በሃሚድ አወል
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን ስር ከሚገኘው የአሶሳ ማረሚያ ቤት 17 ተጠርጣሪዎች ማምለጣቸውን የዞኑ ማረሚያ ቤት መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ጠይባ መሐመድ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ካመለጡት ተጠርጣሪዎች ጋር አብረው ለማምለጥ ሙከራ ያደረጉ ሁለት እስረኞች መያዛቸውንም ኃላፊዋ ገልጸዋል።
ተጠርጣሪዎቹ ከማረሚያ ቤቱ ያመለጡት ትላንት ሐሙስ ግንቦት 11፤ 2014 አመሻሽ ላይ መሆኑን ኮማንደር ጠይባ አስረድተዋል። ከማረሚያ ቤቱ ያመለጡት ግለሰቦች “በወቅታዊ ሁኔታ እና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት” ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ናቸው ያሉት ኃላፊዋ፤ ከእነርሱ ውስጥ የተወሰኑት ትላንት ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር ብለዋል።

ኮማንደር ጠይባ ተጠርጣሪዎቹ ያመለጡት “ቆጠራ እየተከናወነ ባለበት ሰዓት ሮጠው በአጥር ዘልለው” መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ታሳሪዎቹን ለመያዝ የሞከረ የማረሚያ ቤቱ ፖሊስ ጉዳት እንደደረሰበትም አክለዋል።
“ተከትሏቸው የሮጠ አባል በዱላ ተመትቶ ሲወድቅ፤ መሳሪያው ተነጥቆ አንድ መሳሪያ ይዘው ሄደዋል” ሲሉ ኃላፊዋ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ገልጸዋል። በወቅቱ ተጠርጣሪዎቹን ለማስቆም የሞከረው የማረሚያ ቤቱ አባል በስለት ሶስት ቦታዎች ላይ መዋጋቱን እና አሁን በአሶሳ ሆስፒታል ህክምና ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
ተጠርጣሪዎቹ ከማረሚያ ቤቱ ካመለጡ በኋላ የአካባቢው ነዋሪዎቹ ወደ ማረሚያ ቤቱ መሰብሰባቸውን የሚገልጹት ኃላፊዋ፤ “ከነዋሪው ጋር የተቀላቀሉ እስረኞችም ይኖራሉ” ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል። ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ የዞኑ ማረሚያ ቤት ክትትል እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

“በየአቅጣጫው ከጠፉበት ሰዓት ጀምሮ ተከታትለው የሄዱ አሉ። ከዚያም በኋላ በየአቅጣጫው የተላኩ ሰዎች አሉ” ብለዋል ኮማንደር ጠይባ። በጉዳዩ ላይ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ከአሶሳ ማረሚያ ቤት እስረኛ ሲያመልጥ የአሁኑ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። በማረሚያ ቤቱ ታስሮ የነበረው የቀድሞው የቤኒሻንጉል ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ መሪ አቶ አብዱልዋሀብ መሀዲ ከሶስት ወራት በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ ማምለጡ ይታወሳል። የትላንቱ ክስተት ከአቶ አብዱልዋሀብ ጋር ግንኙነት ይኖረው እንደሆነ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው ኮማንደር ጠይባ “ከእርሱ ጋር ግንኙነት ይኑር አይኑራቸው አላውቅም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)