የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር 27 አባላት ያሉትን ካቢኔ ይፋ አደረገ

በአማኑኤል ይልቃል

በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው አዲሱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር 27 አባላት ያሉትን ካቢኔ ይፋ አደረገ። በአዲሱ ካቢኔ ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲሁም የሰላም እና ጸጥታ ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ሆነው የተሾሙ ሲሆን፤ ሌተናል ጄነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ ደግሞ በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ ያልተማከለ አስተዳደር እና ዴሞክራታይዜሽን ካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ሆነዋል።

ከተቋቋመ ሁለት ሳምንት ያስቆጠረው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የካቢኔ አባላቱን በይፋ ያስተዋወቀው ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 27፤ 2015 በመቐለ ከተማ ባካሄደው ስነስርዓት ነው። በዚህ ስነ ስርዓት ላይ የክልሉን መንግስት ሲመራ የነበረው የቀድሞ ካቢኔ፤ የአስፈጻሚነት ስልጣኑን በጊዜያዊ አስተዳደሩ ለተቋቋመው አዲሱ ካቢኔ አስረክቧል።

አዲሱ ካቢኔ የተዋቀረው ከህወሓት፣ ከትግራይ ኃይሎች፣ ከምሁራን እና ከብሔራዊ ባይቶ አባይ ትግራይ (ባይቶና) ፖለቲካ ፓርቲ የተውጣጡ አባላትን በማካተተት ነው። የካቢኔው 51 በመቶ ቦታ የተያዘው በህወሓት ሲሆን፤ ተቃዋሚው ባይቶና ፓርቲ ሁለት ቢሮዎችን በኃላፊነት የመምራት ዕድል አግኝቷል። ከትግራይ ኃይሎች በካቢኔው ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ያገኙት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ፣ ብርጋዴር ጄነራል ተኽላይ አሸብር፣ ሌተናን ጄነራል ፍሰሃ ኪዳኑ፣ ሜጀር ጄነራል ዘውዱ ኪሮስ እና ዶ/ር ከላሊ አድሃና ናቸው። 

ሌተናል ጄነራል ጻድቃንን ጨምሮ በትግራይ ምሁራን የተወከሉ አምስት አባላት በዚሁ የጊዜያዊ አስተዳደር ካቤኒ በኃላፊነት ተሹመዋል። ከተሿሚዎቹ ውስጥ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ እና ስልጠና ካቢኔ ሴክሬተሪያትን በኃላፊነት እንዲመሩ የተሾሙት ዶ/ር አልጋነሽ ተሰማ ይገኙበታል። በትግራይ ምሁራን የተወከሉ ሌሎች ኃላፊ የሚመሯቸው፤ ፍትሕ፣ ኢንዱስትሪ እንዲሁም ባህል እና ቱሪዝም ቢሮዎችን ነው። የክልሉን ትራንስፖርት እንዲሁም የውሃ እና ኢነርጂ ቢሮዎችን እንዲመሩ የተሾሙት ደግሞ የተቃዋሚው ባይቶና ፓርቲ ተወካዮች ናቸው። 

ካቤኔውን ዛሬ በይፋ ያስተዋወቀው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፤ የፌደራል መንግስት እና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተፈራረሙት ስምምነት መሰረት የተቋቋመ ነው። የፌደራል መንግስት “የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር” ደንብን በማጽደቅ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር መመስረቱን ያስታወቀው በመጋቢት 14፤ 2015 ነው። 

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በዚሁ ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ የህወሓት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው መሾማቸውን አስታውቆ ነበር። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሹመት የተሰጣቸው አቶ ጌታቸው፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ሲያዋቅሩ “በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችን ውክልና የማረጋገጥ ኃላፊነት” እንደተጣለባቸውም ጽህፈት ቤቱ በወቅቱ ገልጿል። 

ይህን ሹመት ባገኙ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወደ አዲስ አበባ መጥተው የነበሩት አቶ ጌታቸው፤ ከፌደራል መንግስት ጋር ውይይት ሲያደርጉ ቆይተዋል። በሁለቱ አካላት ውይይት ከተነሱ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ በነበረው ለትግራይ ክልል የሚላከው የፌደራል መንግስት ድጎማ በጀት ላይ  ከስምምነት ላይ መደረሱ ተገልጿል። የፌደራል መንግስት ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ለትግራይ ክልል የበጀት ድጎማውን መልቀቅ እንደሚጀምር የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለፋና ቴሌቭዥን ተናግረው ነበር።

ሚኒስትር ዴኤታው በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች ከዚህ ሳምንት ጀምሮ “ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ይገባሉ” ሲሉ ጥቆማ ሰጥተዋል። እርሳቸው እንዳሉትም አቶ ጌታቸው እና ልዑካቸው ወደ መቐለ ከተማ ከተመለሱ ከቀናት በኋላ፤ 17 የቢሮ ኃላፊዎችን እና ስምንት የካቢኔ ሴክሬተሪያት ኃላፊዎችን የያዘ የጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ይፋ ተደርጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]