ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ መግባት የሚፈልጉ” ያሏቸውን ኃይሎች፤ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳሰቡ

በአማኑኤል ይልቃል

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ እየገቡ መፈትፈት የሚፈልጉ” ያሏቸውን “ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ኃይሎች” ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳሰቡ። “በመገዳደል፣ በመሰዳደብ እና በመናናቅ” ለማሳካት የሚፈለግ “የፖለቲካ ዓላማ” ውስጥ ይሳተፋሉ ያሏቸውን ባለሀብቶች፣ በውጭ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና በሀገር ውስጥ ያሉ ወጣቶችንም “ደጋግማው እንዲያስቡ” ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህንን ማሳሰቢያ ያስተላለፉት፤ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዳውሮ ዞን የተገነባው “የሃላላ ኬላ ሪዞርት”  ዛሬ ሰኞ ሚያዝያ 23፣ 2015 በተመረቀበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ንግግራቸው፤ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ  የተገደሉትን የአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የአቶ ግርማ የሺጥላን ጉዳይ አንስተዋል። 

አቶ ግርማ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከመሃል ሜዳ ወደ ደብረ ብርሃን ከቤተሰብ እና የግል ጥበቃዎቻቸው ጋር እየተጓዙ በነበረበት ወቅት፤ “በታጠቁ  ጽንፈኛ ኃይሎች” በተፈጸመባቸው ጥቃት” መንዝ ጓሳ በተባለ አካባቢ መገደላቸውን የክልሉ መንግስት በዕለቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር። በዚሁ ጥቃት አቶ ግርማን ጨምሮ አምስት ሰዎች መገደላቸውንም ክልሉ በወቅቱ ገልጿል። 

የአቶ ግርማ አስክሬን ትላንት እሁድ በአዲስ አበባ ወዳጅነት አደባባይ ሽኝት ከተደረገለት በኋላ የቀብር ስነ ስርዓቱ በመሀል ሜዳ ከተማ ተፈጽሟል። በትላንቱ የአስክሬን ሽኝት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የተገኙ ሲሆን የአበባ ጉንጉንም አስቀምጠዋል። 

አብይ በዛሬው ንግግራቸው፤ የብልጽግና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑትን የአቶ ግርማን ግድያ “አላግባብ መሰዋት” ሲሉ ጠርተውታል። አቶ ግርማን “ገና ሮጦ ያልጠገበ ወጣት፣ ለህዝቡ ለሀገሩ ብዙ ሊያገለግል የሚችል፣ ልጆች ቤተሰቦች ያሉት” ሲሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “በሰላም ቤተሰቡን ሊጠይቅ እየነዳ የሄደ፤ ጀግና መሳይ ፈሪዎች ተደብቀው በጥይት ገደሉት” ብለዋል። ይህንን ድርጊት የፈጸሙት  ሰዎች፤ የሚፈልጉትን ነገር “በሀሳብ ብልጫ” “ብዙሃንን አሳምነው መከወን እንደማይሳካላቸው ያሰቡ” መሆናቸውን ተናግረዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ግርማ በተገደሉበት ዕለት ባወጡት መግለጫ ተመሳሳይ አንጸባርቀው ነበር። አብይ በሐሙሱ መግለጫቸው፤ “ሐሳብን በሐሳብ ማሸነፍ ያቃታቸው” ሲሉ የጠሯቸውን አካላት እና “ነውጠኛ ጽንፈኞችን” ለአቶ ግርማ ግድያ ተጠያቂ አድርገዋል። በእነዚህ አካላት ተፈጸመ ያሉትን ግድያ “አስነዋሪ እና አሰቃቂ” ሲሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ተግባሩ “ጽንፈኝነትን በጊዜ ታግለን ካላስወገድነው ወደ መጨራረስ እንደሚወስደን ጉልህ ማሳያ ነው” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተው ነበር። 

በዛሬው የሃላላ ኬላ ንግግራቸው ተመሳሳይነት ያለው መልዕክት ያነሱት አብይ “ይህ አይነት ልምምድ ለኢትዮጵያ አደገኛ ነው” ብለዋል። “ከዚህ ቀደም ኖረንበታል። በቀይ ሽብር፣ ነጭ ሽብር የሆነው ነገር ይሄ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል። ሰው ገድሎ “በሰላም መኖር” እና “ስልጣን መያዝ” እንደማይቻል የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “በመገዳደል፣ በመሰዳደብ፣ በመናናቅ” ለማሳካት የሚፈለግ የፖለቲካ ዓላማ “የከሰረ” እና “ወደ ድል የማይወስድ” መሆኑን አስገንዝበዋል።

“በዚህ ጉዳይ ላይ የምትሳተፉ ባለሀብቶች፣ በውጭ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን፣ በሀገር ውስጥ ያሉ ወጣቶች ደጋግማችሁ እንድታስቡ አደራ ልላችሁ እፈልጋለሁ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል። እንደዚህ አይነት መሰል ጉዳዮች በሚፈጠሩ ጊዜ፤ የሚመሩት መንግስት “ከዚህ ቀደም ያለውን አቋም” በመድገም “ህግ የማስከበር ኃላፊነቱን” እንደሚወጣም አብይ ተናግረዋል። መንግስት ህግ የማስከበር ሂደትን በሚያከናውንበት ጊዜም “መላው የኢትዮጵያ ህዝብ” ተባባሪ እንዲሆንም ጠይቀዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ንግግራቸው “ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ኃይሎች” ሲሉ ለጠሯቸው አካላትም ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። እነዚህን ኃይሎች “ኮሽ ባለቁጥር በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ እየገቡ መፈትፈት የሚፈልጉ” ሲሉ የገለጿቸው አብይ፤ ከእንደዚህ አይነት ድርጊታቸው “እንዲሰበሰቡ” እና “እንዲቆጠቡ” አሳስበዋል። “ኢትዮጵያን በማበጣበጥ፣ በማባላት የሚገኝ ትርፍ እንደሌለ አውቀው፤ የእኛን ጉዳይ ለእኛ መተው እንዲችሉ ማሳሰብ እፈልጋለሁ” ሲሉም ጠንከር ያለ መልዕክት አስተላልፈዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)