ከስልጤ ዞን አልቾ ውሪሮ ወረዳ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ በነበሩ ተሽከርካሪዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ጉዳት ደረሰ

በሃሚድ አወል

ከደቡብ ክልል ስልጤ ዞን አልቾ ውሪሮ ወረዳ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ በነበሩ ተሽከርካሪዎች ላይ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት፤ የአንድ አሽከርካሪ ህይወት ሲያልፍ ሶስት የጭነት እና አንድ የህዝብ ማመላለሻ ሚኒባስ ተሽከርካሪዎች በቃጠሎ መውደማቸውን አንድ የወረዳው ባለስልጣን እና የዓይን እማኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ጥቃቱ የተፈጸመበት አካባቢ፤ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ክስተት አስተናግዶ የማያውቅ ነው ተብሏል።

ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ነሐሴ 19፤ 2014 እኩለ ሌሊት ገደማ የተፈጸመው ይህ ጥቃት የተሰነዘረበት ቦታ፤ በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የሚገኝ እና የጉራጌ ዞንን የሚያዋስን መሆኑን የአልቾ ውሪሮ ወረዳ የኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰማን ኸይረዲን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ከሆሳዕና በቡታጅራ ወደ አዲስ አበባ በሚወስደው ዋና መንገድ የተፈጸመው ይህ ጥቃት በአካባቢው ያልተለመደ መሆኑን ኃላፊው አክለዋል።

ፎቶ፦ የአልቾ ውሪሮ ወረዳ የኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት

“ሽፍቶች በአካባቢው አልፎ አልፎ መኪኖችን አስቆመው ብር ይጠይቁ ነበር። እንዲህ አይነት ጥቃት ግን ተከስቶ አያውቅም” ሲሉ የወረዳ የኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሰማን ተናግረዋል። የትላንት በስቲያውን ጥቃት የፈጸሙት ታጣቂዎች በአካባቢው ከዚህ ቀደም ይንቀሳቀሱ ከነበሩ ሽፍቶች የሚለዩበትን ሲያስረዱ፤ “እነዚህ የብር ጥያቄ የላቸውም። መንገድ አስቁመው፤ እናልፋለን የሚሉ መኪናዎችን እዚያው የጥይት እሩምታ ነው ያወረዱባቸው” ብለዋል።

ከአልቾ ውሪሮ ወደ አዲስ አበባ በሚወስደው መንገድ በተደጋጋሚ የሚመላለሰው ሰይፈዲን ሲራጅ የተባለ ሹፌር፤ “[በዚህ መስመር] ሁለት ዓመት ሰርተናል። አንድም ነገር ያየነው የለም” ሲል አካባቢው ሰላማዊ እንደነበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል። በትላንት በስቲያው ጥቃት ቀኝ እግሩ ላይ በጥይት ተመትቶ ጉዳት የደረሰበት ሰይፈዲን፤ ጥቃቱ የተፈጸመው በኦሮሚያ ክልል ተሬ እና ሌመን ከተማ መካከል በሚገኝ አካባቢ መሆኑን አስረድቷል።

ከአልቾ ውሪሮ ወረዳ በሚያሽከረክረው አይሱዙ የጭነት መኪና፤ ጎመን እና ቅመማ ቅመም ጭኖ ተሬ ከተማን እንዳለፈ ታጣቂዎች በተኩስ እንዳስቆሙት የሚናገረው ሰይፈዲን፤ እርሱም መኪናውም በጥይት ከተመቱ በኋላ ከረዳቱ ጋር ነፍሳቸውን ለማትረፍ ወደ ጫካ መግባታቸውን ገልጿል። “ዘልለን ጫካ እንደገባን፤ ከአንድ ደቂቃ በኋላ መኪናው ላይ እሳት ለቀቁበት። እኛ ጫካ ሆነን እያየን ነበር” ሲል በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ አብራርቷል።  

ፎቶ፦ የአልቾ ውሪሮ ወረዳ የኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት

ሰይፈዲን ታጣቂዎቹ ከዚህ በፊት ከተማ መግቢያ ላይ የሚያገኛቸው “የኦሮሚያ ልዩ ኃይል መስለውኝ ነበር” ይላል። “እነዚያ [ልዩ ኃይሎቹ] በእጅ ምልክት ነበር የሚያስቆሙት። እነዚህ ገና የመኪናውን ድምጽ ከሩቅ ሲሰሙ ተኩስ ከፈቱብን” ሲል ታጣቂዎች በቀጥታ እርምጃ ወደ መውሰድ መግባታቸውን አስታውቋል። ታጣቂዎቹ “የድሮውን የመከላከያ [የደንብ] ልብስ የለበሱ ናቸው” የሚለው አሽከርካሪው፤ “በደንብ የታጠቁ” መሆናቸውንም አክሏል። 

እምብዛም ጥቃት ባልተለመደበት አካባቢ የደረሰውን ጥቃት የፈጸሙ አካላትን በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የአልቾ ውሪሮ ወረዳ የኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ፤ “ሸኔ ነው የሚባል ነገር አለ። ግን እኛ አላረጋገጥንም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ጥቃቱ በደረሰበት ዕለት ተረኛ የነበሩ እና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የኬላ ፖሊስ በበኩላቸው “ማንነታቸው ሽፍታ ይሁን ሸኔ ይሁን ተለይቶ ገና አልታወቀም” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ በመንገዱ የሚመላለሱ ተሸከርካሪዎች በኦሮሚያ ልዩ ኃይል ታጅበው እየተጓዙ መሆኑን የፖሊስ አባሉ ጨምረው ገልጸዋል። የአልቾ ውሪሮ ወረዳ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊም መንገዱ በአሁኑ ወቅት ለአገልግሎት ክፍት መሆን አረጋግጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)