የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት የነበሩት የፓርላማ አባል ያለመከሰስ መብት ተነሳ

በሃሚድ አወል

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶ/ር ጫላ ዋታ ያለመከሰስ መብት ተነሳ። የፓርላማ አባሉ ያለመከሰስ መብት የተነሳው፤ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት “ከመንግስት ሕግ ውጪ ተፈጽመዋል” የተባሉ ግዢዎች እና የፋይናንስ አስተዳደር ጉድለቶችን “ለመፈጸማቸው በቂ አመላካች ሁኔታዎች” በመኖራቸው ነው ተብሏል።

ዶ/ር ጫላ ዋታ ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ቀርጫ ምርጫ ክልልን ወክለው ወደ ፓርላማ የገቡ ናቸው። የገዢው ብልጽግና ፓርቲን የወከሉት እኚሁ ተመራጭ፤ የተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆናቸው በህግ የተሰጣቸውን “ያለመከሰስ መብት” እንዲነሳ የውሳኔ ሀሳብ የቀረበባቸው በፓርላማው የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ነው።   

ቋሚ ኮሚቴው ያለመከሰስ መብት ማንሳትን የተመለከተውን የውሳኔ ሃሳብ ያዘጋጀው፤ ይህንኑ አስመልክቶ በፍትሕ ሚኒስቴር አማካኝነት ለተወካዮች ምክር ቤት የቀረበ ጥያቄ ከተመራለት በኋላ መሆኑን አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ተናግረዋል። ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 26፤ 2015 በተካሄደ የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ በንባብ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ፤  ዶ/ር ጫላ  የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት ተፈጽመዋል የተባሉ የግዢ እና የአስተዳደር ጉድለቶችን የዘረዘረ ነበር። 

በፓርላማው የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እጸገነት መንግስቱ የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ በቀዳሚነት የተጠቀሰው፤ “BHU Consulting Engineers General Level 1 ከተባለ አማካሪ ድርጅት ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው። በዶ/ር ጫላ የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንትነት ዘመን የተቋቋመው ይህ ድርጅት፤ “ከመንግስት ግዢ ህጎች ውጪ” 195 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን የግንባታ እቃዎች ከዘጠኝ ተቋራጮች በቀጥታ  እንዲገዛ ማድረጉ በውሳኔ ሃሳቡ ላይ ተጠቅሷል። 

የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ለካፒታል በጀት ከተፈቀደለት ገንዘብ ላይ፤ ለእነዚሁ ተቋራጮች “የግዢ ህግ እና ደንብን ባልተከተለ መልኩ” ተሽከርካሪዎች እና ማሽነሪዎች እንዲገዙ ማድረጉም በውሳኔ ሃሳቡ ተገልጿል። በ116 ሚሊዮን ብር ዋጋ ለተቋራጮቹ ተገዙ የተባሉት ተሽከርካሪዎች እና ማሽነሪዎች ብዛት 14 ነው። ተሽከርካሪዎች እና ማሽነሪዎች የተገዙበት ዋጋ “እጅግ ተጋነነ” እንደሆነ በውሳኔ ሃሳቡ ላይ ተነስቷል። ለዚህም በማሳያነት የተጠቀሰው 3.3 ሚሊዮን ብር ለተገዛ አንድ “ደብል ጋቢና ፒክ አፕ” መኪና፤ በ6.1 ሚሊዮን ብር ሂሳብ ክፍያ እንዲፈጸም መደረጉ ነው። 

