በአማኑኤል ይልቃል
ከስራቸው ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር በዋሉ ጋዜጠኞች ላይ የቀረቡ ክሶችን፤ የፍትህ ስርዓቱ “በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ብቻ” በመመራት እንዲመለከታቸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ጠየቀ። በቁጥጥር ስር የዋሉ ጋዜጠኞች “እንደማንኛውም ተከሳሽ” ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቅዶባቸው እንዲታሰሩ መደረጉንም፤ ምክር ቤቱ “በምንም መለኪያ ተቀባይነት የሌለው” ሲል ተችቷል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ይህን ያለው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጋዜጠኞች ላይ የተፈጸሙ እስሮችን እና የፍርድ ቤት ሂደቶቻቸውን አስመልክቶ ዛሬ ሰኞ ሚያዝያ 9፤ 2015 ባወጣው መግለጫ ነው። ምክር ቤቱ በዚሁ መግለጫው፤ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ውስጥ የሚሰሩ ጋዜጠኞች በተደጋጋሚ “ከሕግ አግባብ ውጪ መያዝ እና መታፈናቸውን” እንዲሁም በሚሰሩባቸው ተቋማት ላይ “ያለፍርድ ቤት ማዘዣ ወረቀት ብርበራ” መፈጸሙን እንደተገነዘበ አስታውቋል።
በሚዲያ አማካኝነት ተፈጽሟል በተባለ ወንጀል የተጠረጠሩት እነዚህ ጋዜጠኞች፤ በፖሊስ በቁጥጥር ስር እየዋሉ እና ወደ ፍርድ ቤት እየቀረቡ ያሉት በመገናኛ ብዙኃን አዋጁ መሰረት አለመሆኑንም ምክር ቤቱ ገልጿል። ይህ ድርጊትም “ባለሙያዎች ስራቸውን በነጻነት እንዳይሰሩ፤ እንዲሸማቀቁ እና የፕሬስ ምህዳሩ የበለጠ እንዲጠብ” እያደረገ መሆኑን በዛሬው መግለጫው ጠቅሷል።
ከሁለት ዓመት በፊት የወጣው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ፤ “በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም አካል፤ በወንጀል ስነ ስርዓት የሕግ ድንጋጌዎች መሰረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ፤ ክሱ በቀጥታ በዓቃቤ ሕግ አማካኝነት ለፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለበት” የደነገገ ነው። አዋጁ ይህን ቢልም፤ “ከሕጉ መንፈስ ተቃራኒ በሆነ መንገድ የዜጎች መብት በፍትህ አካላት በተደጋጋሚ እየተጣሰ” መሆኑን ምክር ቤቱ በመግለጫው አመልክቷል።
“ጋዜጠኞች ተከስሰው ሲቀርቡ በመገናኛ ብዙኃን አዋጁም መሰረት መከሰሳቸው ግልጽ ሆኖ ሳለ፤ በስራ ገበታቸው ላይ ሆነው ጉዳያቸውን መከታተል እንዳይችሉ፣ እንደማንኛውም ተከሳሽ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ እንዲታሰሩ ማድረግ በምንም መለኪያ ተቀባይነት የለውም” ሲል በመግለጫው የተቸው ምክር ቤቱ፤ “ስለሆነም ከሕግ አግባብ ውጪ የታሰሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ እንጠይቃለን” ሲል በጉዳዩ ላይ ያለውን አቋም አስታውቋል።
የሰሞኑን የጋዜጠኞች እስር በተመለከተ ባለፈው ሳምንት መግለጫዎች ያወጡት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበርም ተመሳሳይ አቋም ማንጸባረቃቸው ይታወሳል። ባለፈው አንድ ወር ብቻ ስምንት ጋዜጠኞች እና አንድ የማህበረሰብ አንቂ ለእስር መዳረጋቸውን የገለጸው ኢሰመኮ፤ በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ተፈጽሟል በተባለ ወንጀል የተጠረጠሩ ታሳሪዎች “በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ” ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቆ ነበር። የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበሩ በበኩሉ፤ በአሁኑ ወቅት የተያዙት ጋዜጠኞች የታሰሩት “ያለ ምንም የህግ አግባብ” መሆኑን ጠቅሶ፤ መንግስት ባለሙያዎቹን “በአስቸኳይ እንዲፈታ” ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በዛሬው መግለጫው፤ መንግስት “የወንጀል ተግባሮችን ሁሉ የመከላከል፣ የመመርመር እና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለበት” እንደሚረዳ ገልጿል። ሆኖም ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት የሚከናወኑ ተግባራት ግን “ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በማያጠብ እና የዜጎችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ተሳትፎ በማያቀጭጭ መልኩ” ሊተገበሩ እንደሚገባ አሳስቧል። መንግስት ህግን ለማስከበር የሚወስዳቸው ማንኛቸውም ተግባራት “በህግ አግባብ ብቻ” መመራት እንዳለባቸውም አጽንኦት ሰጥቷል።
የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤቱ “ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት መሰረት እንዲኖረው፤ የፍትሕ ስርዓቱ በመገናኛ ብዙኃን አዋጁ ድንጋጌ ብቻ በመመራት ሕገመንግስታዊ ግዴታውን እንዲወጣ እንጠይቃለን” ሲልም ጥያቄ አቅርቧል። ጋዜጠኞችን ተጠያቂ የሚያደርግ ክስ በሚኖርበት ጊዜ ጉዳዩ የሚታይበት “የእርስ በእርስ ቁጥጥር ስልት” መዘርጋቱን ያስታወሰው ምክር ቤቱ፤ የፍትህ ስርዓቱ “አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም በሕግ መንግስቱ የተረጋገጠውን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሊያስከብር ይገባል” ብሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)