ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሰሜን ኢትዮጵያ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው ቦታዎች “በሀገሪቱ ህግ ብቻ ምላሽ” እንደሚያገኙ አስታወቁ 

በደቡብ አፍሪካ ላይ በነበረው ድርድር ኢትዮጵያ የቀረበችው ሀሳብ “መቶ በመቶ ተቀባይነት አግኝቷል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው ቦታዎችም “በሰላም እና በድርድር እንዲሁም በሀገሪቱ ህግ ብቻ ምላሽ እንዲያገኙ” ከስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል በትላንትናው ዕለት በደቡብ አፍሪካ የተደረገውን የሰላም ስምምነት አስመልክቶ ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 24 በአርባ ምንጭ ስቴድየም ባደረጉት ንግግር ነው። አብይ በዚሁ ንግግራቸው፤ የሰላም ስምምነቱን ለኢትዮጵያ “ታላቅ ዕድል ነው” ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከተዘረዘሩት የትላንቱ የሰላም ስምምነት አንኳር ነጥቦች መካከል፤ በተፋላሚ ወገኖች “የይገባኛል ጥያቄ” የሚነሳባቸው ቦታዎችን የተመለከተው ይገኝበታል። “በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው እና አከራካሪ የሆነ ቦታዎች፤ ዳግም የሰው ልጆችን ህይወት ሳይነጥቁ፤ በሰላም፣ በድርድር እና በሀገሪቱ ህገ መንግስት መሰረት ብቻ ምላሽ እንዲያገኙ በሁለቱም ወገኖች ከመተማመን ተደርሷል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። 

በዛሬው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የተነሳው ሌላ አዲስ ጉዳይ፤ በትግራይ ተካሄዶ የነበረው ክልላዊ ምርጫ የወደፊት ዕጣ ፈንታን የተመለከተ ነው። “ህጋዊ እና ህጋዊነትን ማስፈን ለአንድ ሀገር ህልውና መሰረት ስለሆነ፤ የራሳችንን ህግ የማናከብር፣ ማሻሻል ሲኖርብንም በህግ አግባብ የማናደርግ ከሆነ፤ ተቋማዊነት ሀገር የሚለው ቁመና ስለሚሸረሸር፤ ህገ ወጥ በሆነ መንገድ የተደረገው ምርጫ በህጋዊ ምርጫ መተካት አለበት የሚለውም በሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት አግኝቷል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በብሔራዊ ቴሌቪዥን በቀጥታ በተላለፈ ንግግራቸው አስታውቀዋል።

በአርባ ምንጭ ስቴድየም በነበረው ታዳሚ ተደጋጋሚ ጭብጨባ ይቋረጥ በነበረው በዛሬው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ለሰላም ስምምነቱ ፈተናዎች ሊሆኑ የሚችሉ ተግዳሮቶችም ተጠቅሰዋል። ብዙ ጊዜ ከሰላም ድርድር በኋላ “ሸፍጦች፣ ተንኮሎች እና ደባዎች ይታያሉ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “እኛ ልባችንን ከፍተን ሰላም ለማምጣት ዝግጁ ነን” ሲሉ ተደምጠዋል። በተፈረመው ስምምነት መሰረት “የተገባውን ቃል ለመጠበቅ” የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን የበኩል ሚና እንዲወጣም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጥሪ አቅርበዋል። 

“ተንኮል፣ ክፋት፣ ሸር እዚህ ጋር እንዲበቃ፤ ጥቂቶች እየሸረቡ ዳግም ኢትዮጵያውያንን አደጋ ውስጥ እና ጦርነት ውስጥ እንዳያስገቡ፤ ህዝባዊ፣ ኢትዮጵያዊ፣ ዜግነታዊ ሚናችሁን እንድትወጡ ለትግራይ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በታላቅ ትህትና አደራ ማለት እፈልጋለሁ” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)