ ለሰብዓዊ መብቶች እና ለዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕጎች መጣስ፤ “የግጭት ቀስቃሸ መልዕክቶች፣ የጥላቻ ንግግሮች፣ የተሳሳተ መረጃ እና የጦርነት ፕሮፓጋንዳ” ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን እንደሚያምኑም በግልጽ ጥሪው ላይ ፊርማቸው ያኖሩ 20 የሲቪል ማህበራት ገልጸዋል። በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወቅት እና ከጦርነቱ በፊት በነበረው ፕሮፓጋንዳ፣ በሐሰት መረጃዎች ዘመቻ እንዲሁም በመረጃ ተደራሽነት ገደብ ምክንያት “እውነታው መስዋዕት ተደርጓል” የሚል እምነት እንዳላቸውም ማህበራቱ አክለዋል። 

ያልተገደበ የመረጃ ተደራሽነት እና የጋዜጠኞች ነጻነት “የተከሰተውን ክፍተት በመሙላት እውነቱን ለመረዳት በማገዝ” እንዲሁም “የግጭት አፈታት እና ዕርቀ ሰላም ሙከራዎችን በማቀላጠፍ” ረገድ ሚና እንዳለው የጠቀሱት የሲቪል ማህበራቱ፤ ሆኖም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢዎች  ያለው ነባራዊ ሁኔታ ከዚህ ተቃራኒው መሆኑን አመልክተዋል። ለዚህም እንደ አንድ የጠቀሱት፤ በትግራይ እና በተወሰኑ አጎራባች የአማራ እና የአፋር ክልል አካባቢዎች፣ በምዕራብ ኦሮሚያ እና በተወሰኑ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል አካባቢዎች የበይነመረብ እና ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች አገልግሎት መገደቡን ነው።

ጋዜጠኞች ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በዘፈቀደ እንደሚታሰሩ እና ክስ ሳይመሰረትባቸው በእስር እንዲቆዩ እንደሚደረጉ የሲቪል ማህበራቱ በተጨማሪነት ማሳያነት አንስተዋል። በዚህ ሁኔታ የሚታሰሩ ጋዜጠኞች ከጎብኚዎች ጋር እንዳይገናኙ ጭምር እንደሚከለከሉ የጠቀሱት ማህበራቱ፤ “ይህ [አካሄድ] ብዙኃኑ ላይ የፍርሐት እና የደህንነት ስጋት ስሜት እንዲያድርባቸው፤ እንዲሁም የሲቪክ ምህዳሩ እንዲጣበብ አድርጓል” ሲሉ ተችተዋል። 

የሚዲያ ነጻነትን በማክበርም ሆነ በኢትዮጵያ የተከሰቱ ግጭቶችን በማስቆም ረገድ መንግስት “ያለውን ቁርጠኝነት እንዲያረጋግጥ” የጠየቁት የሲቪል ማህበራቱ፤ ለጋዜጠኞች እና ለዜጎች ያልተገደበ የሚዲያና የግንኙነት ዘዴዎችን በመፍቀድ ሊካሄድ የታቀደውን አገራዊ ምክክር እንዲያበረታታ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። የሲቪል ማህበራቱ፤ በትግራይ ጦርነት “ዋና ተዋናዮች” ላሏቸው እና በመላው ኢትዮጵያ በተከሰቱ ግጭቶች ውስጥ “ተሳታፊ ናቸው” ላሏቸው አካላትም ጥሪ አስተላልፈዋል። ማህበራቱ በዚሁ ጥሪያቸው እነዚህ አካላት በግጭት ቀስቃሽ ተግባራት ከመሳተፍ፣ ግጭቶችን ከማባባስ እና ሰብዓዊነት የጎደላቸው ንግግሮችን ከማሰራጨት እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።  

ማህበራቱ ጥሪውን ካቀረቡላቸው የፖለቲካ መሪዎች መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የፍትህ፣ የሰላም፣ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሮች ይገኙበታል። ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በጥሪው ተካተተዋል።

“ጋዜጠኞች ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ፣ በዘፈቀደ ሲታሰሩና እና ክስ ሳይመሰረትባቸው፣ አልፎ ተርፎም ጎብኚዎች ተከልክለው በእስር እንዲቆዩ ሲደረጉ ተስተውሏል። ይህም ብዙኃኑ ላይ የፍርሐት እና የደኅንነት ስጋት ስሜት እንዲያድርባቸው እንዲሁም የሲቪክ ምኅዳሩ እንዲጣበብ አድርጓል” 

– የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀንን ምክንያት በማድረግ 20 የሲቪል ማህበራት ካቀረቡት ግልጽ ጥሪ የተወሰደ

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተርም በጥሪው የተዘረዘሩ ጉዳዮችን በማስፈጸም ረገድ “አዎንታዊ እና ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ” ተጠይቀዋል። ከመንግስት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተጨማሪ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም የጦርነት ፕሮፖጋንዳን እና የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል እና የሚዲያ ነጻነትን እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃን ለማሻሻል አዎንታዊ እና ገንቢ ሚና እንዲጫወቱም የሲቪል ማህበራቱ በግልጽ ጥሪያቸው አሳስበዋል። 

የግልጽ ጥሪ ደብዳቤውን ፈራሚ መሆናቸውን ዛሬ ባወጡት መግለጫ ካስታወቁ የሲቪል ማህበራት ውስጥ ሰባቱ ከጋዜጠኝነት ሙያ ጋር በቀጥታ የተገናኙ ማህበራት ሲሆኑ ስድስቱ ደግሞ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ናቸው። በሰላም እና ልማት ዘርፍ የሚሰሩ አራት ማህበራት እና ሶስት የህግ ባለሙያዎች ማህበራትም የግልጽ ጥሪው አካል መሆናቸውን በፊርማቸው አረጋግጠዋል። 

በዛሬው ደብዳቤ ከተካተቱ የሲቪል ማህበራት ውስጥ ዘጠኙ፤ በ2014 አዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ በተላለፈ ተመሳሳይ “የሰላም ጥሪ” አካል እንደነበሩ ይታወሳል። በወቅቱ ዘጠኙን የሲቪል ማህበራት ጨምሮ 24 ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በኢትዮጵያ እየተስተዋሉ ያሉ ግጭቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ፣ በግጭቶች ተሳታፊ የሆኑ አካላት ግጭቶችን ያለ ቅደም ሁኔታ እንዲያቆሙ፣ ከግጭት አባባሽ ተግባራት እንዲቆጠቡ እና ለሰላማዊ መፍትሔዎች ራሳቸውን እንዲያስገዙ ጥሪ አቅርበው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)