ኢዜማ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ካሉ የታጠቁ ኃይሎች ጋር በሚደረግ ሰላማዊ ንግግር መፍትሔ እንዲፈለግ ጠየቀ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ካሉ የታጠቁ ኃይሎች ጋር በሚደረግ ሰላማዊ ንግግር መፍትሔ እንዲፈለግ ጠየቀ። ፓርቲው ዛሬ ሐሙስ በሰጠው መግለጫ፤ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት “መርህን የተከተለ” ነው ብሏል። 

ኢዜማ የዛሬውን ጋዜጣዊ መግለጫ የጠራው በደቡብ አፍሪካ የተደረገውን የሰላም ስምምነት በማስመልከት መሆኑን አስቀድሞ አሳውቆ የነበረ ቢሆንም፤ አብዛኛውን የመግለጫ ጊዜ የወሰደው ግን ዛሬ ሁለተኛ ዓመቱን ለደፈነው የሰሜኑ ጦርነት የተዘጋጀ ዝክር ነበር። በኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ሙሉዓለም ተገኘወርቅ በንባብ የቀረበው መግለጫ፤ ፓርቲው የሰላም ስምምነቱን በተመለከተ ያለውን አቋም ያሳወቀበት ነው።   

የትላንቱን የሰላም ስምምነት “ይበል የሚያሰኝ መልካም ጅማሮ” ሲል በመግለጫው የጠራው ኢዜማ፤ “መንግስት የተደረገውን ስምምነት እንዳይጨናገፍ እና ተመልሰን የጦርነት አዙሪት ውስጥ እንዳንገባ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል” ሲል አሳስቧል። “የሀገር ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለማስከበር ትጥቅ ይዞ የሚንቀሳቀስ እና የማዘዝ ስልጣን ሊኖረው የሚገባው፤ የፌደራል መንግስት ብቻ ስለመሆኑ ሀገራዊም ዓለም አቀፋዊ ድንጋጌዎች አስረግጦ በማስገንዘብ፤ ህወሓት ትጥቁን እንዲፈታ ሊደረግ ይገባል” ሲል ፓርቲው አቋሙን አስረግጧል። 

የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ ለ10 ቀናት ሲያካሄዱ የቆዩትን የሰላም ንግግር ካጠናቀቁ በኋላ ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን ማስጠበቅ እንዲሁም በሀገሪቱ የሚኖረው “አንድ የመከላከያ ኃይል ብቻ” መሆኑን በተመለከተ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል። ሁለቱ ወገኖች “በመሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ የህወሓት ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ እንዲበተኑ ማድረግ እና እንደገና መዋሃድ በሚያስችል ዝርዝር መርሃ ግብር” መስማማታቸውንም ገልጸዋል። 

ኢዜማ ትላንት የተደረገው የሰላም ስምምነት “መርህን የተከተለ ነው” በሚል አድናቆቱን ቢገልጽም፤ የፓርቲው አመራሮች ግን የሰላም ንግግሩ ከጦርነቱ አስቀድሞ መደረግ ነበረበት የሚለውን አቋማቸውን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ አንጸባርቀዋል። ይህንኑ አቋም ያስተጋቡት የፓርቲው ዋና ጸሐፊ አቶ አበበ አካሉ “የትላንትናው የሰላም ድርድር ከሁለት ዓመት በፊት ቢደረግ የበርካታ ዜጎች ህይወት አይቀጠፍም ነበር። የሀገር ሀብትም አይወድምም ነበር” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። 

ፓርቲው በዛሬው መግለጫው በመጨረሻ ያነሳው ጉዳይ፤ በሌሎች የሀገሪቷ ክፍሎች ያሉ “የታጠቁ ኃይሎችን” ጉዳይ ነው። ከእነዚህ ኃይሎች ጋር “ሰላማዊ ንግግር” ሊደረግ ይገባል የሚለውን አቋሙን ያሳወቀው ኢዜማ፤ ከታጣቂዎቹ ጋር “መፍትሄ የሚገኝበት መንገድ ላይ በአጽንኦት መስራት ያስፈልጋል” ሲልም በአጽንኦት አሳስቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)