ኢትዮቴሌኮም የአምስተኛው ትውልድ (5G) የኔትወርክ አገልግሎትን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባሉ አምስት አካባቢዎች መስጠት ጀመረ። ኩባንያው የ5G የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎቱን፤ በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ባሉ 150 ቦታዎች ላይ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የማስፋፋት እቅድ እንዳለው አስታውቋል።
መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ተቋም የሆነው ኢትዮቴሌኮም የ5G አገልግሎት የጀመረው በቅድመ ገበያ ሙከራ (pre-commercial) ደረጃ መሆኑን የኢትዮቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ተናግረዋል። ዋና ስራ አስፈጻሚዋ በአዲስ አበባው ሸራተን ሆቴል በተካሄደው የአገልግሎቱ ማብሰሪያ መርሃ ግብር ላይ እንደገለጹት፤ ኩባንያው በሙከራ ደረጃ አገልግሎቱን የሚሰጠው በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙት ዩኒቲ ፓርክ፣ ወዳጅነት (ፍሬንድሺፕ) ፓርክ፣ ሸራተን አዲስ ሆቴል፣ የኢትዮቴሌኮም ዋና መስሪያ ቤት በሚገኝበት ቸርችል ጎዳና እና አካባቢዎቹ ላይ ነው።
የ5G የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት በሰከንድ እስከ 10 ጊጋ ባይት የሚደርስ ከፍተኛ ፍጥነት እንዳለው የጠቀሱት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፤ ይህ አሁን በጥቅም ላይ የሚገኘው የ4G አገልግሎት ካለው ፍጥነት ሲነጻጸር በ20 እጥፍ የላቀ እንደሆነ አስረድተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ዳታ በማስተላለፍ ረገድ ያለውን መዘግየት (latency) በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ ወደ 1ሚሊ ሰከንድ የሚያወርድ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮቴሌኮም የ5G አገልግሎቱን አሁን በሙከራ ደረጃ ከጀመረባቸው አምስት አካባቢዎች፤ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ 150 የማሳደግ እቅድ እንዳለው የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ አስታውቀዋል። “በመላው አዲስ አበባ ወይም በመላው ሀገራችን በዚህ ጊዜ 5Gን cover እናደርጋለን ብለን አንናገርም። ይሄ realistic ስለማይሆን ማለት ነው። የደንበኞችን ፍላጎት፣ ከፍተኛ የኢንተርኔት ፍላጎት እና የ5Gን ባህሪያት ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለን በምናስባቸው አካባቢዎች ግን ተግባራዊ ማድረጋችንን እንቀጥላለን ማለት ነው” ሲሉ ፍሬህይወት ተናግረዋል።
ኩባንያው አገልግሎቱን ለማስፋፋት “የደንበኞች ዝግጁነትና 5G የመጠቀም ፍላጎት ማደግ፣ የ5G መጠቀሚያ መሳሪያዎች እና ቀፎዎች በስፋትና አቅምን ባገናዘበ መልኩ ገበያ ላይ መኖርን” ከግምት ውስጥ እንደሚያስገባ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል። ኢትዮቴሌኮም በአሁኑ ወቅት ካሉት 64 ሚሊዮን ደንበኞች ውስጥ የ5G መጠቀሚያ ቀፎ የያዙት 110 ሺህ ብቻ መሆናቸው በዛሬው መርሃግብር ላይ ተገልጿል። ይህ አሃዝ፤ በአጠቃላይ በኢትዮቴሌኮም ኔትወርክ ጋር ከተያያዙ 76 ሚሊዮን ገደማ ቀፎዎች ጋር ሲነጻጸር “በጣም ትንሽ” መሆኑን የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ጠቅሰዋል። (በተስፋለም ወልደየስ- ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)