ኢሠፓን ዳግም ለማቋቋም የተሰባሰቡ አደራጆች፤ ከምርጫ ቦርድ ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ ለማግኘት እየተጠባበቁ መሆናቸውን አስታወቁ

በሃሚድ አወል

በደርግ ዘመነ መንግስት ገዢ ፓርቲ የነበረውን የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲን (ኢሠፓ) ዳግም ለማቋቋም የተሰባሰቡ ግለሰቦች፤ የምስረታ ሰነዶቻቸውን ለምርጫ ቦርድ አስገብተው ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ ለማግኘት እየተጠባበቁ መሆኑን አስታወቁ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፓርቲው የምስረታ ሰነዶች እንደደረሱት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጧል።

ኢሠፓን ከ30 ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ለመመለስ የተሰባሰቡት ግለሰቦች፤ የምስረታ ሰነዶችን ለምርጫ ቦርድ ያስገቡት ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ መሆኑን የፓርቲው አደራጆች ገልጸዋል። ከአደራጆቹ መካከል የሆኑ እና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ግለሰብ “የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን በሙሉ አሟልተን [ለቦርዱ] አስገብተናል” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

“በአዲስ መልክ ተመልሶ ይመሰረታል” የተባለለትን ኢሠፓን በማደራጀት ላይ ከሚገኙት ውስጥ የቀድሞው የፓርቲ አባላት ይገኙበታል ተብሏል። ከእነዚህ የቀድሞ አባላት ውስጥ በኢሠፓ በከፍተኛ አመራርነት ያገለገሉ እንዳሉበት እኚሁ አደራጅ ቢገልጹም፤ ማንነታቸውን ከመግለጽ ግን ተቆጥበዋል። 

ፎቶ፦ ይድነቃቸው ኃይሌ

የቀድሞዎቹ የኢሠፓ አመራሮች “በእስር ቤት ያለፉ ሰዎች ናቸው። ከስህተታቸው ብዙ ትምህርት ተምረዋል” የሚሉት አደራጁ፤ ግለሰቦቹ እንደገና በሚቋቋመው ፓርቲ የሚኖራቸው ሚና “ከኋላ ሆነው ልምዳቸውን የማካፈል” መሆኑን አስረድተዋል። በአደራጆቹ ስብስብ ውስጥ ከቀድሞዎቹ የኢሠፓ አመራሮች እና አባላት በተጨማሪ ወጣቶችም መካተታቸውን አክለዋል። 

“ ‘እናቴ ኢሠፓ ነበረች። አባቴ ኢሠፓ ነበር’ የሚሉ ብዙ ወጣቶች አሉ። የጦሩ ቤተሰቦችም በብዛት አሉ” ሲሉ ዳግም እየተዋቀረ በሚገኘው የሠራተኞች ፓርቲ ውስጥ በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት እንዲበተን የተደረገው የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰራዊት የቤተሰብ አባላት እንደተካተቱ አብራርተዋል። 

ኢሠፓን በዚህ ጊዜ በድጋሚ ለማቋቋም እንደተፈለገ የተጠየቁት አደራጁ፤ “አሁን ካለው ሁኔታ አንጻር ብዙ ደስ የማይሉ ነገሮች ስላሉ፤ በዚያ መንፈስ በኢትዮጵያ አንድነት ዙሪያ ባለው አቋም እና በቆራጥነቱ ብዙ ሰዎች ኢሰፓ ቢመጣ አይሻልም ወይ?” የሚሉ ፍላጎቶች ተደጋጋመው መንሸራሸራቸውን ተከትሎ መሆኑን አስረድተዋል። 

