የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዓመታዊ ሪፖርት በአባል ድርጅቶች ቅሬታ ቀረበበት

በተስፋለም ወልደየስ

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ስድስተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ በተመለከተ በዓመታዊ የስራ ክንውን ሪፖርቱ ያቀረበው ገለጻ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅሬታ አስነሳ። የምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚ አመራሮች፤ የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት እና ሀገሪቱ አሁን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ የሚመጥን ሪፖርት አላቀረቡም በሚል ተተችተዋል። 

ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ 53 የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአባልነት ያቀፈው ምክር ቤቱ ይህን ቅሬታ እና ትችቱን ያስተናገደው፤ ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 27፤ 2014 በአዲስ አበባው ማዶ ሆቴል ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ነው። በዛሬው ጠቅላላ ጉባኤው ከጥር 2013 እስከ ሚያዝያ 2014 የነበረው የምክር ቤቱ የስራ ክንውን በሪፖርት መልክ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። 

በ25 ገጾች የተዘጋጀው ይህ ሪፖርት፤ በምክር ቤቱ የተሰሩ አበይት ስራዎች፣ የተገኙ ውጤቶች፣ ዋና ዋና ተግዳሮቶች እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን የዳሰሰ ነበር። የጋራ ምክር ቤቱ ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ “ከፍተኛ ትኩረት፣ ጊዜ እና ሀብት መድቦ” ካከናወናቸው ስራዎች ውስጥ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫን የተመለከቱ ክንውኖች እንደሚገኙበት በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

“ምክር ቤቱ ከአባል የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አጋሮች ጋር በመተባበር ምርጫው ሰላማዊ፣ ነጻ እና ፍትሀዊ ይሆን ዘንድ የምርጫ ዑደትን መሰረት በማድረግ ከምርጫ በፊት፣ በምርጫው ዕለት እና ድህረ ምርጫ ስራዎችን በቅርበት በመከታተል የድርሻውን ለመወጣት ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርጓል” ያለው ሪፖርቱ፤ በዚህም ምርጫው “ከዚህ ቀደም ከተካሄዱ ምርጫዎች በተሻለ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ” የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁሟል።

“በስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አብዛኛው መራጩ ህዝብ ‘ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ በሚል ሆደ ሰፊነት ከምርጫ በፊት እና በምርጫ ቀናት የታዩ የህግ፣ የአስተዳደር እና የቴክኒክ ችግሮችን አይቶ እንዳላየ ያለፈ ሲሆን፣ በተለይም የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ባሳዩት አርቆ አስተዋይነት ምክንያት ከምርጫ በፊትም ሆነ ከምርጫ በኋላ እዚህ ግባ የሚባል የጸጥታ መደፍረስ እና ድህረ ምርጫ ግጭት ሳይከሰት ምርጫው ተጠናቅቋል” ሲል የጋራ ምክር ቤቱ በዓመታዊ ሪፖርቱ አስፍሯል። 

ምርጫው ህዝቡ እና ተሳታፊ ፓርቲዎች እንደጠበቁት “ነጻ እና ፍትሃዊ መሆን አልቻለም” ያለው የምክር ቤቱ፤ የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ ራሳቸውን ማግለላቸው “በምርጫ ሂደት እና ውጤት ላይ አሉታዊ ድባብ ጥሎበት አልፏል” በማለት የምርጫ ግምገማውን አቅርቧል። የምክር ቤቱ ሪፖርት፤ በምርጫ ወቅት የተከሰቱ አንኳር ጉዳዮችን የዳሰሰ አባሪ እና አባል የፖለቲካ ድርጅቶች ከምርጫው መጠናቀቅ በኋላ ያወጡትን የአቋም መግለጫ ጭምር በማያያዝ ስለ ሂደቱ ለማብራራት ቢሞክርም፤ በርከት ያሉ ትችቶችን ከማስተናገድ አላመለጠም። 

በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራውን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በመወከል በዛሬው ጠቅላላ ጉባኤ የተሳተፉት አቶ ጀቤሳ ጋቢሳ በምርጫው ሂደት እና በምክር ቤቱ ሪፖርት ላይ የሰላ ትችት በመሰንዘር ቀዳሚ ሆነዋል። አቶ ጀቤሳ፤ የምክር ቤቱ አመራሮች የሀገሪቱን ተጨባጭ የፓለቲካ ሁኔታ በተመለከተ ያስቀመጡት ግምገማ “አሁን ያለንበትን ተጨባጭ ሁኔታ የሚቃረን ነው” ሲሉ ተችተዋል። 