በዩኒቨርስቲው በጀት የተገዙት እነዚህ ተሽከርካሪዎች እና ማሽነሪዎች፤ “በግል ተቋራጮች ስም እንዲሆኑ መደረጉ”፤ ሌላው በውሳኔ ሃሳቡ በጉድለትነት የተጠቀሰ ጉዳይ ሆኗል። በዩኒቨርስቲው የተቋቋመው አማካሪ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ እና የቦርድ ዳይሬክተር ዶ/ር ጫላ መሆናቸው እና የተቋሙ ንግድ ፈቃዱም በስማቸው ያለ መሆኑም በውሳኔ ሀሳቡ ላይ ተጠቁሟል። ለዚሁ ድርጅት ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ የባንክ ሂሳብ 23.1 ሚሊዮን ብር ገቢ እንደተደረገለት የጠቀሰው የውሳኔ ሃሳቡ፤ ከድርጅቱ የባንክ ሂሳብ ላይ ደግሞ 2.1 ሚሊዮን ብር ለዶ/ር ጫላ ገቢ መደረጉን አትቷል። 

ዶ/ር ጫላ በስማቸው አዲስ አበባ ውስጥ አንድ ኮንዶሚኒየም ቤት ተገዝቶ መገኘቱ እና በባለቤታቸው ወ/ሮ ጸሀይ ኃይሉ ስም በ10 ሚሊዮን ብር ባለሶስት ወለል ህንጻ እና ግዢ መፈጸሙ ጉዳዩን ለማስረዳት በማስረጃነት ቀርበዋል። እነዚህ ማስረጃዎች በፍትሕ ሚኒስቴር የቀረቡለት የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴም፤ “ለድርጊቱ መፈጸም በቂ አመላካች ሁኔታዎች መኖራቸውን” እንዳረጋገጠ ለፓርላማ አባላት በተነበበው የውሳኔ ሀሳብ አስታውቋል።  

በቋሚ ኮሚቴው በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ በቅድሚያ እድል ያገኙት፤ ያለ መከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ጥያቄ የቀረበባቸው  ዶ/ር ጫላ ናቸው። ከግዢ እና ገንዘብ አስተዳደር ጋር በተያያዘ የተነሱት ጉዳዮች፤ ከዚህ ቀደም በኦዲት ግኝት ቀርበው ምላሽ እንደተሰጠባቸው ዶ/ር ጫላ ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል።

በእርሳቸው የስልጣን ዘመን በዩኒቨርስቲው የተቋቋመው “BHU Consulting Engineers General level 1” የተባለው አማካሪ ድርጅትም ቢሆን፤ ምስረታው “ህጋዊ መሰረት ያለው” መሆኑን አስረድተዋል። የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ፤ ዩኒቨርስቲዎች የገቢ ማመንጫ የሚሆኑ ድርጅቶችን ማቋቋም እንደሚችሉ መደንገጉን በመጥቀስም ይህንኑ ሀሳባቸውን አጠናክረዋል። 

“ከግዢ አሰራር ውጪ እና በተጋነነ ዋጋ ተገዝተዋል” የተባሉ ተሽከርካሪዎችን በተመለከተ ለቀረበባቸው ውንጀላ ምላሽ የሰጡት ዶ/ር ጫላ፤  “በፕሮጀክት ማዕቀፍ ውስጥ ለፕሮጀክት የተገዙ ናቸው እንጂ፤ በቀጥታ ለዩኒቨርስቲው የመኪና ግዢ ተብሎ የተከናወነ [አይደለም]” ሲሉ ተከራክረዋል። ተሽርካሪዎቹ በተጋነነ ዋጋ ስለመገዛታቸው በውሳኔ ሀሳቡ ላይ የቀረበውን ሀሳብ፤ “በወቅቱ አላየንም” ሲሉ በፕሬዝዳንትነት ቆይታቸው የተነሳ ጉዳይ አለመሆኑን ለፓርላማ አባላቱ ገልጸዋል።

በፕሬዝዳንትነት ይመሩት የነበረው ቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ፤ መሰረተ ልማቶች ያልተሟሉለት መሆኑን፣ በዚያን ወቅት በሀገሪቱ መረጋጋት እንዳልነበር እንዲሁም የኮቪድ ወረርሽኝ አዳዲስ አሰራሮችን ለመከተል አስገድዷቸው እንደነበር ዶ/ር ጫላ ለፓርላማው ባቀረቡት ማብራሪያ ላይ አስረድተዋል። “ከህግ ውጪ እና በተጋነነ ዋጋ ተፈጽመዋል” በተባሉት ግዢዎች ላይ “ክፍተት ከታየ በህግ አግባብ ሊታይ የሚችል” መሆኑን አንስተዋል። 

