ስለ ኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ምን አለ? 

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ትላንት ረቡዕ የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት፤ የሁለት ዓመታቱ ደም አፋሳሽ ጦርነት በድርድር እንዲቋጭ ግፊት ሲያደርግ ከቆየው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አዎንታዊ ምላሽ አግኝቷል። የኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራት መሪዎች እና ሌሎች የአፍሪካ ፖለቲከኞችም አድናቆታቸውን ገልጸዋል። 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፤ ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች የተፈራረሙት ስምምነት “የበርካታ ኢትዮጵያውያን ህይወት እና መተዳደሪያ የጠፋበትን የሁለት ዓመት ጦርነት ለማቆም ወሳኝ እርምጃ” ሲሉ ገልጸውታል። ዋና ጸሀፊው የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ህወሓት ወስደውታል ያሉትን “ደፋር እርምጃ”፤ የአገሪቱ ህዝብ እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት በተፈራረሙት ስምምነት ለተካተቱ ጉዳዮች ተግባራዊነት እገዛ እንደሚያደርጉ ቃል የገቡት ዋና ጸሀፊው፤ ሁለቱ ወገኖች ዘላቂ የፖለቲካ መፍትሔ ለማበጀት እና አገሪቱን ወደ ሰላም እና መረጋጋት ለመመለስ “በዕርቅ መንፈስ በዋና ዋና ልዩነቶቻቸው ላይ ድርድር” እንዲቀጥሉ አበረታተዋል። ይህን ስምምነት ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ለተቸገሩ ሰላማዊ ሰዎች ሁሉ የሚሰጠውን ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማሳደግ እና እጅጉን የሚፈለጉ መሰረታዊ አገልግሎቶች ወደነበረበት ለመመለስ እንዲጠቀሙበት ጉተሬዝ አሳስበዋል።

ለሁለት ዓመት ያህል በተካሄደ ደም አፋሳሽ ጦርነት ሲዋጉ የቆዩ ኃይሎች ለድርድር እንዲቀመጡ ግፊት ስታደርግ የቆየችው አሜሪካም ለሰላም ስምምነቱ ተመሳሳይ አድናቆቷን ገልጻለች። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፤ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ህወሓት ግጭት ለማቆም እና በዋና ዋና ልዩነቶቻቸው ላይ ድርድር ለመቀጠል በመስማማታቸው አሞግሰዋል። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር ጋር በስልክ ከተነጋገሩ በኋላ ባወጡት መግለጫ፤ አሜሪካ በመጪዎቹ ሳምንታት በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን ጥረት ለመደገፍ ተሳትፎዋን እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል። 

ብሊንከን የሚመሩት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ የሆኑት ኔድ ፕራይስ፤ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ካነሷቸው ዐበይት ጉዳዮች መካከል አንዱ አድርገውታል። በመግለጫው ላይ ከተገኙ ጋዜጠኞች ከቀረቡ ጥያቄዎች ውስጥ፤ የፕሪቶሪያው የስምምነት ፈራሚዎች ይፋ ያደረጉት “የህወሓት ትጥቅ መፍታት” እንዲሁም “የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ መውጣት ምን ያህል ይሳካል?” የሚለው አንዱ ነበር። 

ኔድ ፕራይስ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ የአፍሪካ ህብረት እንደ ሰላም ንግግሩ ሰብሳቢነቱ “ስለ ዝርዝር ጉዳዮች ቢያብራራ ይሻላል” ብለዋል። የአፍሪካ ህብረት ሂደቱን መምራቱን ይቀጥላል ያሉት ኔድ ፕራይስ፤ አገራቸው ህብረቱ፣ ንግግሩን ከሚያመቻቹ የቀጠናው ወገኖች፣ ከኢትዮጵያ መንግስት እና ከህወሓት ጋር የሚኖራት ግንኙነት እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት በአፋጣኝ ተግባራዊ መሆን እንደሚኖርበት ጥሪ አቅርቧል። ህብረቱ ትላንት ረቡዕ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ባወጣው መግለጫ “በሁሉም የተጎዱ አካባቢዎች በተለይም በትግራይ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እና መሰረታዊ አገልግሎቶችን ወደነበሩበት መመለስ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ” ሊሆን እንደሚገባ አሳስቧል።

የትላንቱን ስምምነት ተከትሎ መልዕክታቸውን ካስተላለፉ አፍሪካውያን ፖለቲከኞች መካከል የሱዳን ምክትል ወታደራዊ መሪ መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ይገኙበታል። ዳጋሎ “የኢትዮጵያን ወንድማማች ህዝቦች አንድነት እና መረጋጋት ለማስጠበቅ” የስምምነቱ ፈራሚዎች አሳዩት ያሉትን “ቀና መንፈስ” አድንቀዋል። የቀድሞዋ የላይቤሪያ ፕሬዝደንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ በበኩላቸው በፕሪቶሪያ የተፈረመው ስምምነት “በውይይት እና ፖለቲካዊ ግንኙነት ወደሚገነባ ለዘላቂ ሰላም የሚመራ የመጀመሪያው እርምጃ” እንደሚሆን ተስፋቸውን ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)