“ዛሬ አገሪቱ በጦርነት እየታመሰች ነው። ሰላም የለም፣ ብዙ ህዝብ ተፈናቅሏል። ረሀብ አለ፣ የኑሮ ውድነት አለ፣ የስራ አጥነት በጣም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ይሄ ምንጩ ደግሞ ያለፈው ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ካለመሆኑ ነው” የሚሉት አቶ ጀቤሳ፤ ሆኖም የጋራ ምክር ቤቱ አመራሮች በሚዲያዎች በመቅረብ “ያለፈው ምርጫ ሰላማዊ ነበር፤ መንግስት ሊኖረን ይገባልና በቃ መንግስት ይኑር ብለን ነው የተቀበልነው” ማለታቸው አግባብ እንዳልነበር ተናግረዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተወሰኑ ወረዳዎችን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ምርጫ ያልተካሄደው “ሰላም ስለሌለ” መሆኑን የጠቆሙት የኦነጉ ተወካይ፤ “ያለፈው ምርጫ የተካሄደው በሰላማዊ ሁኔታ ውስጥ ነው ብለን፣ ሪፖርቱ ላይ አስቀምጠን ሪፖርቱን የምናጸድቅ ከሆነ በጣም ስህተት ውስጥ ነው የምንገባውና እንዲታረም ነው የምንፈልገው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ (ቤህነን) ሊቀመንበር አቶ አብዱሰላም ሸንግል፤ የእርሳቸው ፓርቲ በሚንቀሳቀስበት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምርጫው የተካሄደው “ክልሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ በነበረበት ወቅት” እንደሆነ አስታውሰው በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ምርጫ ማድረግ አጠያያቂ እንደሆነ ተናግረዋል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ካሉት 22 የምርጫ ክልሎች ውስጥ ምርጫ የተካሄደው በሰባቱ ብቻ መሆኑን የጠቀሱት የፓርቲው ሊቀመንበር፤ ይህ የሆነው ደግሞ በአካባቢው ሰላም በመታጣቱ እንደሆነ አስረድተዋል።

ምርጫው ሰላማዊ ካለመሆኑ ባሻገር፤ በምርጫው ወቅት እና ከዚያም በኋላ እርሳቸውን ጨምሮ በርካታ የፓርቲው አባላት እና ታዛቢዎች መታሰራቸው ሂደቱ “ከፍተኛ ችግር” እንዳለበት የሚያመለክት መሆኑን ጠቁመዋል። “ይሄ በነበረበት ሁኔታ ‘ምርጫው ፍትሃዊ ነበር፤ አልነበረም’ የሚለው ምንም የሚያጨቃጭቅ ነገር ያለ አይመስለኝም። ምርጫው ፍትሃዊ አልነበረም” ሲሉም ድምዳሜያቸውን ለተሰብሳቢው አጋርተዋል።

የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዎብን) ሊቀመንበር አቶ አማኑኤል ሞጊሶ በበኩላቸው  ብልጽግና ፓርቲ በምርጫ እንዲያሸንፍ የጋራ ምክር ቤቱ “ሚና ተጫውቷል” ሲሉ ወንጅለዋል። የምክር ቤቱ አመራር “ብልጽግና እንዲያሸንፍ ደግፈናል” በማለት በተለያዩ መድረኮች ሲናገሩ መስማታቸውን የጠቀሱት የፓርቲው ሊቀመንበር፤ ይህ አይነቱ “አስተሳሰብ እና አካሄድ መስተካከል” እንዳለበት አስገንዝበዋል።   

የጋራ ምክር ቤቱ፤ ብልጽግና ፓርቲ በምርጫ ወቅት ወደ መስመር እንዲገባ ለማድረግ ደብዳቤ ከመጻፍ እና አቤቱታ ከማቅረብ የዘለለ “እርምጃ አልወሰደም” ሲሉም አቶ አማኑኤል ተጨማሪ ነጥብ አንስተዋል። የተለያዩ የሰላማዊ የትግል ስልቶችን መጠቀምን በተመለከተ ምክር ቤቱ አቋም ባለመውሰዱም “የኢትዮጵያን ህዝብ ድምጽ እንዲባክን አድርገናል” ሲሉም ነቅፈዋል። 

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) የስራ አስፈጻሚ ኮሜቴ አባል የሆኑት አቶ ሙላቱ ገመቹ በበኩላቸው፤ “ሪፖርቱ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የቀረበ ሳይሆን ለፓርላማ የቀረበ ይመስላል” ሲሉ ተችተዋል። ሪፖርቱ “በሀገሪቷ ውስጥ የሚደረገውን ነገር የሚገልጽ አይደለም” ያሉት አቶ ሙላቱ፤ የፓለቲካ ፓርቲዎች ስሜትም ከሪፖርቱ ጋር “አብሮ የሚሄድ አይደለም” ብለዋል። 

“[ሪፖርቱ] የኢትዮጵያ የፓለቲካ ፓርቲዎችን አቋም የያዘ አይመስለኝም። ስለዚህ በጣም አሳዛኝ ነው። በአንዳንዱ ድንጋይ የሚያቀብል፣ ነገሮችን ሆይ ሆይ የሚል፣ ለሀገር ሰላም፣ ለሀገር ጤንነት እሳቤ የሌለው ፓርቲ አይነት ነገር ነው። ስለዚህ በጣም አዝናለሁ” ሲሉም አቋማቸውን ለተሰብሳቢው አስረድተዋል።

በጠቅላላ ጉባኤው ተሳታፊዎች ለተነሱ አስተያየቶች ምላሽ የሰጡት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር አብዱልቃድር አደም፤ በሪፖርቱ ማጠቃለያ በአባሪነት በተያያዘው የምርጫ ግምገማ ላይ ምርጫው “ነጻ እና ፍትሃዊ” እንዳልነበር በግልጽ መቀመጡን አስረድተዋል። ምርጫው “ሰላማዊ ነበር” በሚል የተጠቀሰውም “አንጻራዊ” እንደሆነ ገልጸዋል። 

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዓመታዊ ሪፖርት በዛሬው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተነሱ ሃሳቦች ታክለውበት እንዲጸድቅ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ 40 ተሳታፊዎች ደግፈውታል። አምስት ተሳታፊዎች ሪፖርቱ መጽደቅ የለበትም ሲሉ ድምጻቸውን የሰጡ ሲሆን ሌሎች አምስት ተሳታፊዎች ደግሞ ድምጽ ከመስጠት ታቅበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)