በእርሳቸው እና በባለቤታቸው ስም ተመዝገበው የተገኙ ንብረቶችን በተመለከተ በውሳኔ ሀሳቡ ላይ የቀረቡት ማስረጃዎች “ከስራው ጋር በቀጥታ ግንኙነትም የላቸውም” ሲሉም ተከራክረዋል። በፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው ለዩኒቨርስቲው ያደረጓቸውን ጥረቶችን በመጥቀስም፤ “ይህ ሁኔታ ያልተመቻቸው እና በርካታ ጥላቻ የነበራቸው ግለሰቦች ነበሩ” በማለትም ተናግረዋል። 

ከዶ/ር ጫላ አስተያየት በኋላ ሶስት የምክር ቤት አባላት አስተያየት እንዲሰጡ እድል የተሰጣቸው ሲሆን፤ ሁለቱ የውሳኔ ሀሳቡን ያቀረበው ቋሚ ኮሚቴ አባል ናቸው። ሁለቱ የምክር ቤት አባላት የዶ/ር ጫላ ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ የቀረበውን ሃሳብ ደግፈዋል። የመጨረሻውን እድል ያገኙት የምክር ቤት አባል ግን አስቀድሞ ከቀረቡት አስተያየቶች ለየት ያለ ሃሳብ ሰንዝረዋል። 

እኚህ የምክር ቤት አባል ያለመከሰስ መብት ማንሳት ጥያቄ “ከፖለቲካ ሂደት” እና “ከግለሰቦች ጥላቻ” በተያያዘ መልኩ ለምክር ቤቱ ይቀርባሉ የሚል ጥርጣሬ እንዳላቸው ተናግረዋል። የውሳኔ ሀሳብ የቀረበባቸው ዶ/ር ጫላ ከዚሁ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሀሳብ ማንሳታቸውም ይህንን ጥርጣሬያቸውን እንዳጠናከረላቸው ገልጸዋል። “ቋሚ ኮሚቴው በዚህ ልክ ከተከበሩ ዶ/ር ጫላ ጋር ተግባብቶበታል ወይ?” ሲሉም ጥያቄ አቅርበዋል። ቋሚ ኮሚቴው ከፍትሕ ሚኒስቴር ከቀረበለት ማስረጃ ባሻገር፤ በቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ተገኝቶ ምርመራ አድርጎ እንደሆነም ማብራሪያ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል።

ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እጸገነት፤ ቋሚ ኮሚቴው ዝርዝር የማጣራት ስራ የመስራት ኃላፊነት እንደሌለው አስረድተዋል። ጉዳዩን በተመለከተ በፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የቀረበው ሪፖርት ህጋዊ መሆኑን ያነሱት ወ/ሮ እጸገነት፤ ቋሚ ኮሚቴው ከዶ/ር ጫላ ጋር ባደረገው ውይይት “መተማመን ላይ የተደረሰባቸው” ጉዳዮች መኖራቸውንም ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል። 

ለጥያቄዎች ከተሰጠው ምላሽ በኋላ፤ በዛሬው የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ የተገኙ 248 አባላት ድምጽ ሰጥተዋል። በዚህም መሰረት የፓርላማ አባላት የዶ/ር ጫላን ያለመከሰስ መብትን በተመለከተ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ጉዳዩ ከአንድ ድምጽ ተዐቅቦ በስተቀር በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል። በድምጽ አሰጣጡ ላይ ድምፀ ተዐቅቦ ያስመዘገቡት ብቸኛው የፓርላማ አባል፤ “የግዢዎች እና የፋይናንስ አስተዳደር ጉድለቶችን ፈጽመዋል” ተብለው የተወነጀሉት ዶ/ር ጫላ ዋታ ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)