በሃሚድ አወል
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 18፤ 2014 በዋለው ችሎት፤ አንድ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የስራ ኃላፊ ታስረው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጠ። በፖሊስ ኮሚሽኑ የስራ ኃላፊ ላይ ትዕዛዙ የተላለፈው፤ በእስር ላይ ከሚገኙት የብሔራዊ ባይቶ አባይ ትግራይ (ባይቶና) ፓርቲ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ክብሮም በርኸ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ነው።
በፌደራል ፖሊስ ታስረው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ የተሰጠባቸው፤ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በወንጀል ምርመራ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት ስር ያሉ ኃላፊ ናቸው። በጽህፈት ቤቱ የሰው መግደል ወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት የሙስና ወንጀሎች ምርመራ ዲቪዥን ኃላፊው ታስረው ይቅረቡ የተባለው፤ አቶ ክብሮም ከእስር ያልተፈቱበትን ምክንያት ለፍርድ ቤት እንዲያስረዱ ታዝዘው በተከታታይ ሊቀርቡ ባለመቻላቸው ነው።
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ሁለተኛ ልዩ ልዩ ችሎት ባለፈው ነሐሴ 6፤ 2014 በነበረው ቀጠሮ፤ የፌደራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኃላፊዎች ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። ለሁለቱ የጸጥታ ተቋማት ኃላፊዎች ትዕዛዙ ተላልፎ የነበረው፤ አቶ ክብሮም በርኸ ዋስትና ከተፈቀደላቸው በኋላ እስካሁን ከእስር ያልተፈቱበትን ምክንያት ለፍርድ ቤት እንዲያስረዱ ነው።
ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ነሐሴ 10፤ 2014 በነበረው የችሎት ውሎ የፌደራል ፖሊስ ተወካይ በአካል ቢቀርቡም፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኃላፊው ግን ተወካይ ልከው በፍርድ ቤት ሳይገኙ ቀርተዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወክለው ችሎት የተገኙት ግለሰብ “ኃላፊው ለአንድ ሳምንት በአስቸኳይ ሀገራዊ ጉዳይ ከከተማ ወጥተዋል” ሲሉ ኃላፊው ፍርድ ቤት ያልቀረቡበትን ምክንያት ለችሎቱ ገልጸው ነበር።
ፍርድ ቤቱ ለዛሬ ቀጠሮ በሰጠበት ወቅት፤ በችሎት ያልተገኙት ኃላፊ በሚቀጥለው ቀጠሮ በአካል ቀርበው አቶ ክብሮም ያልተፈቱበትን ምክንያት እንዲያስረዱ በድጋሚ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። ሆኖም ትዕዛዙ የተላለፈላቸው የስራ ኃላፊ ዛሬ በነበረው የችሎት ቀጠሮም አልቀረቡም።
ይህንን ተከትሎም የአቶ ክብሮም ጠበቃ “ፍርድ ቤቱ ይሆናል በሚለው መንገድ፤ ጉዳዩን የበለጠ ይፈታል ብሎ የሚያምነውን ትዕዛዝ እንዲሰጥልን” ሲሉ ችሎቱን ጠይቀዋል። ጥያቄውን ያደመጡት የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኃላፊ በችሎት ያልቀረቡ በመሆኑ “የፌደራል ፖሊስ አስሮ እንዲያቀርባቸው” ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሰው የተቃዋሚው ባይቶና ፓርቲ አመራር የሆኑት አቶ ክብሮም በርኸ በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የዋሉት ከአንድ ወር ገደማ በፊት ሐምሌ 3፤ 2014 ነበር። አቶ ክብሮም ከተያዙ ከሁለት ቀናት በኋላ፤ በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቃቂ ምድብ ችሎት የቀረቡ ሲሆን ፍርድ ቤቱ በሁለት ሺህ ብር ዋስትና እንዲፈቱ ወስኖላቸው ነበር።
የአቶ ክብሮም ቤተሰቦች የዋስትና ገንዘቡን ቢከፍሉም፤ የባይቶናው አመራር ከእስር ባለመለቀቃቸው እና ከፍርድ ቤት ውሳኔ በኋላ የታሰሩበትን ቦታ መታወቅ ባለመቻላቸው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደውታል። በተጠርጣሪው ጠበቃ በአቶ ወንድወሰን በፍቃዱ በኩል፤ ባለፈው ወር ሐምሌ 12፤ 2014 ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት “አካልን ነጻ የማውጣት” (habeas corpus) አቤቱታ አስገብተዋል።
“አካልን ነጻ የማውጣት” አቤቱታው በፍርድ ቤት እየታየ ባለበት ወቅት፤ አቶ ክብሮም ቀደም ሲል ተወስደው ከነበረበት አዋሽ ሰባት ኪሎ ወደ አባ ሳሙኤል ማረሚያ ቤት መዘዋወራቸውን ባለቤታቸው ትዝታ ኃይለ ሰንበት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የባይቶናው አመራር ከሐምሌ 6 እስከ ነሐሴ 11 በአፋር ክልል በሚገኘው አዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ በእስር ላይ እንደነበሩ እንደነገሯቸው ባለቤታቸው ገልጸዋል።
አቶ ክብሮም በአዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ በእስር ላይ በቆዩበት ወቅት፤ የፌደራል ፖሊስ በአፋር ክልል ፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት እንዳቀረባቸው መናገራቸውንም ባለቤታቸው አክለዋል። ፖለቲከኛው በወረዳው ፍርድ ቤት የቀረቡት “ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት ወንጀል” ተጠርጥረው መሆኑን አቶ ክብሮምን ዋቢ አድርገው ባለቤታቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)