የኢዜአ የቦርድ አባላት ሹመት፤ በፓርላማ አባላት “የአሰራር እና የብዝሃነት” ጥያቄ ቀረበበት

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ቦርድ አባላት ሹመት ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት የአሰራር (procedure) እና የብዝሃነት ጥያቄ ተነሳበት። የምክር ቤት አባላቱ ትላንት ሐሙስ ታህሳስ 13፤ 2015 በነበረው ስብሰባ “ሹመቱ ባለፈው ዓመት የተሰጠ ነው” የሚል አስተያየት አቅርበዋል።

ጥያቄዎችን እና አስተያየቶቹን ያሰሙት፤ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) ወክለው ፓርላማ የገቡ የምክር ቤት አባላት ናቸው። የኢዜማ ተወካዩ ዶ/ር አወቀ አምዛዬ ለምክር ቤቱ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ “የፕሮሲጀር ችግር” አለበት ሲሉ ተናግረዋል። “ይህ ሹመት የተሰጠው አምና በመጋቢት ወር ነው” ያሉት ዶ/ር አወቀ፤ “በ2014 የተሰጠ የሹመት ደብዳቤ አሁን የሚቀርበው ለምንድን ነው” የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል።

የአብን ተወካዩ አቶ ክርስቲያን ታደለም በተመሳሳይ የዶ/ር አወቀን አስተያያት እንደሚደግፉ በትላንትናው ስብሰባ ተናግረዋል። አቶ ክርስቲያን አክለውም “ሰዎቹ ዛሬ ቃለ መሐላ ፈጽመው ሹመቱን ይውሰዱት እንጂ፤ በተጨባጭ ስራ ላይ ነበሩ” ሲሉ የዶ/ር አወቀን አስተያየት አጠናክረዋል።

ዶ/ር አወቀ እና አቶ ክርስቲያን ላነሱት ሃሳብ፤ የፓርላማው አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ምላሽ ሰጥተዋል። አፈ ጉባኤው በምላሻቸው “ሰዎቹ አልተሾሙም። ዛሬ ነው የሚሾሙት። የኢዜአ አዋጅ የጸደቀው ቅርብ ጊዜ ነው። አዋጁን ሳናጸድቅ፤ አመራሩን ማጽደቅ ስለማንችል ነው” ሲሉ ሹመቱ እስካሁን ምክር ቤቱ ሳይጸድቅ የዘገየበትን ምክንያት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን አንደገና ለማቋቋም የወጣው አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው፤ ከአንድ ወር በፊት ባለፈው ህዳር ወር አጋማሽ ላይ ነበር። አፈ ጉባኤው ይህን ቢሉም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለኢዜአ ቦርድ አባልነት ያጯቸውን ግለሰቦች ዝርዝር የያዘውን ደብዳቤ ለተወካዮች ምክር ቤት የጻፉት፤ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማ ባቀረቡት የአባላት ዝርዝር መሰረት፤ ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ የኢዜአ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ተሹመዋል። በህዝብ አስተዳደር እና ፖሊሲ የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው ዶ/ር ቢቂላ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ነበሩ። ዶ/ር ቢቂላ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስቴር ነበሩ።  

ዶ/ር ቢቂላ ካለፈው ጥቅምት ወር መጀመሪያ ጀምሮ የኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል። ዶ/ር ቢቂላ ወደ ኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ጽህፈት ቤት የሄዱት ኃላፊነታቸውን ለአቶ ሳዳት ነሻ አስረክበው ነው። አቶ ሳዳት የብልጽግና ፓርቲ የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ሆነው ከመሾማቸው በፊት በኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ  ጽህፈት ቤት  የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ነበሩ። 

በኢዜአ ቦርድ አባልነት ሹመትን ካገኙት ውስጥ አቶ ነብዩ ባዬ ይገኙበታል። ላለፉት ሁለት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት አማካሪ ሆነው ሲሰሩ የቆዩት አቶ ነብዩ፤ ካለፈው ህዳር ወር አጋማሽ ላይ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው መሾማቸው ያታወሳል። 

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት አቶ መሐመድ ራፊዕ አባራያ ሌላኛው የኢዜአ ቦርድ አባል ተሿሚ ናቸው። ዛሬ በፓርላማ ሹመታቸው ከጸደቀላቸው ስድስት የቦርድ አባላት መካከል ሁለቱ ሴቶች ናቸው። እነዚህ የቦርድ አባላት፤ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዲኤታ ሁሪያ አሊ እና ወ/ሮ ሚሊዮን ተረፈ ናቸው።  

የቦርድ አባላቱ ስብጥር ላይ አስተያየት የሰጡት የአብን ተመራጩ አቶ ክርስቲያን ታደለ፤ “ብዝሃነቱ ላይ ጥያቄ አለኝ” ሲሉ ተደምጠዋል። አቶ ክርስቲያን አክለውም ከቦርድ አባላቱ መካከል ግማሾቹ “በብሔረሰብ ደረጃ ተቀራራቢ ናቸው” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። 

ከብሔር ስብጥር በተጨማሪም አብዛኛዎቹ አባላት “የአንድ ፓርቲ አባላት እና  በተለያየ ደረጃ የሚገኙ አመራሮች ናቸው” ያሉት አቶ ክርስቲያን፤ “ኢትዮጵያ ብልጽግና ፓርቲን ብቻ ነው ወይ የምትመስለው?” የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል። “ኢዜአ የዲሞክራሲ ተቋም ነው። የሃሳብ ብዝሃነት እንዲያስተናግድ እንፈልጋለን” ያሉት የፓርላማ አባሉ፤ “ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ጊዜ የመንግስት እና የህዝብ ሚዲያዎች፣ የዲሞክራሲ ተቋማት ለገዢው ፓርቲ ብቻ የሚያደሉ የሚመስሉ ነገሮችን ሲሰሩ ይስተዋላል” የሚል ጠንከር ያለ አስተያየት ሰጥተዋል። 

የቦርድ አባላቱን ሹመት የያዘውን የውሳኔ ሃሳብ በንባብ ያሰሙት በፓርላማ ረዳት የመንግስት ተጠሪዋ ወይዘሮ መሰረት ኃይሌ፤ ከአባላቱ የተነሱት “አብዛኛዎቹ አስተያየት እና የማጠናከሪያ ሃሳብ ናቸው” ከማለት ባለፈ ለተነሱ ጥያቄዎች ቀጥተኛ ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል። ይህን ተከትሎም ፓርላማው በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የቀረበውን የኢዜአ ቦርድ አባላት ሹመት በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል። 

የተወካዮች ምክር ቤት የስድስቱን የቦርድ አባላት ሹመት ያጸደቀው፤ በአምስት ተቃውሞ እና በሰባት ድምጸ ተዐቅቦ ነው። በኢዜአ ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት የተቋሙ ቦርድ ተጠሪነቱ ለተወካዮች ምክር ቤት ነው። ቦርዱ የተቋሙን ሰራተኞች ቅጥር እድገት የሚመለከት መመሪያ የማውጣት ስልጣን አለው። በተጨማሪም ቦርዱ “በአገልግሎቱ የሚዘጋጁ ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎች እንዲሁም ፕሮግራሞች የተለያዩ አመለካከቶችንና አስተያየቶችን በሚያስተናግድ መልኩ መቅረባቸውን” የማረጋገጥ ኃላፊነት በአዋጁ ተጥሎበታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)