የኢትዮጵያ ሠራተኞች በይፋ ህልውና አግኝቶ የተመሰረትው ከ37 ዓመታት በፊት በመስከረም 1977 ዓ.ም ነበር። ፓርቲው ከተመሰረተ በኋላ እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ ለስድስት ዓመታት ኢትዮጵያን አስተዳድሯል። የደርግ መንግስት ከወደቀ እና አማጽያኑ የማዕከላዊ መንግስቱን ስልጣን ሲቆጣጠሩ፤ የፓርቲው ዋና ጸሐፊ እና የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት የነበሩት ኮሎኔል መንግስት ኃይለማሪያምን ጨምሮ የተወሰኑ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ሀገሪቱን ጥለው በመውጣት ለስደት ተዳርገዋል። አብዛኞቹ የፓርቲው አመራሮች እና አባላት ደግሞ ለዓመታት በእስር ቆይተዋል።

ኢሠፓ ቀድሞ ያቀንቅነው የነበረው ርዕዮተ ዓለም ይዞ ይቀጥል እንደሆነ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው አደራጁ፤ “የድሮውን ይዘን አይደለም የመጣነው። በአዲስ መልክ ነው የሚደራጀው። በአጠቃላይ ያለፉትን ስህተቶች ነቅሶ አውጥቶ እና አሻሽሎ አዳዲስ ነገሮችንም ጨምሮ የመጣ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ፓርቲው የሚከተለው ርዕዮተ ዓለም ወደ “ሊበራሊዝም” ያጋደለ እንደሚሆንም ጠቁመዋል። 

“ይበልጥ ሊብራል የሆነ እና ሁሉን አካታች የሆነ፤ በአዲስ መልኩ ዘመኑን የዋጀ ሀሳብ [ያለው ነው]። ለምሳሌ የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት ያከበረ ግን ከወቅቱ ጋር አብረው የሚሆኑ ሀሳቦችን የያዘ ነው። የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት በፊት አይከበርም ማለቴ ግን አይደለም” ሲሉ ከፓርቲው አደራጆች አንዱ የሆኑት ግለሰብ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በሀገር አቀፍ ፓርቲነት የሚመሰረተው አዲሱ ኢሠፓ “በዘር እና በጎሳ ላይ የማይመሰረት፤ በኢትዮጵያ እና በሀገር አንድነት ላይ ትኩረት የሰጠ ድርጅት ነው” ሲሉም አክለዋል።

ፎቶ፦ ዶ/ር ዮናስ አሽኔ

ኢሠፓን በድጋሚ ለመመስረት እየተንቀሳቀሱ ያሉት አደራጆች፤ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያስገቧቸው ሰነዶች ተቀባይነት አግኝተው ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ ሲሰጣቸው የፓርቲውን የፖለቲካ ፕሮግራም በሰፊው ለማስተዋወቅ ወጥነዋል። የቦርዱን ጊዜያዊ ፍቃድ ይዘው ለፓርቲው ምስረታ የሚያስፈልጉ ፊርማዎችን ለማሰባሰብ እና አባላትን ለመመልመልም አቅደዋል። 

የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ፤ የፖለቲካ ፓርቲ ለማቋቋም የሚፈልጉ ዜጎች ከቦርዱ ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ይደነግጋል። ቦርዱ የሰነዶችን መሟላት አረጋግጦ የሚሠጠው ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ የሚያገለግለው ለሶስት ወራት ሲሆን አመልካቾች በቂ ምክንያት ካቀረቡ ለተጨማሪ ሶስት ወራት ሊራዘም ይችላል።

ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ ያገኘ ፓርቲ ፍቃዱን የሚጠቀመው፤ ፓርቲውን ለማስመዝገብ የሚያስፈልጉ ተግባራትን ለማከናወን ብቻ መሆኑ በአዋጁ ተደንግጓል። አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በሀገር አቀፍ ፓርቲነት የሚመሰረተው 10 ሺህ መስራች አላት ሲኖሩት እንደሆነ በአዋጁ ሰፍሯል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የኢሠፓ አደራጅ፤ “ከሚጠበቀው በላይ መስራች አባላት እንደምናገኝ እናስባለን” ሲሉ በአዋጁ የተቀመጠውን መስፈርት ለማሟላት እንደማይቸገሩ በልበ ሙሉነት ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)